Saturday, July 6, 2013

በደቡብ ጎንደር በአሸባሪነት ተጠርጥረው የታሰሩ


በደቡብ ጎንደር በአሸባሪነት ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች ድብደባና እንግልት እየደረሰብን ነው፡፡
በደቡብ ጎንደር በደብረታቦር ከተማ እና በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ከአሽባሪነት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች እስካሁን ክስ እንዳልተመሰረተባቸውና በጊዜ ቀጠሮ እንዳሉ የታሳሪ ሰዎች ቤተሰቦችና ጓደኞች ገለጹ፡፡ 
ከታሰሩት ሰዎች ውስጥ 13 የሚሆኑት በዞኑ ባሉ አዲስ ዘመንና ወረታ ከተማ በሚገኙ ጣቢያዎች ቆይተው ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ ባህር ዳር ከተማ ሁለተኛና አራተኛ ጣቢያ ተዛውረው 25 ቀን በላይ ምንም አይነ ክስ እንዳልተመሰረተባቸው እና በጊዜ ቀጠሮ ብቻ እንዳሉ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ከሶስት ሳምንታት በፊት በስራ ገበታቸው እና በልዩ ልዩ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች በደህንነት ሀይሎች የተያዙት እነኚሁ ግለሰቦች፣ በምርመራ ሰዓት እንግልት እንደሚደርስባቸው፣ እንደሚደበደቡና ‹‹አማራ›› በመሆናቸው ብቻ በምርመራ ሰዓት ማንነታቸውን የሚነካ ስድብ ሁሉ እንደሚሰደቡ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
መጀመሪያ ሲያዙ በደቡብ ጎንደር ፋርጣ ወረዳ ውስጥ በመንግስት ሰራተኛነት ሲሰራ የነበረ አቶ ቴዎድሮስ ሀይሌ የተባለ ግለሰብ ከስራ ገበታው ምንነቱ ባልታወቀ ምክንያት ከስድስት ወራት በፊት ይጠፋል፡፡ ግለሰቡ በረሃ ወደ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ ሂዷል ተብሎ የሚገመት ሲሆን የሚደውልበት ግን የኢትዮጵያ ስልክ ቁጥር ነው፡፡ ከዚያም ከእርሱ ጋር ተደዋውላችኋል በሚል ሰበብ እንደታሰሩ እነኚሁ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

የታሰሩ ሰዎች ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር /ቤት፣ ለሰብዓዊ መብት ጉባዔና ለልዩ ልዩ ተቋማት በጻፉት የአቤቱታ ድራፍት ደብዳቤ ህገ መንግሰታዊ መብቶቻቸው እንደተገፈፉና መንገላታት እንደደረሰባቸው አትተዋል፡፡ የፌስ ቡክና የኢሜል አድራሻና ፓስዎርድ ሁሉ ተቀብለው የግል መረጃዎቻቸው እደተበረበሩ ገልጸዋል፡፡ ግለሰቦቹ በተያዙበት በደብረታቦር፣ በስማዳ እና ላይ ጋይንት ወረዳ፣ አሊያም በክልሉ ፍርድ ቤቶች ጉዳያቸው መጣራት ሲገባው በወረታ እና አዲስ ዘመን ፍርድ ቤቶች ታይቶ ውሳኔ ሳይሰጣው ከዞናቸውና ከሚኖሩበት ወረዳ ውጭ በባህር ዳር ከተማ ፍርድ ቤት በጊዜ ቀጠሮ እንደሚገኙ በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ምርመራውን የሚያደርገው የብሄራዊ ደህንነት አባላት ሲሆኑ ከሳሽ ደግሞ ጉዳዩን የማያውቀው ፖሊስ ሆኖ መቅረቡም አግባብ አይደለም ሲሉ በዚሁ ድራፍት ደብዳቤ አስፍረዋል፡፡ ብዙዎቹ ቤተሰብ የሚመሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ደመወዛቸው በመታገዱ እንዲሁም ነጋዴዎችም የንግድ ድርጅቶቻቸው በመዘጋታቸው ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ እንደሆኑ ጭምር ገልጸዋል፡፡ 
በባህር ዳር 2 እና 4 ዋና ፖሊስ ጣቢያዎች ከታሰሩ ሰዎች መካከል አሸናፊ በላይ፣ ፈቃዱ ጌትነት፣ ታደሰ መንግስቴ፣ ብርቁ አዲሱ፣ የጸዳው ካሳ፣ ንጉሴ አዱኛ፣ ክንዳልም በረካው፣ ታደሰ ባዬ፣ ቴዎድሮስ አለባቸው፣ ሻለቃ አለምነው አየለ፣ ማስረሻ ታፈረ፣ ምስጋነው መልካም፣ ሀብታሙ ወርቁ እና በሪሁን ውበቴ የተባሉ በመንግስት ስራና በንግድ የሚተዳደሩ ግለሰቦች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

No comments: