Friday, July 19, 2013

የአንድ ፓርቲ ገናናነት የነገሰበት የአገራችን ፓርላማ

የአንድ ፓርቲ ገናናነት የነገሰበት  የአገራችን ፓርላማ

አንድ ፓርቲ የገነነበት ፓርላማ አሉታዊ፡- ፓርላማው በገዢ ፓርቲና ለስልጣናት የተዘጋጁ ህጎችን ብቻ    ያፀድቃል፤ ሁሌም። ፓርላማ ለምን አስፈለገ?” ያሰኛል። አወንታዊ፡- በአለም ህዝብ ፊት “ፓርላማ የሌለው ኋላቀር አገር” ከምንባል ይመስላል


ገዢው ፓርቲና አጋር ድርጅቶች ከ99.9 በመቶ በላይ የተቆጣጠሩት ፓርላማ የፓርላማና የፌደሬሽን ምክርቤት አመታዊ የጋራ ስብሰባ
በነገራችን ላይ የፌደሬሽን ምክርቤት፤ ሙሉ ለሙሉ የኢህአዴግና የአጋር ድርጅት አባላትን ብቻ የያዘ ሆኗል። የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሉበትም። ለነገሩ የክልል ምክርቤቶች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው።  ድሮ ድሮ፤ መንግስት “ዲሞክራሲያዊ ስርአት እየገነባሁ ነው” ብሎ ለማሳመን ምን ይል እንደነበር ታስታውሳላችሁ? “ይሄው ተመልከቱ፤ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ወደ ፓርላማና ወደ ክልል ምክርቤቶች ገብተዋል” ይል ነበር። ዛሬስ? “ይሄው ተመልከቱ፤ ምክርቤቶቹ ከተቃዋሚ ፓርቲ የፀዱ ሆነዋል” ሊባል ነው?
በስልጣኔ ደህና የተራመዱ አገራት ውስጥ እንደምናየው ቢሆን ኖሮ፤ ፓርላማና ምክርቤት ሲባል... የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች መናሃሪያ እንደማለት ነው። አንደኛው ፓርቲ ወይም ፓለቲከኛ፤ ከሌላው በልጦ ለመገኘትና የተሻለ ሃሳብ ለማቅረብ ሲከራከሩ የምናይበት ነው - ፓርላማ ወይም ምክርቤት። 
ስልጣን የያዘው ፓርቲ ወይም ፖለቲከኛ፤ ጠቅላላ የፖሊሲ ሃሳቦችን ሲመርጥ፣ ህጎችን ሲያዘጋጅና እቅዶችን ሲያወጣ፣ ሁሉም ነገር አልጋባልጋ አይሆንለትም። ፓርላማ ውስጥ ከፈታኝ ጥያቄዎች ጋር ይፋጠጣል - ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል በሚሰነዘሩ ጥያቄዎች፣ ሃሳቦችና መከራከሪያዎች። በዚህም ምክንያት ነው፤ በሰለጠኑት አገራት ውስጥ ገዢ ፓርቲዎችና የፖለቲካ መሪዎች፤ የመንግስት እቅድ ሲያወጡም ሆነ ህግ ሲያረቁ፤ በእጅጉ ለመጠንቀቅና ህጉን በጥራት ለማዘጋጀት የሚጣጣሩት። አለበለዚያ ያረቀቁት ህግ ውድቅ ይደረጋል፤ ከዜጎች የሚያገኙት ድጋፍም ይወርዳል - ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ሃሳብ ካቀረቡ። ይህም ብቻ አይደለም። እቅድ ለመተግበር የሚያከናውኗቸው ስራዎችና በየእለቱ የሚፈፅሟቸው ነገሮች ላይም፤ ገዢው ፓርቲና ባለስልጣናቱ በጣም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ጎደሎ ወይም ብልሹ እቅድ፤ ውጤት አልባ ወይም አባካኝ ተግባር ከተገኘባቸው፤ ሸፋፍነው ማለፍ አይችሉም - ፓርላማ ውስጥ “በመረጃና በማስረጃ” ፍርጥርጡ እንደሚወጣ ይታወቃላ። ይህንን  የሚከታተሉ ዜጎችም፤ ለገዢው ፓርቲ ድጋፍ መስጠታቸውን እያቆሙ፤ ወደ ሌሎች ፓርቲዎች ሊሳቡ ይችላሉ - ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ሃሳብና እቅድ፤ አሳማኝ መረጃና መከራከሪያ የሚያቀርቡ ከሆነ። 
ገዢውን ፓርቲና ባለስልጣናትን ለመፈተንበት፣ ለመመርመርና ለመፈተሽ ብቻ አይደለም የፓርላማ አገልግሎት። በዚያው መጠን፤ ዜጎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችንም በግላጭ እንዲፈትሹና እንዲመዝኑ እድል ይሰጣቸዋል - በምርጫ ወቅት ለእያንዳንዱ ፓርቲ ዋጋውን ለመስጠት።
 
በአጠቃላይ ፓርላማ፤ ከየትኛውም ፓርቲ በኩል ለሚመጡ ጉድለቶች መፍትሄ ለማበጀት፤ መልካም ጥንካሬዎችን ደግሞ ለማበረታታት እንደሚጠቅም፤ ከሰለጠኑት አገራት ታሪክ መገንዘብ እንችላለን። ጭፍን ሃሳቦች፣ የተሳሳቱ ህጎች፣ ጎጂ  እቅዶችና የጥፋት ድርጊቶች በጊዜ ውድቅ የሚደረጉበትና የሚወገዱበት እድል ይፈጥራል። ምክንያታዊ ሃሳቦች፣ ትክክለኛ ህጎች፣ ጠቃሚ እቅዶችና የስኬት ድርጊቶች ተቀባይነት አግኝተው እውን የሚሆኑበት እድል ለማግኘትም ያገለግላል - ፓርላማ።
ይሄን ሁሉ የምለው፤ በስልጣኔ ደህና የተራመዱ አገራት ውስጥ የሚገኙ ፓርላማዎችንና ምክርቤቶችን በማየት እንደሆነ ልብ በሉ። የአገራችን ፓርላማና ምክርቤቶች ከዚህ በእጅጉ ይለያሉ። ከ99.9 በመቶ በላይ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ የተያዙ ናቸውና። የአንድ ፓርቲ ገናናነት ሰፍኖባቸዋል። ምን ይሄ ብቻ?
እያንዳንዱ የፓርላማና የምክርቤት አባል፤ ከራሱ ህሊና ውጭ ለማንም ተገዢ እንደማይሆን በህገመንግስት ውስጥ ቢሰፍርም፤ የአገራችን ፓርቲዎች ይህንን አሰራር አይፈቅዱም። በፓርቲ መሪዎች በኩል (በማእከላዊና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች በኩል) ተዘጋጅተው የሚመጡ ሃሳቦችንና ህጎችን በመደገፍ ማፅደቅ እንጂ፤ መቃወምና ሌላ ሃሳብ ማቅረብ አይቻልም። በገዢው ፓርቲ አሰያየም፤ “ማእከላዊነት” ይባላል ይህ የተዋረድ አሰራር። እንግዲህ ፍረዱ። የአንድ ፓርቲ ገናናነት የነገሰበት ፓርላማ ላይ፤ የ”ማእከላዊነት” አሰራት ሲጨመርበት አስቡት። 

እንደምናየው፤ ፓርላማው ሁሌም በገዢው ፓርቲ የበላይ አካላትና በባለስልጣናት ተዘጋጅተው የሚመጡ ሃሳቦችንና ህጎችን ብቻ ያፀድቃል። የተሳሳቱና ጎጂ ህጎችን ውድቅ ለማድረግ፤ በእነዚሁ ምትክም በተሻሉ ሃሳቦች የተረቀቁ ህጎችን ለምቀረብ የሚቻልበት እድል አይኖርም። “ታዲያ፤ ፓርላማ እና ምክርቤቶች ለምን አስፈለጉ?” የሚል ጥያቄ መምጣቱ አይቀርም። የገዢው ፓርቲ የበላይ አካላትና ባለስልጣናት በቀጥታ ህጎቹን ቢያፀድቁና ቢያውጁ ልዩነት አለው? ልዩነት ከሌለውኮ፤ (ሌላውን ሌላውን ሁሉ ጉዳት ለጊዜው ብንተወው እንኳ)፤ በየአመቱ ለፓርላማ የሚመደበው መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ ገንዘብ በከንቱ እየባከነ ነው ያስብላል። ለሌሎቹ ምክርቤቶች የሚወጣውንም ገንዘብ አስቡት። ብዙ ነው። የዜጎች የሚሰበሰብ ቀረጥና ግብር እንደሆነ አትርሱ። በስልጣኔ እንደተራመዱት አገራት የፓርላማ ጥቅሞችን ለማግኘት አለመቻላችን ያነሰ ይመስል፤ በከንቱ ገንዘብ ሲባክን ማየት ያስቆል።ዛሬ የምናየው የሃገራችን ፓርላማ ይዘትና ጥቅም የሌለው፣ ቅርፅና ስም ብቻ


ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ

ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!


No comments: