ተቃዋሚዎች፤ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በጥንቃቄ ሊያዙ ይገባል አሉ
ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች አጀንዳ አድርገው ማራገባቸው ለሃገሪቱ መፃኢ እድል ጠቃሚ አለመሆኑንና ሁለቱም ወገኖች ከዚህ ድርጊት መታቀብ እንዳለባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አሳሰቡ፡፡ በደሴ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት አባት በሆኑት በሼህ ኑሩ ይማም ላይ የተፈፀመውን ግድያ መንግሥት በቶሎ አጣርቶ ትክክለኛውን ውጤት እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡ የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ የደሴ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት አባት የነበሩት የሼህ ኑሩ ግድያን አጥብቀው እንደሚያወግዙና ገዳዮቻቸውም በፍጥነት ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
መንግሥት፤ ተቃዋሚዎች የሃይማኖት አጀንዳን እያራገቡ ነው የሚል ወቀሳ ማቅረቡን አልቀበለውም ያሉት ፕ/ር በየነ፤ የመብት ይከበር ጥያቄና የሃይማኖት ጥያቄ የተለያየ ነው ብለዋል፡፡ ጉዳዩን ያለቅጥ ማራገብና ማጦዝ በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን መግባባት ላይ ስለማያደርስ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች ጉዳዩን በጥንቃቄ ሊይዙት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ሃይማኖት የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን በማመልከት፣ ከተቃዋሚዎች ቀድሞ ወደዚህ ጉዳይ የገባው ኢህአዴግ ነው ብለዋል፡፡ “ኢህአዴግ ይህን ጨዋታ የጀመረው ምርጫ 97 ላይ ነው” የሚሉት ዶ/ር መረራ፤ መንግሥት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጁን በጉዳዩ አስገብቷል ይላሉ፡፡ “ሰሞኑን ደሴ ውስጥ በተገደሉት የሃይማኖት አባት የተነሳ ሃይማኖትን አጀንዳ አድርጐ እየተንቀሳቀሰ ያለው መንግሥት እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም” የሚሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ እኛ ሃይማኖትን አጀንዳ የማድረግ እቅድም ሃሳብም የለንም ብለዋል፡፡
የኢዴፓ ሊ/መንበር ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ደሴ ላይ የሃይማኖት አባት መገደላቸው በማንኛውም መንገድ ተገቢ አለመሆኑን አስምረው፣ መንግሥት ጉዳዩን ለህዝብ ግንኙነትና ለፕሮፓጋንዳ ከመጠቀም ይልቅ ገዳዮቻቸው ተገቢውን ፍርድ እንዲያኙ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎችም ህገ መንግሥቱን መሰረት ያደረጉ እስከሆኑ ድረስ በመንግሥት አካላት ሊወገዙ እንደማይገባ ጠቁመው እነዚህ ወገኖች መብታቸውን የሚጠይቁበትን ምቹ መድረክ መንግሥት ራሱ መፍጠር ይገባዋል ብለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment