ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴና በአባይ ወንዝ ጉዳይ እንዲሁም በፀረ ሙስና ትግሉ ስለተከናወኑና ስለሚከናወኑ ተግባራት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ሁለት ጽሑፎች በፖለቲካ ገፅ ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው የኢኮኖሚ ገፅ ደግሞ በእድገትና ትራንስፎሜሽን፤ በግብርና ልማትና ሰራተኞች፤ በአክሲዮን ትርፍ ክፍያ፤ በማክሮ ኢኮኖሚ እና በንግድ ሚዛን አለመመጣጠን፤ በብር የመግዛት አቅምና ምንዛሬ በተለመከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። እድገት፣ ትራንስፎርሜሽንና ግብርና
በዘንድሮው የ2005 በጀት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀማችን በአጠቃላይ በሚታይበት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ያለው። ዕቅዱ በተለያዩ መስኮች ሲታይ የግብርና ልማት የኢኮኖሚው ዋና የጀርባ አጥንት እንደ መሆኑ መጠንና የዕድገታችን ምንጭ በመሆኑ በዘንድሮው የግብርና ስራ እንደሚታ ወቀው በ2004ዓ.ም እና በ2005ዓ.ም የመኽር ስራ ዋናው ነው። በእዚህ መሰረት በቅርቡ የስታስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ ያደረገው መረጃ የሚያሳየን የሰብል ምርታማነት ብቻ ወደ ስድስት በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በተጨማሪም የግብርና ዕድገት ሲባል የመስኖ ልማት፤ የእንስሳት ሀብት ልማትና የደን ልማት ጭምር ሳያካትት ነው። እንደዚሁም የበልግ እርሻ ልማት ገና ውጤቱ ይፋ አልሆነም። እነዚህ ተደማምረው የዘንድሮ የግብርና ልማታችን የተሻለ ሊሆን እንደሚችል እንጠብቃለን። ከእዚህም ባለፈ አሁን ባለንበት ደረጃ የዘንድሮ የግብርና ስራ ሳይሆን 2005 እና 2006 ዓ.ም የመኽር ወቅት ስራ እየተሰራ ይገኛል። ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት በጀት ላይ ዕድገቱ የሚተመን ይሆናል። አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕደገት ውጤቱ የሚታወ ቀው ጥቅምትና ህዳር ወር አካባቢ ነው። ምክንያቱም የዓመቱ መረጃ ተሰብስቦ የሚጠናቀ ቅበት ወቅት ገና በመሆኑ ነው። ለማንኛውም የ2004 እና 2005ዓ.ም ግን የግብርና ዕድገት በጥሩ ሁኔታ ሄዷል ማለት ይቻላል።
የዘንድሮ የግብርና ስራንም በኢህአዴግ ጉባዔ በሚገባ ከገመገምን በኋላ በሙሉ አቅምና ተነሳሽነት የግብርና ልማታችን ለማሳደግ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።የግብዓት አቅርቦትን በተመለከተም ለዘንድሮ የሚሆን የማዳበሪያ ግብዓት ያለችግር ወደ ቀበሌዎች እየደረሰ ነው ያለው። የምርጥ ዘር አቅርቦት አስመልክቶም በምርጥ ዘር ድርጅቶች የሚቀርብ ምርጥ ዘር አለ። እንዲሁም ከእዚህ ቀደም በአርሶ አደሩ የነበሩ የምርጥ ዘር ዝርያዎች አሉ። እነዚህን አርሶ አደሩ እርስ በእርስ የሚለዋወጣቸው ይሆናል። እነዚህን ምርጥ ዘሮች ጥራታቸውን የማረጋገጥና ልውውጡን የተሳለጠ የማድረግ ጉዳይ ነው ዋናው ስራ የሚሆነው። በእዚህ አካባቢ የተወሰነ ጉደለት አለ። ጉድለቱን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ስለዚህ የ2005\6ዓ.ም የግብርና ውጤት በመኽር የሚመሰረት በመሆኑ የተሻለ ውጤት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። እንቅስቃሴያችንም የተጠናከረ ነው።
የግብርና ባለሙያዎችን ጥያቄ በተመለከተ ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄ ያቀረቡት አለ። በተለይ የስራ ሁኔታን የማሻሻል እና ለስራቸው ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ጉዳይ እስካሁን በየክልሉ የተለያየ አፈፃፀም ነው ያለው። ስለዚህ በክልሎች ያለውን አፈፃፀም አንድ ወጥ ለማድረግ ከክልል ኃላፊዎች ጋር በጋራ ተነጋግረናል። በዚህ መሰረት በሁሉም ክልሎች ለግብርና ባለሙያዎች የትምህርት፤የመስሪያ መሳሪያዎችና አልባሳትና የመሳሰሉ ለስራቸው ምቹ የሆኑ መኖሪያ ቤት በገጠር አካባቢ የማዘጋጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይነት እንዲኖረው ለማድረግ እየተሰራ ነው። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት አለን።
No comments:
Post a Comment