Tuesday, July 30, 2013

የተቃውሞ‬ ‪ቀን‬

የሐምሌ 19 በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄደውን የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን ተቃውሞን ጨምሮ የረመዷን ወር ሶስት ተከታታይ ጁምዓዎች ፍፁም ጨዋነት በተሞላበት ሥርዓትና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ የሚፈለገውን መልዕክት ማስተላለፍ የተቻለባቸው እጅግ በጣም በርካት ሕዝበ ሙስሊም የተገኙባቸውን ተቃውሞዎች አስተናግደዋል - አልሐምዱሊላህ፡፡

ይህ ያየዝነው ሣምንት የረመዷኑ የመጨረሻው ጁምዓ የሚገኝበት ሳምንት እንደመሆኑ መጠን በአገር አቀፍ ደረጃ ጠንከር ያለና በድጋሜ ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነ ሙስሊም ሕዝብ የሚሳተፍበት የተቃውሞ ቀን ሆኖ ይውላል፡፡ ቀጣዮቹን ተቃውሞዎች የምናካሄደው ከዚህ ቀደም ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን ዳግም ለማንሳትና የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጠን ለመጠየቅ ነው፡፡

የአራተኛው ሳምንት የጁምዓ ተቃውሞ ‹‹የዒባዳና የነፃነት ሳምንት›› በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባና በክልል ከተሞችና በተለመዱ መስጂዶች ተካሂዶ እንደሚውል ይጠበቃል፡፡ የዚህን ሳምንት የተቃውሞ መርሐ ግብር ሳምንቱ የረመዷን የመጨረ አስር ቀናት የሚገኙበት በመሆኑ ከወትሮው ለየት ያለ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የጁምዓ ተቃውሞ በልዩ ሁኔታ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ማድረጋችን እንደተጠበቀ ሆኖ ለዚህ ተቃውሞ ከምናወጣው ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ ባልተናነሰ በግላችንም ሆነ በጀመዓ በመሆን ሁላችንም ፊታችንን ወደ አላሁ ሱብሐነሁ ወተዓላ በማዞር እጆቻችንን ከፍ በማድረግ ለአገራችን ሠላም፣ ለእምነት ነጻነት መከበር፣ ለፍትህ እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ለምናደርጋቸው ፍፁም ሠላማዊ ትግል መሳካት ፈጣሪያችንን መለመን ይኖርብናል፡፡ ብዙዎቻችን በርካታ ወንጀሎች ቢኖሩብንም ከመካከላችን ያሉ ደጋግ (ሷሊህ) አሉና እንደ ሰው ያልሆነው ፈጣሪያችን በነኚህ ሰዎች ዱዓ ሰሰብ እርዳታውን ያቀርብልናልና  በጌታችን ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ከቁርኣን ጋር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትስስር በመፍጠር በርካታ የቁርኣን አንቀፆችን ማንበብ፣ ሰደቃ (ምፅዋት) መስጠት፣ የቲሞችን ማስታወስ፣ ባጠቃላይ ኸይር ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

የተቃጣብንን የእምነት ጣልቃ ገብነት ተከትሎ እያደረግነው ያለነው ፍፁም ሠላማዊ የሆነ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መራዘሙን ባንፈልገውም የተሻለ ነገር ከመምጣቱ ይልቅ መንግስት ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት፣ ዜጎች ሕገ መንስግታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች ያልተገባ ስዕል በመስጠት ብሎም የዜጎችን ጤናማ የመብቴ ይከበርልኝ ትግል ከአክራሪነት፣ ፅንፈኝነትና አሸባሪነት ጋር በመፈረጁና ሁኔታዎች መሻሻል ባለማሳየታቸው እነሆ መስዋዕትነትን እየከፈልን እዚህ ደርሰናል፡፡ ይህ ሂደት ወደ ኋላ ይቀለበስና ሁኔታዎችም ተረጋግተው አደባባይ የወጣው ሙስሊም ሕዝብ ወደ ቤቱ ይመለስ ዘንድ ከመንግስት የሚፈለገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ መብቱ እንዲከበርለት ከሚሻው ሠላም ወዳድ፣ ሕግና ሥርዓት አክባሪ ከሆነው ሕዝብ ጎን መሠለፍ፡፡ ይህ ከሆነ መንግስት ልቦናውን ሰብስቦ የዜጎቹን የፍትህ ጥሪ መስማት ይጀምራል፣ የዜጎቹን ድምፅ ማክበር ይጀምራል፣ ዜጎች ሕግና ሥርዓቱን ተከትለው ያቀረቧቸው ጥያቄዎችም ተገቢውን ምላሽ ያገኛሉ፣ የህዝብ ህጋዊ ውክልና ባለቤት የሆኑ የፍትሕ ታጋዮች ከእስር ነፃ ይወጣሉ፣ መረጋጋትም ይሰፍናል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸው እጅግ ግልጽና ቀላል የሆኑ ሐይማኖታዊ የመብት ጥያቄዎቹ በማያሻማ መልኩ ተገቢውን መልስ ማግኘታቸው የአስቸጋሪው ጎዞ መቋጫ እንደሆነ ያምናል፡፡ እነኚህ ጥያቄዎች እንዳቀራረባቸው ግልፅ የሆነ አረዳድ ተችሯቸው ምላሽ ያገኙ ዘንድ ሕዝበ ሙስሊሙ ሳይሰለችና ሳይደክም ሕግና ሥርዓት የሚፈቅደውን ስልት በመጠቀም እስከ መጨረሻው ድረስ እንደሚጓዝ ዛሬም አበክሮ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

አላሁ አክበር!


No comments: