Friday, July 12, 2013

እኛ ኢትዮጵያዉያን በአገራችን ያለዉን ችግር ለመቅረፍ በቁርጠኝነት የምንነሳበት ጊዜዉ አሁን ነዉ ባይ ነኝ። አሁንም አገራችን ኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅት ላይ ነዉ ያለችዉ። ተስፋ የቆረጥን፣ የሰላማዊዉን ትግል የተዉንና የማያዋጣ በሌሎች በመተማመን ላይ ያተኮረ የትግል መንገድ የተከተልን አለን። ብዙዎቻችን «አይቻልም» መንፈስ ተሞልተናል።
ይሄ መቀየር አለበት። በራሳችን መተማመን አለብን። ከስሜትና ከንዴት በጸዳ መልኩ የሚጠቀመዉንና የሚበጀዉን የሰለጠነዉንና በሕዝብ ጉልበት ላይ የተመሰረትዉን መንገድ መያዝ ይኖርብናል። ከበረታን፣ ከተባበርን ከግብ የማንደርስበት ምንም ምክንያት የለም።
የሰማያዊ ፓርቲ በቅርቡ በጠራዉ አንድነትና መኢአድም በደገፉት የአዲስ አበባዉ ሰላማዊ ሰልፍ፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የፍርሃትን ካባ አዉልቀዉ ድምጻቸዉን ማሰማታቸው ይታወቃል። ሰሞኑን ደግሞ የአንድነት ፓርቲ በሌሎች አንጋፋ የኢትዮጵያ ከተሞች ሕዝብን እየቀሰቀሰ ነዉ። በጎንደርና በደሴ በመኪና ላይ ጡሩምባ በመንፋት፣ ወረቀቶችን በመበተን፣ በየመንደሩ ዜጎችን ፔቲሽን በማስፈረም፣ ሕዝቡ ቀና ብሎ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲነሳ እያደፋፈሩት ነዉ። በዚህም ምክንያት የአንድነት አስተባባሪዎች በመታሰር ላይ ናቸው።ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነዉ።
ነገር ግን የጨዋታዉ ሕግ ተቀይሯል። እንደ ትላንትና ፈርቶ መመለስ ቀርቷል። «/ቤቶቻችን እስኪዘጉና ሁላችንንም አስረዉ እስኪጨርሱ ድረስ ለመብታችን መጮሃችንን አናቆምም» እያሉ ነዉ አንድነቶች።
እንግዲህ «ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን» እላለሁ። በደሴና በጎንደር የምንኖር ሁሉ በነቂስ እንዉጣ። በርቀት ያለንም እየደወልን፣ በፌስቡክና በኢሜል በጎንደርና በደሴ ያሉ ዘመዶቻችን ጓደኞቻችን እንዲወጡ እናበረታታ። በፓርቲዉ የተዘጋጀዉን ፔቲሽን በመፈረም በመንፈስ የሰልፉ ተካፋዮች እንሁን። የምናወቃቸዉን ሁሉ እናስፈረም። ለትግሉም ያለንን አጋራነት በተግባር እናሳይ።

No comments: