Monday, July 29, 2013

ዓለም አቀፉ ተቃውሞ በልዩ ስኬት ተጠናቋል!

   ዓለም አቀፉ ተቃውሞ በልዩ ስኬት ተጠናቋል!

እሁድ ሐምሌ 21/2005 አለም

መሰል አለም አቀፋዊ አንቅስቃሴዎች ይቀጥላሉ!

በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን መጠነ ሰፌ የዴሞክራሲያው መብት.ረገጣዎችን ለማውገዝና መንግስት ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጫና እንዲያሳድር በማሰብ የተካሄደው አለም አቀፍ የተቃውሞ እንቅስቃሴ
በአስደናቂ ትእይንቶች ታጅቦ ተጠናቋል፡፡ 

ይህ ክፍለ አሕጉራት እና አሕጉራት ሳገድቡት የተካሄደው የተቃውሞ ትእይንት በርካታ አገራትን ያካተተ ሲሆን በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም በስፋት ተሳትፈውበታል፡፡በተቃውሞዎቹ ትእይንቶች በዋነኝነት የመንግስት
በሃይማኖት ውስጥ የሚደረግ ያልተገደበ ጣልቃ ገብነት በስፋት ተወግዟል፡፡

በቁጥር የበረከቱ ሰልፎች በአንድ ቀን ካስተናገዱ አገራት በዋነኝነት የምትጠቀሰው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ናት፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ መዲና ዋሺንግተን ዲሲ መጀመሪያ በተደረገውና ከአንድ ሺ የሚልቁ ሰዎች በተገኙበት የተቃውሞ ትእይንት ወሳኝ አገራዊ መልእክቶች መተላለፍ ችለዋል፡፡ በዋሺንግተን ዲሲ ነጩ ቤተ-መንግስት (ዋይት ሐውስ) ፌት ለፌት የተደረገው የተቃውሞ ትእይንት ጁምአ እለት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከአሱር ሰላት በኋላ ተጀምሮ
ለሁለት ሰዓታት ከዘለቀ ትእይንት በኋላ ተጠናቋል፡፡ በእለቱ ድምጻችን ይሰማ፣ ሕገ መንግስቱ ይከበር፣ ኮሚቴዎች ይፈቱ፣ የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል የሚሉና ሌሎችም በአማርኛና በእንግሊዛኛ ቋንቋዎች የተጻፉ መፈክሮችና የመሪዎቻችንን ምስሎች የያዙ ትላልቅ ባነሮች ከፍ ብለው ታይተዋል፡፡ በሰልፉ ላይ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደተለመደው ከሙስሊሞች ጎን መሆናቸውን ለመመስከር በቦታው ተገኝተው ነበር፡፡

በሌላው የአሜሪካ ግዛት ዳላስ ቴክሳስ የተቃውሞ ትእይንት የተደረገው በዚያው እለት ጁምአ ነበር፡፡ በግዛቷ የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጎዳና ላይ በመውጣት ባደረጉት ተቃውሞ በአገር ቤት ወንድሞቻቸው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደረስ በደል እንዲገታና አክራሪነትን በመዋጋት ስም ሙስሊሙ ላይ እየተሰነዘረ ያለው የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡ በሰልፉ ላይ የተገኙት ከ500 የሚልቁ ሙስሊሞች ስሞታቸውን ለመንግስት ማስገባታቸው የተገለጸም ሲሆን ወቅታዊውን የሙስሊሞች ጥያቄ የሚያንጸባቅሩ መፈክሮች ሲያስተጋቡም ተሰምቷል፡፡ እንደሌሎቹ ተቃውሞዎች ሁሉ በዳላሱ ተቃውሞው የሴቶች ተሳትፎ አበረታች
ነበር፡፡ ትናንት ቅዳሜ የወጣው የአካባቢው ጋዜጣ ‹‹ዳላስ ዴይሊ›› ለተደረገው ሰልፍ ሽፋን በመስጠት የተቃውሞውን መነሻና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ በደሎችን አትሞ አውጥቷል፡፡

በአሜሪካ ሰሜን ምእራብ አቅጣጫ
የምትገኘውና ከዋናው ከተማዋ ስድስት ሰዓት የአየር ጉዞ የምትርቀዋ የሲያትል ከተማ እንደሌሎቹ የአሜሪካ ከተሞች በዚህ ሳምንት ማገባደጃ ደማቅ ተቃውሞ አስተናግዳለች፡፡ በከተማው የሚኖሩ ዜጎች ድምጻችን ይሰማ፣ መብታችን ይከበር፣ ሃይማኖት በኋይል አይጫንም የሚሉና ሌሎችም መሰል መፈክሮችን በማንገብ ጎዳና ላይ ባደረጉት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

በሌላዋ የአሕጉረ ሰሜን አሜሪካ አገር የሆነችው ካናዳ በአለም አቀፉ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በመቀላቀል ተቃውሞዋን አሰምታለች፡፡ በአገረ
ካናዳ በሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በካናዳ ዋና ከተማ ቶሮንቶ በመሰየም ነበር ተቃውሞውን
ያሰሙት፡፡ ተቃውሞው የተካሄደው በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽ/ቤት ፌት ለፌት ሲሆን መልእክታቸውን ለካናዳና ለኢትዮጵያ መንግስት አድርሰዋል፡፡ በተካሄደው ተቃውሞ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን መፈክሮቻቸውን ይዘውና መንግስትን ተቃውሞው ያደረጉት ተቃውሞ በርካታ ዜጎች የተገኙበትና ይበል የሚያሰኝ ሞራል እና ወኔ የታየበት ነው፡፡ 

በአውስትራሊያ መዲና ሜልቦርን የተደረገው ተቃውሞውም ሌላው
የትእይንታችን አካል ነበር፡፡ በሜልቦርን ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ቅዳሜ እለት ባካሄዱት ተቃውሞ አገር ቤት ያለውን የመብት ረገጣ በጽኑ ያወገዙ ሲሆን አለም አቀፉ ማህበረሰብና የአውስትራሊያ መንግስትም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ በሰልፉ ላይ ከተቃውሞው ጎን ለጎን ለተሳታፊዎች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የመብት እንቅስቃሴ ላይ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡

ከክፋላተ አሕጉራትና አሕጉራት ተሻግሮ በበርካታ ከተሞች የተደረገው ተቃውሞ አፍሪካንም ደርሷት ነበር - ደቡባዊቷ አፍሪካን፡፡ በደቡብ አፍሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ በዚህቺው አገር የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ወቅቶች ለሙስሊሙ ወገናቸው አጋር
መሆናቸውን ሲያሳዩ ከመቆየታቸውም በላይ በአገር ቤት የሚደረገውን የመብት ረገጣ ደጋግመው ሲቃወሙም ቆተዋል፡፡ ባለፈው ጁምአም ይሄን እንቅስቃሴያቸውን በይፋ ደግመውታል፡፡ በርካታ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እና የሌላ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በጀሀንስበርግ በጋራ የጁምአ ሰላት በመስገድ ከሰላቱ መጠናቀቅ በኋላ
ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ በተቃውሞአቸው የተገኙ በርካታ ዜጎች
ሙስሊሞች በእምነታቸው ምክንያት
የሚደርስባቸውን አፈናና በደል በማውገዝ መንግስት ከዚህ አፋኝ ድርጊቱ እንዲታቀብ ጠይቀዋል፡፡ በተቃውሞ ትእይንቱ በሙስሊሙ ጉዳይ ዙሪያ ገለጻም ተደርጓል፡፡

ከጎዳና ላይ ተቃውሞዎች ውጪ በቤት ውስጥ ተቃውሞና በሌሎችም ስነ ስርአቶች የተካሄዱ ትእይንቶች በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ውጤታማና አመርቂ ነበሩ፡፡ በተለይ በበርካታ የአውሮፓ ከተሞች በሚገኙ ኮሚኒቲዎች አማካኝነት የተካሄዱት ከበር መልስ ተቃውሞዎችና ኢፍጣር ፕሮግራሞች በውጪ የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በአገር ቤት
የምናደርገውን እንቅስቃሴ በሙሉ አጋርነት እየደገፉ መሆኑን አመላክቷል፡፡ 

በጀርመን፣ በስዊድን፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በሆላንድ፣ በኖርዌይ፣ በስዊድን፣ በቤልጂየም እና በሳዑዲት
አረቢያ ፕሮግራሞቹ ተካሄደዋል፡፡ የአመሪካዋ ሎስ አንጀለስ ከተማም ተመሳሳይ ሂደት አስተናግዳለች፡፡

በእነዚሁ አገራት የሚገኙ ኮሚኒቲዎች
ባዘጋጇቸው መርሐግብሮች ላይ ተመሳሳይ መርሐግብሮች ማዘጋጀታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ በሳኡዲ አረቢያ እስከ ዛሬ ምሽት ድረስ በዘለቀው መርሐግብር የኢፍጣር፣ የኢባዳ፣ በጋራ የመሰባሰብና ተቃውሞን በቤት ውስጥ
የማሰማት ትእይንቶች ተካተዋል፡፡ በሳኡዲ የሚገኙ በርካተ ሙስሊሞች ሙስሊም ኢትዮጵያውንን በማሰብም መካ ድረስ በመሄድ ጸሎት አድርሰው ተመልሰዋል፡፡

በዚህ በአለም አቀፍ ደረጃ በተደረገው ተቃውሞ እኛ ሙስሊም ኢትዮጵያውን አሁንም አንድ መሆናችንና ለተነሳንለት የፍትህ እና የእምነት ነጻነት ጥያቄ እስከመጨረሻው ድረስ ለመዝለቅ በቂ መልእክት ያስተላለፍን ሲሆን እነዚህ ጽናትና ቁርጠኝነታችንም በቀጣዮቹ ጊዜያት ቀጥለው ይሄዳሉ፡፡ መንግስት የአገሪቱን የበላይ ሕግ ሕገ መንግስቱን በመጣስ በሃይማኖት ጣልቃ በመግባትና ዜጎች የማይሹትን እምነት በግድ አንዲቀበሉ በማስገደድ ተግባሩ እስካልተገታ ድረስና ይህንኑ የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ወህኒ ቤት የገቡ መሪዎቻን እስካልተፈቱና ጥያቄዎቻችን.እስካልተመለሱ ድረስ እንቅስቃሴያችን እያየለ እንጂ እየቀዘቀዘ እንደማይሄድ ከጁምአ ጀምሮ ባካሄድናቸው አለም አቀፍና አስደማሚ ትእይንቶች በድጋሚ አስመስክረናል፡፡ 

በእርግጥም እንዳልነው በአዲስ አበባ ኑር መስጂድ ተሰራው ታሪክ በሌሎችም አገራትና አካባቢዎች ተደግሟል፡፡

No comments: