Monday, July 29, 2013

የአዲስ አበባ ከተማ አዲሱ አስተዳደር የታጠረውን የሚድሮክ ይዞታ አልታገስም አለ


የአዲስ አበባ ከተማ አዲሱ አስተዳደር የታጠረውን የሚድሮክ ይዞታ አልታገስም አለ

@Ethiopian Reporter

 
ለሚድሮክ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ላከ - የከንቲባ ኩማ አስተዳደር ሥልጣኑን ሲይዝ ይህንኑ ብሎ ነበር

በመሀል አዲስ አበባ ከማዘጋጃ ቤት አጠገብ ላለፉት 15 ዓመታት ታጥሮ በተቀመጠው የሚድሮክ ይዞታ ላይ ትዕግሥት የለኝም ያለው የአዲስ አበባ
ከተማ አዲሱ አስተዳደር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡

አስተዳደሩ ሚድሮክ ፒያሳ አካባቢ አጥሮ ባስቀመጠው መሬት ጉዳይ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም፣ ኩባንያው ግንባታውን ያካሂዳል ብሎ እምነት ባለመጣሉ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ ንግግር መጀመሩ ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የመሬት ባንክና መሬት ማስተላለፍ ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ አቶ ገብረ
ሥላሴ አብርሃ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አረጋግጠው፣ ኩባንያው ለግንባታው መዘግየት የሚያቀርበው ምክንያት በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ በመሆኑ ያንን መልክ ሲያሲዝ ወደዚህኛው ፕሮጀክት እንደሚመጣ መናገሩን ነው፡፡


‹‹
በእኛ በኩል አሳማኝ ምክንያት አይደለም፤›› ሲሉ አቶ ገብረ ሥላሴ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሚድሮክ ኢትዮጵያ በሁዳ ሪል ስቴት ኩባንያ ስም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 1990 .. በፊት 36 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቧል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ በወቅቱ 48 እና 39 ፎቅ ከፍታ ያላቸው መንታ ግዙፍ ሕንፃዎች የመገንባት ዕቅድ ነበረው፡፡ ነገር ግን ሚድሮክ ቦታውን ከወሰደ ጀምሮ አምስት ከንቲባዎች ቢቀያየሩም፣ መሬቱ የታጠረበት አጥር እንጂ ግንባታውን ለማካሄድ አልተንቀሳቀሰም፡፡

በቅርቡ የተሰናበተው የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት አቶ ኩማ ደመቅሳ ሥልጣኑን በተረከቡበት 2001 .. ቦታው ታጥሮ ለዓመታት
መቀመጡ አስተዳደራቸውን እንደሚያሳስበው በመግለጽ፣ የኩባንያውን ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ አል አሙዲንን ጠርተው አነጋግረው ነበር፡፡

የቀድሞው ከንቲባ በወቅቱ የከተማው ሥራ አስኪያጅ ከነበሩት አቶ መኩሪያ ኃይሌ ጋር በመሆን ከሼኩ ጋር ከተወያዩ በኋላ ግንባታው 15 ቀናት ውስጥ
እንደሚጀመርና በዚህ ጊዜ ውስጥ ካልተጀመረ ዕርምጃ እንደሚወሰድ መግባባት ላይ መድረሳቸው በወቅቱ ተገልጿል፡፡ አቶ ኩማና አቶ መኩርያ
በወቅቱ ችግሩ የአስተዳደሩ እንደሆነ በመግለጽ ግንባታው በቅርቡ እንደሚጀመር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ሚድሮክ ከዚህ በኋላ ቀደም ሲል ግንባታውን ለማካሄድ ኃላፊነቱን ወስዶ ከነበረው ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ሥራውን በመንጠቅ ለሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስተላልፎ ነበር፡፡

ሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በዚህ ቦታ ለሚሠራው ሕንፃ የግንባታ ፈቃድ በድጋሚ ወስዷል፡፡ በወቅቱ ለዚህ ግንባታ የተሰጠው መሬት 34,500
ካሬ ሜትር ቦታ ነበር፡፡ ለግንባታውም 148.6 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደተመደበ ተገልጾ ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ የፒያሳ እምብርት በሆነው ቦታ ላይ የግዙፉን ሕንፃ መሠረት ለመጣል ቁፋሮ ቢጀመርም፣ ብዙም ሳይቆይ ቁፋሮው የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ ተስተውሏል፡፡

ነገር ግን 15 ቀናት ውስጥ ካልተጀመረ ዕርምጃ እወስዳለሁ ያለው የአቶ ኩማ አስተዳደር ዕርምጃ ለመውሰድ ሳይደፍር የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመኑን በቅርቡ አጠናቆ ተሰናብቷል፡፡ አሁን ደግሞ አዲሱ አስተዳደር ግንባታው ካልተጀመረ አልታገሰም ማለቱ ተሰምቷል፡፡

No comments: