Sunday, July 7, 2013

ኢህአዴግ ስለ ሰላማዊ ትግል ያለው አመለካከት

        ኢህአዴግ ስለ ሰላማዊ ትግል ያለው አመለካከት

    ኢህአዴግ ከአፈጣጠሩ በሰላማዊ ትግል እምነት የሌለው በመሆኑ ስልጣንን በትጥቅ ትግል መያዙ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የህዝቡን ልብ ለማማለል 4 ዓመት የሽግግር መንግስት ቆይታ በኋላ ባፀደቀው ህገ መንግስት በሀገሪቱ የመደበለ ፓርቲ ሥርዓት መመስረቱንና ሐሳብን በነፃነት መግለፅ እንደተረጋገጠ ይፋ አድርጐ ነበር፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ቃሉን ማክበር ቢሳነውም፤ የመንግስት ሥልጣን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚያዝ መሆኑን መግለፁ አይዘነጋም፡፡
      በኢህአዴግ አመለካከት ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ማለት እርሱ በሚፈቅደው ርዕሰ ጉዳይ እና በሚመራው መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት ይገነዘባል፡፡ የመደበለ ፓርቲ ሥርዓትንም ቢሆን የምስክር ወረቀት ያላቸው ብዙ ፓርቲዎች በሀገሪቱ መኖራቸውን እንጂ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ከህዝቡ ጋር እንዲወያዩና አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውንና ፕሮግራሞቻቸውን እንዲያቀርቡ አይፈቅድም፡፡ ምናልባት በሁኔታዎች አስገዳጅነት ቢፈቅድ እንኳ ለእንቅስቃሴያቸው ሌላየህግ ገደብያለው ቀይ መስመር ያሰምራል፡፡ ነገር ግን የመጫወቻ ሜዳውን አጥብቦ በየጊዜው የመንግስት ስልጣን የሚያዘው በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ይደሰኩራል፡፡
       ምናልባት እንደ 1997 . ጠባብ የምርጫ ምህዳር በመፍጠር ቢሸነፍ የመጣበትን የትጥቅ ትግል ያስታውስና ማወራረጃ በማድረግ የተፎካካሪዎቹን ትግል ለመቀልበስ ይተጋል፡፡
      በርግጥ ሰላማዊ ትግል ከትጥቅ ትግል ያላነሰ ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደሚያስከፍል ቢታወቅም አዋጭነቱ ላይ ግን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህም ከሀገሪቷ አምባገነን ሥርዓትን በማስወገድና በማንኛውም እንቅስቃሴ ህዝባዊ ተሳትፎን እንደሚያጐለብት ይታወቃል፡፡ ስለዚህ
ለዜጐች ተጠቃሚነት ሰላማዊ ትግል ትልቅ አስተዋፅዖ አለው፡፡
     ለአብነትም የአሜሪካው ማርቲን ሉተርኪንግ፣ የህንዱ ማህተመ ጋንዲና የደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላንና ሀገሮቻቸው አሁን ያሉበትን ደረጃ ማየት በቂ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግና አመራሮቹ ግን የመጡበት መንገድ የትጥቅ ትግል በመሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን አምኖ ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰላማዊ ትግል የሚያደርጉትንና ለማድረግ የሚፈልጉትንም ወደ ሌላ የትግል አቅጣጫ (ወደ ትጥቅ ትግል) እንዲያዘነብሉ እያስገደደ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ቀድሞም ቢሆን ኢህአዴግ የሰላማዊ ትግል እውነታን የሚረዳው በህግ እንዳፀደቀው ሳይሆን እንደራሱ ፍላጐትና ልምድ በመሆኑ ነው፡፡


ሰላማዊ ትግል በኢትዩጵያ
   የስልጣን ሽግግሩ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲከናወን ሁሉም የሚመኝ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ከችግር አልጸዳም፡፡የውጪ ጠላትን ያንበረከክንበትን የጦር ጀብደኝነት ስሜት በሀገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ላይም መተግበራችን አንዱ አንዱ እንቅፋት ነው፡፡ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታትና ጠቃሚውን ከመውሰድ ይልቅ የአልሸነፍ ባይነትን ባህል የሙጥኝ ማለታችን ለሰላማዊ ትግሉ አለመሳካት ዋነኛው ነው፡፡
     ሌላው ገዥዎች ስልጣንን የህዝብና የሀገር አገልጋይ መሆኛ አድርጎ ከመቀበል ይልቅ እስከ ዕለተ ሞት(እንደ አቶ መለስ ዜናዊ) ድረስ የግል ርስት አድርጎ የመቁጠር አባዜ አንዱ ለሰላማዊ ትግል አለመሳካት ምክንያት ነው፡፡
     ተቃዋሚዎች የሚጠቀሙትን የሰላማዊ ትግል ስልት ከህዝቡ ባህልና ወግ፣ ከጊዜው ትውልድና ቴክኖሎጂ ጋር አጣምሮና አስማምቶ ከመጠቀም ይልቅ ጊዜ ያለፈባቸውንና በተቃራኒ ጎራ ያለው ተቀናቃኛቸው የሚያውቃቸውን የተወሰኑ የምዕራባዊያን ሰላማዊ የትግል ስልት ብቻ በመጠቀም ድልን መናፈቃቸው ሂደቱን ስኬት አልባ አስመስሎታል፡፡ በአንጻሩ ህዝቡ 1997. የምርጫ ወቅት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ያሳየውን ቁርጠኝነትባለመድገሙ ዛሬ የመከራ ጌዜን እንዲገፋ አስገድዶታል፡፡ በአጠቃላይ ሰላማዊ ትግሉ ውጤታማ ይሆን ዘንድ ገዥው ፓርቲ ቢያንስ በወረቀት ላይ ያሰፈራቸውን ህጎች ቢተገብርና ዓርዓያ ቢሆን፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ ከሀገራችን ህዝብና ከትውልዱ ጋር ሊሄዱ የሚችሉ የመታገያ ስልቶችን ቢቀይሱና ቢተገብሩ፣ ህዝቡም ሌላ ሰው ነፃ እንዲያወጣው ከመጠበቅ ይልቅ ራሱን ነፃ ለማውጣት ቢሞክርና ላመነበት ተቃዋሚም አስፈላጊውን ድጋፍ ቢያደርግ ሰላማዊ ትግሉ ባጭር ጊዜ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሰላማዊ ትግሉ በአግባቡና በጊዜው ከተጠቀሙበት መስዋዕትነትን በማስከፈሉ ከባድ ቢመስልም ከውጤቱ አንፃር ሲታይ ግን ቀላል ነው ለማለት እንደፍራለ፡፡
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ

ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!



No comments: