Wednesday, July 31, 2013

ለኢህአዴግ እድሜ መራዘም የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አስተዋፅኦም

ለኢህአዴግ እድሜ መራዘም የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አስተዋፅኦም የጎላ ነው
ለኢህአዴግ እድሜ መራዘም የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አስተዋፅኦም የጎላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለነፃነትና ዲሞክራሲ ትግሉም መቀዛቀዝ ያሳደሩትና እያሳደሩ ያሉት አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ እንደ ምርጫ ቦርድ መረጃ መሠረት በመላ አገሪቱ (በፌደራል እና በክልል ደረጃ) የተዋቀሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቁጥር እስከ 90 እንደሚደርሱ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ሀቀኛ ወይም ጠንካራ ተቃዋሚ አይደሉም፡፡የህዝብ ብሶት የወለዳቸውእንዳሉ ሁሉ ከኢህአዴግ አብራክ የተከፈሉም ቁጥራቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ እነዚህ በተቃዋሚ ፓርቲ ስም የምርጫ ወቅት ሙሽራውን ኢህአዴግን ለማጀብ የሚታደሙ ናቸው፡፡ ማለዳ ታይተው ማምሻውን የሚከስሙ፣ አድራሻቸው በውል የማይታወቅ ዓላማና ራዕይ የሌላቸው በቁጥር ቀላል የማይባሉ ናቸው፡፡ ለኢህአዴግ መድብለ ፓርቲ አለ እንዲባል ጥሩ መጋረጃዎች ናቸው፡፡

ከቅንጅት መፈረካከስ በኋላ ሲውተረተሩ የምናያቸው ነባርም ሆኑ አዳዲስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁልቆ መሣፍርት በሌላቸው ችግሮች የተተበተቡ ናቸው፡፡ውስጡን ለቄስእንዲሉ ከሚጠሩበት ስያሜና ከምርጫ ቦርድ የህጋዊነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት በዘለለ ውስጣቸው ሲፈተሽ እያሉ አለመኖራቸውን ያረጋግጣል፡፡ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ መተዳደሪያ ደንብ፣ ማኒፌስቶ የፓርቲ አባላት፣ መዋቅራዊ አደረጃጀት የሚለው አይታሰብም፡፡ አንዳንዶቹማ ቢሮ እንኳን የላቸውም፡፡

ብልጭ ድርግም በሚለው የዲሞክራሲና የነፃነት ትግል ውስጥ ውር ውር ሲሉ የምናያቸው ተቃዋሚዎች (አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል) የቆሙበት መሠረት በብሄር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እነሱም ኢህአዴግ በሄደበት መንገድ ነው ጉዟቸውን የጀመሩት፡፡ በመሀከላቸው ሰፊ ገደል አለ፡፡ የአንድን ብሄር ነፃነት ለማረጋገጥ በተነሳ ፓርቲና ብሄራዊነትን በሚያቀነቅን ፓርቲ መሀከል ያለውን የዓላማ ልዩነት ተቃርኖ ለማስታረቅ ስርዓቱን ከመታገል በላይ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ ይሄን ልዩነት በውይይትና ተቀራርቦ በመማማር በጋራ ለመስራት ከስምምነት ቢደረስ እንኳን በውስጣቸው የሚጦዘው የስልጣን ሽኩቻ ብርቱ ጋሬጣ ነው፡፡

በምርጫ 2002 የቅንጅትን መንገድ ተከትሎ ለውድድር ብቅ ያለው መድረክ  ወደ ግንባር መሸጋገሩን ቢያውጅምስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻእንዲሉ ነው፡፡ እንደ ሰንበቴ ጥዋ የመድረክ አባል ፓርቲ መሪዎች የሊቀመንበርነት ቦታውን በየተራ ቢይዙትም እርስ በርስ ከመሻDኮትና ከጋዜጣዊ መግለጫ በዘለለ ሲንቀሳቀሱ አይታይም፡፡ እነዚህ የመድረክ (የግንባር) ስብስብ ፓርቲዎች የራሳቸውን ልዩነት እያጣበቡ ሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለመሳብ አይዳዳቸውም፡፡ ለምሳሌ ከአገሪቱ ህዝብ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘውን የኦሮሞ ብሄረሰብ እንወክላለን የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውህደት ፈጥረው አንድ ጠንካራ ፓርቲ ለመመስረት ለምን ተሳናቸው? አላማቸው የኦሮሞን ህዝብ እምባ ለማበስና ጥቅሙን ለማስከበር ከሆነ ለምን አስር ቦታ መበጣጠስ አማራቸው?በአዲሱ ግንባር ውስጥ የታቀፉትም ሆኑ ብቻቸውን ተገልለው ያሉት ልዩነቶቻቸውን አጥበብውና አቻችለው ለመዋሃድ ለምን አመነቱ?
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ

ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: