ህይወትህ በመንግስት እጅ ነው ያልፍልሃል ወይም ያለፋሃል
ይህች አገር የማን ነች? በየወሩ ትገብራለህ፤ ወይም በየወሩ ትደጎማለህ
ህይወት ሎተሪ ነች? በመንግስት እጣ፤ አከራይ ወይም ተከራይ ትሆናለህ
በ”ፍትህ” እና በ”ማህበራዊ ፍትህ” መካከል ያለው ልዩነት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? “ወንበር” እና “የኤሌክትሪክ ወንበር” እንደማለት ነው - አንደኛው ለህይወት የሚመች ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ህይወትን የሚያጠፋ። እስቲ ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከታክስ እስከ ኮንዶምኒየም ... ጥቂት ዞር ዞር ብለን እንመርምረው።እንደምታውቁት፤ የብዙ ዜጎች ኑሮ፤ ከቅዠት በባሰ ምስቅልቅል ተውጧል - በከተማም በገጠርም። አዲስ አበባ ወይም ድሬዳዋ፤ መቀሌ ወይም ናዝሬት፤ ባህርዳር ወይም ሃዋሳ ሊሆን ይችላል። በ400 ብር ደሞዝ፤ ራሱን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ የሚያስተዳድር የጥበቃና የፅዳት ሰራተኛ በየትኛውም ከተማ እናገኛለን - የአመት ገቢው 4800 ብር መሆኑ ነው።
መቼም ኢትዮጵያ ሁላችንም የምንኖርባት አገር ነች። ለድሃው የፅዳት ሰራተኛና ለድሃው ገበሬ፤ እኩል አገራቸው አይደለችም? አንዱ በሌላው ኪሳራ ለመጠቀም ሳይሞክር፤ እንደየዝንባሌው ለስራ የሚሰማራባት የነፃነት አገር መሆን የለባትም? አንዱ የሌላውን ምርትና ገቢ በሃይል ለመውሰድ ሳይሞክር፤ እንደየጥረቱ ውጤት ተጠቃሚ የሚሆንባት የፍትህ አገር ልናደርጋት አይገባም? የአገሪቱ መንግስትስ፤ ሁሉንም ዜጎች በህግ ፊት እኩል የሚያይና የሚያስተናግድ መሆን የለበትም? ሁሉንም የአገሪቱ ሰው፤ የከተማና የገጠር ድሆችንም ጭምር፤ በእኩል የዜግነት አይን የሚመለከት፤ የሰዎችን ነፃነትና መብት የሚያስከብር፤ በህግ የበላይነት ፍትህን የሚጠብቅ መንግስት ሊኖረን አይገባም? ታዲያ ምነው፤ ከአንዱ ድሃ ብር ይወሰድበታል፤ ለሌላው ድሃ ብር ይሰጠዋልሳ? ምነው፤ ፍትህ ተንጋደደችሳ?
እንዲህ አይነቱ ፍትህን የሚጥስ ተግባር፤ “ማህበራዊ ፍትህ”፤ “ፍትሃዊ ክፍፍል” ተብሎ መሰየሙ ደግሞ፤ ይበልጥ ህሊናን ይቆረቁራል። “ማህበራዊ”፤ በሚሉ ቅጥያ የፍትህ ትርጉም በአናቱ ተገለበጠ። ከዚያማ፤ ዝርፊያ እንደ ስጦታ ይቆጠራል። የተለመደና ሲደጋገም የኖረ ዘዴ ነው። “ፍትህ”፤ “ነፃነት”፤ “መብት”፤ “እኩልነት” እና ሌሎች ትክክለኛ ፅንሰሃሳቦችና መርሆች፤ በየጊዜው በዚሁ መንገድ ይጣሳሉ - ፅንሰሃሳቦቹንና መርሆቹን የሚያፈርስ ቅጥያ እየተጨመረባቸው።
መንግስት፤ የአንዳንዶችን የስራ ገቢ በታክስ ይወስዳል። ለአንዳንዶች ደግሞ፤ ያለ ስራ ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል - አየርባየር። ይሄው ነው፤ “ማህበራዊ ፍትህ”። መንግስት፤ “ለአገር ልማት፤ ለህዝብ ፍላጎት፤ ለድሆች ጥቅም፤ ለማህበራዊ ፍትህ” በሚሉ ሰበቦች የኢኮኖሚና የቢዝነስ ስራዎች ውስጥ ሲገባ፤ ሁሌም እንዲህ አይነት “አድልዎ” መፈጠሩ ፈፅሞ ሊቀር አይችልም። ለአንዱ ዜጋ ለመስጠት፤ ከሌላው ዜጋ መንጠቅ የግድ ነው (አንዱን ዜጋ ለመጥቀም፤ ሌላውን መጉዳት)። መንግስት፤ ኮንዶምኒየም ቤቶችን ለመስራት፤ ከተወሰኑ ዜጎች ታክስና ግብር ይወስዳል፤ ቤት የመስራትም ሆነ የመከራየት አቅም ያሳጣቸዋል ማለት ነው። የተገነባውን ኮንዶምኒየም ለጥቂት አልያም ለሌሎች ዜጎች ይሰጣል፤ የኮንዶምኒየም ባለቤት ሆነው እያከራዩ ገቢ ያገኛሉ። ይሄው ነው “ማህበራዊ ፍትህ”።የመንግስት እጅ ያልገባበት የነፃ ገበያ ስርአት ውስጥ፤ የአንድ ዜጋ ጥቅም፤ በሌላው ዜጋ ጉዳት ላይ የተመሰረተ አይደለም። በራሳቸው ጥረትና ቁጠባ ቤት የሚገነቡ ሰዎች፤ ከጥረታቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ - ቤቱን ይኖሩበታል፤ ወይም አከራይተው ገቢ ያገኙበታል። ቤቱን ለመገንባት ማንንም ሰው መጉዳት አይችሉም። ሌሎች ዜጎች በከፈሉት ታክስና ግብር አይደለም ቤቱ ተገንብቶ የተሰጣቸው - በራሳቸው ገንዘብና ወጪ እንጂ። በራሳቸው ጥረትና ወጪ አማካኝነት ቤት የሚገነቡ ዜጎች ሲበራከቱ፤ ሌላውንም ይጠቅማሉ - የቤት ኪራይ አማራጭ በማበራከት፤ የኪራይ ዋጋ እንዲቀንስ ይረዳሉ። አዲስ ሃብት እየፈጠሩ እንጂ፤ ከሌሎች ዜጎች እየነጠቁ አይደለማ። ስለዚህ፤ በነፃ ገበያ ውስጥ፤ የበርካታ ዜጎች ቢዝነስ ሲያድግ፤ ግንባታቸው ሲበራከትና ህይወታቸው ሲሻሻል፤ ድርብ ጥቅም እናገኛለን። አንደኛ ነገር፤ የስራ እድልና የምርት አቅርቦት እንዲጨምር እያደረጉ ስለሆነ፤ ህይወታችንን የምናሻሽልበት ተጨማሪ እድል እየፈጠሩልን ነው። ሁለተኛ ነገር፤ በራስ ጥረት መበልፀግና ህይወትን ማሻሻል እንደሚቻል በተግባር እያሳዩን ስለሆነ፤ በአርአያነት መንፈሳችንን ያነቃቁልናል።
መንግስት የአገሪቱ ኢኮኖሚና ቢዝነስ ውስጥ ጣልቃ ሲገባ፤ እናም “በመንግስት ቸርነትና ድጎማ” አማካኝነት የተወሰኑ ሰዎች “ህይወታቸው ሲሻሻል” ግን፤ “በአንዱ ዜጋ ኪሳራ ሌላው ዜጋ መጠቀሙ”፤ ቅሬታንና ሽሚያን ያስከትላል እንጂ፤ የስራ እድልንና የመንፈስ ብርታትን አይፈጠርም።
No comments:
Post a Comment