Monday, July 29, 2013

በብሔርተኝነት ዙሪያ ያለ የተሳሳተ ግንዛቤና እንድምታዎች

ትላንት የታሰሩት ‹‹የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ›› ጠበቃ የሆነው ተማም አባቡልጉ በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉና ሕገመንግሥቱ መካከል ያሉ መጣረሶችን አስመልክቶ በአንድነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ያቀረበውን ጽሑፍ ለማድመጥ ሄጄ ፓርቲው 2003 ያሳተመውንየአምስት ዓመት ስትራቴጂመጽሐፍ ገዝቼ ተመለስኩ፡፡ በውስጡ የብሔር፣ ብሔረሰቦችን ጉዳይ የሚያትትበትን ጥቂት አንቀጾች ካነበብኩ በኋላ ቀንጭቤ ማካፈል እንዳለብኝ ስለተሰማኝ እነሆ፡- 

‹‹በብሔርተኝነት ዙሪያ ያለ የተሳሳተ ግንዛቤና እንድምታዎ 

‹‹
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር እንደመሆኗ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር በሀገራችን ፖለቲካ ትልቅ ስፍራ እንደያዘ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰብ መብት መከበር በቋንቋ የመናገር መብት ብቻ አይደለም፡፡ በፖለቲካ የመወከልና የመደመጥ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፍ አድሎን የማጥፋትና ፍትሕንና ዕኩልነትን የማንገሥ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ስስ ጉዳይ በሚገባ ሊያዝ ይገባዋል፡፡ 

‹‹
የብሔር ጉዳይ አያያዝን በሚመለከት በአገራችን ሁለት ጫፍ የረገጡ አዝማሚያዎች ይታያሉ፡፡ አንዱ ጫፍ ለኢትዮጵያ አንድነት እንጨነቃለን ከሚሉ ግን የብሔር መብትን ለመቀበል ከሚቸገሩ ወገኖች የሚመጣ ሆኖ ጉዳዩን የማሳነስና የማጣጣል ብሎም የብሔር መብት ጥያቄ የሕዝብ መብት ጥያቄ መሆኑን የመካድ ዝንባሌን የሚያጠቃልል ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች የሕዝብና የአገራችን አንኳር ጉዳይ መሆኑን በመቀበል ፈንታ የየብሔሩ ልሂቃን የሥልጣን ጥማቸውን ለማርካት ሲባል የፈጠሩት ችግር አድርገው ያነቡታል፡፡ ልሂቃኑም አይለጥጡትም ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ግን የጉዳዩን ክብደትና በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ስፍራ ለማሳነስ ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡ 

‹‹
ሁለተኛው ጽንፍ የረገጠው አመለካከት የብሔር ብሔረሰብ መብትን ለማስጠበቅ እንታገላለን ከሚሉ ወገኖች የሚመጣና የብሔር መብት መከበርን ከአገር አንድነትና አብሮነት ነጥሎ የሚመለከት ዝንባሌ ነው፡፡ ከነዚህ ወገኖች ውስጥ ጉዳዩን በማክረር ውጤቱ መገንጠል እንዲሆን የሚፈልጉ አሉ፡፡ በግልጽ መገንጠልን እንደዓላማ ያነገቡም አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች እኛ ያልነው ካልሆነ በማለት አንድነትን በመያዣነት ያግቱታል (ሆስቴጅ ያደርጉታል)፡፡ ሁሉም የየራሱን መብት እያጠበቀና እያከረረ ከሄደ እያንዳንዱ ብሔረሰብ፣ ከአጠገቡ ካለ ሌላ ብሔረሰብ እየተናከሰ እንደሚኖር እና ከአንድነቱ መፍረስ ጋራ ሠላምም እንደሚደፈርስ ያለመገንዘብ ችግር አለባቸው፡፡ 

‹‹
ሁለቱም አመለካከቶች በሐሳብ ብቻ ሳይሆን ልዩነታቸው በአደረጃጀት መልክ ይታያል፡፡ የመጀመሪያው ኅብረብሔራዊ አደረጃጀት የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ብሔራዊ ወይም ክልላዊ አደረጃጀት መልክ የያዘ ሆኖ አንዱ ከሌላው ጋራ አብሮ መሥራትና መኖርን የማይቀበሉ ናቸው፡፡ 

‹‹
በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በብሔር/ብሔረሰብ መብት ማስከበር ዙሪያ ያለውን ልዩነት ማጥፋት አይቻል ይሆናል፡፡ ጫፍ ከረገጡት ሁለት አመለካከቶች ወጣ ያለና የአገር አንድነትን እና የብሔረሰቦች ዕኩልነትን የሚያረጋግጥ አማካይ መስተጋብር መቅረጽና አብዛኛው ሕዝብ ወደዚህ አስተሳሰብ እንዲመጣም መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በአደረጃጀትም እንደዚሁ ኅብረ ብሔራዊ እና ክልላዊ አደረጃጀቶችን (ያቀናጀ) ያስተሳሰረ አንድ አገር አቀፍ መዋቅር ለመፍጠር መሥራት ይገባል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ በአንድ ድምፅ የኢሕአዴግን አገዛዝ እንዳያስወግድ እንቅፋት እየሆነና ለቀጣይነቱ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው፡፡ 

‹‹
ክልላዊና አካባቢያዊውን ገጽታ እንዲሁም አገራዊ ገጽታዎችን ያጣመረ አንድ አገራዊ ስብስብ ወይም ፓርቲ እንዴት ይፈጠራል? ይህንን የሚያንፀባርቅ አደረጃጀትስ ምን መልክ ይኖረዋል?...››

No comments: