Saturday, July 13, 2013

ኢትዮጵያ በአለም ወጣቶች ሻምፒዮና የመጀመሪያዋን ወርቅ ሜዳሊያ አገኘች

ኢትዮጵያ በአለም ወጣቶች ሻምፒዮና የመጀመሪያዋን ወርቅ ሜዳሊያ አገኘች


ዩክሬን ዶኔትስክ ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ስምንተኛው የአለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊው መረሰ ካህሳይ በወጣት ወንዶች 2 ሺህ ሜትር መሰናክል አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የመጀመሪያውን ወርቅ ሜዳሊያ አስገኘ።
መረሰ ርቀቱን በ5 ደቂቃ ከ19.99 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ እ.አ.አ በ2006 ዓ.ም ሞሮኳዊው ኦሀዲ ናቢል ይዞት የነበረውን የአለም ወጣቶች ክብረወሰን  በመስበር አንደኛ ወጥቶ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን፣ ለድሉ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ኬኒያዊያኖቹ ኒኮላስ ቤት እና ጀስተስ ላጋት እንደቅደም ተከተላቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመውጣት የብር እና ነሀስ ሜዳሊያዎች ባለቤት ሆነዋል።
በዚሁ ውድድር ላይ ተሳትፎ የነበረው ሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣት ሜካኤል አጽብሀ በርቀት የራሱን ምርጥ ሰአት (5:36.64) በማስመዝገብ አምስተኛ ደረጃን አግኝቶ አጠናቋል።
እስካሁን በተካሄዱት የሶስት ቀናት የአለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድሮች በወጣት ሴቶች 3 ሺህ ሜትር በርሀን ደሜሳ እና ስለእናት ይስማው እንደቅደም ተከተላቸው ያገኟቸውን የብር እና ነሀስ ሜዳሊያዎች ጨምሮ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ሶስት ሜዳሊያዎችን አግኝታ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ ችላለች።

No comments: