Tuesday, July 9, 2013

የጠፋው ትውልድ

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ከትውልድ ጋራ አያይዘው ለመረዳትና ለመፍታት የሚሞክሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ። እርግጥ አንድ ትውልድ የአገርን ችግሮች በተለያዩ ምክንያቶችና የታሪክ አጋጣሚዎች ሊፈታ ወይም ሊያባብስ ይችላል። ሆኖም የኢትዮጵያን ችግሮችም ይሁን መፍትሔዎች በአንድ ትውልድ ሥራዎች ውስጥ መፈለግ/መጠበቅ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ሊያደርስ ይችላል። በተጨማሪም ሐሳብን ለማደራጀት በትውልድ ቀመር እንነጋገራለን እንጂ ማንኛውም ማኅበረሰብ ሕይወትን የሚመራው በተለያዩ ትውልዶች ተሳትፎ ነው። በአንድ ትውልድ አባላት ብቻ የሚመራና የሚኖር የሕይወት አካል የለም።
የአገራችንን ፖለቲካ በትውልድ ለመረዳት ሲሞከር የውይይቱ ማዕከል የሚሆነው ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” ያለው የአብዮቱ አንቀሳቃሽ ትውልድ ነው። የ “ያ ትውልድ” ብዙዎቹ አባላት አሁን ዕድሜያቸው በአማካይ ከ50-75 ነው። “ያ ትውልድ” ከ1960ዎቹ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ፖለቲካውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል። በእርግጥ ለአንድ ትውልድ 40 ዓመት ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊ ሆኖ መቆየት እጅግ ብዙ ሊባል የሚችል አይደለም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትውልድ አከፋፈል ላይ የተሠራ ጥናት አለነበብኩም፤ ባገኝ እጅግ እወድ ነበር። ለዚህ ጽሑፍ ያህል “ያ ትውልድ”ን መነሻ አደርጌ ሦስት ዘመኖችን አስቀምጫለሁ። ይህን ሳደርግ ግን ወደ ፖለቲካ ትውልድ አከፋፈል ዝርዝር ሐልዮቶች (ቲዎሪዎች) መግባቱ አስፈላጊ አልመሰለኝም። የትውልዱን መለያ “ስም”፣ የትውልዱን አማካይ የትውልድ ዘመን (ልደት)፣ ፍላጎቱ ገኖ የወጣበትን የፖለቲካ ዘመኑን (ፖለቲካ)፣ እንዲሁም የትውልዱ አባላት አሁን የደረሱበትን ዕድሜ (ዕድሜ)በቅደም ተከተል አስቀምጫጨዋለሁ።
  1. “ያ ትውልድ”፤ ልደት 1925-1950፤ ፖለቲካ 1960-1997፤ ዕድሜ 53-78
  2. “የጠፋው ትውልድ”፤ ልደት 1951-80፤ ፖለቲካ 1995- ፤ ዕድሜ 23-52
  3. “አዲሱ ትውልድ”፤ ልደት 1981-1990፤  ፖለቲካ፣ አልደረሰም፤ ዕድሜ 20-
ዛሬ ላነሳ የፈለኩት (ነገር ፍለጋ በሚመስል መልኩ) “የጠፋው ትውልድ” ስላልኩት የራሴ ትውልድ ነው። ይህ ትውልድ በመሠረቱ ስለ አገርም ይሁን ስለ ፖለቲካ ያለው አመለካከት በቅድሚያ የተቃኘው “እናት አገር” ወይም “ኢትዮጵያ” በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ ነው። የ“እናት አገር”  ገናና ታሪክ፣ ሉአላዊነት እና አንድነት የፖለቲካው እንብርት ነበር። ስለ እናት አገር ለተከታዩ “አዲሱ ትውልድ” የሚተርፍ አክብሮትና ፍቅር ያደረበትም ለዚህ ነው። የአክብሮቱና የፍቅሩ መገለጫ ሁሉ “ትክክል” መሆኑን ግን እጠራጠራለሁ። አብዛኛው በተለይም ከተማ ቀመሱ በ”እናት አገር” ርዕዮተ ዓለማዊና ባህላዊ መሠረት ቢቀረጽም፣ በሒደት “በብሔረሰብ መብት” አስተምህሮ መማረክ የጀመሩ ቁጥራቸው የማይናቅ የትውልዱ አባላት አሉ።
የዘመኑ ፖለቲካ ለ“ለጠፋው ትውልድ” ስለ ነጻነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት ወዘተ ይህ ነው የሚባል ሐልዮታዊም ሆነ ተግባራዊ ቁም ነገር የሚያስጨብጠው አልነበረም። በተቀራዊው የፖለቲካን አስከፊ ገጽታ “እያደነቀ” ለማደግና ለመኖር የተገደደ ነበር። በማንኛውም መመዘኛ ነጻነቱን እና መብቱን የተነጠቀ፣ ተስፋውን በቅርብ የማይመለከት፣ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ በተግባር የኖረ ነው። በመሠረታዊ ተፈጥሯቸው ጨቋኝ የሆኑት ብዙዎቹ የፖለቲካ ቡድኖች (ደርግ፣ ህወሓት፣ ኦነግ፣ ሻእቢያ…) ለደም ግብር የጠሩትም እርሱኑ ነው። “ወይ በባሌ ወይ በቦሌ” ያለውም ይኸው የእኔ ትውልድ ነው።
በዘመነ ደርግ ትውልዱ ስለ ነጻነትና ስለዴሞክራሲ ከመስማትና ግፋ ቢል ከማሰብ ያለፈ ዕድል አልነበረውም። እርሱም ቀርቶበት ሁሉንም የሕይወቱን ገጽታዎች ለመቆጣጠር የሚደረገው ትግል ስርአቱ በማንም እንዲተካለት ከመመኘት አድርሶታል። ህወሓት/ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ጠንካራና የተደራጀ ሕዝባዊ ተቃውሞ ያልገጠመውም በዋናነት በዚህ ምክንያት ነው። ምናልባት ይህ የሆነው የትውልዱ አባላት በአብዛኛው ህወሓት/ኢሕአዴግን “እንደ ነጻ አውጪ ተቀብሎት” የሚመስለው ካለ ተሳስቷል። ሲጀመር ህወሓት/ኢሕአዴግ “የእናት አገር” አስተምህሮ ለመናድ እንደሚሰራ ሲናገር የቆየ ነው፤ በተጨማሪም አብዛኛው ሕዝብ ስለ “ነጻ አውጪዎቹ” ያለው መረጃ የወቅቱ መንግሥት የሚሰጠው ብቻ ነበር። ይህን ሐሳብ ያነሳሁት “የጠፋው ትውልድ” ለወሰደው አንድ መሠረታዊ ምርጫ መነሻ ምክንያት ስለሆነ ነው። ይህም ብዙ የትውልድ አቻዎቼ ለኢሕአዴግ እና በአጠቃላይም ለብሔር ፖለቲካ አራማጆች ዕድል መስጠት፣ ማዳመጥ እና ለመረዳት መሞከር እንደሚገባ ማመኑ ይመስለኛል። ከብዙ መሰሎቼ ጋራ የአገራችንን ታሪክ በብሔር መብት ጥያቄዎች አንጻር እንደገና የመገምገም፣ አዳዲስ እይታዎችን የማስተናገድ፣ የብሔር ጥያቄን በተለያየ ጥልቀትና አቅጣጫም ቢሆን የማሰላሰል (appreciate) ፖለቲካው ፈቃደኝነትም ድፍረትም አላጣንም። ቢያንስ በግሌ የብሔር ጥያቄን ከሚያነሱ ጋር እንደ ጥያቄው የምጋራቸው ብዙ ነገሮች አግኝቻለሁ፤ በአጀንዳው አቀራረጽና አቀራረብ፣ እንዲሁም በመፍትሔው ላይ ግን ልዩነቶች አሉኝ። ይህ ተሞክሮ ትውልዴን ይወክላል ብዬ መናገር ግን አልችልም። ዛሬ በብሔረሰብ በተደራቹ የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ/እናት አገር ቀና አመለካከት ያለቸው ሰዎች በአብዛኛው የዚህ ትውልድ አባላት ሆነው ቢገኙ አይገርምም። በተቃራኒውም የብሔረሰብ መብት ጥያቄ በታሪካዊዋ ኢትዮጵያ ማእቀፍ ውስጥ ሊስተናገድ የሚችል ነው የሚሉም እንዲሁ።
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ

ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: