Thursday, July 4, 2013

የወያኔ የስህተት ጉዞና የተቃዋሚው ያለመስማማት ጉዞ


የወያኔ የስህተት ጉዞና የተቃዋሚው ያለመስማማት ጉዞ
   ወያኔ ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከዚች ሰዓድረስ ከሰራቸው መልካም ስራ ይልቅ ያጠፋው ጥፋቶች በይበልጥ ጎልተው ይታያሉ፡፡ የሀገሪቱን ህገመንግስት በመጣስም ቢሆን ኢህአዴግ ከሚከሳቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች በበለጠ ደረጃ ራሱ ሲጥስ ይስተዋላል፡፡ ኢህአዴግ ከግልጽነቱ ይልቅ ግልጽነት የጎደለው አሰራሩ ይበልጣል፡፡ ለዚህም አቶ በረከት ስምኦን ስለድርጅቱ ግልጽ አለመሆን በራሳቸው አንደበት ከቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ
ሚንስትር መታመም ጋር ተያይዞ ለህዝብ አለመነገሩ ከድርጅቱ ግልጽነት ማጣት እንደሆነ እንደመልካም ነገር አስረድተዋል፡፡
     ወያኔ ከቀድሞው የኢትዮጵያ // ሞት ጋር በተያያዘ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ለማዳመጥ እንደቻልነው አብዘኛው የተጀመሩትንና የተሰሩትን ሁሉ እርሳቸው መሆናቸውን ሲናገሩ እንደነበረ ሰምተናል፡፡ ይህንን ሪፖርት ላዳመጠ ሰው ካድሬዎች ሁሉ ምንም ሥራ የመስራት፣ የማቀድና የማስወሰን አቅም እንደሌላቸው እና ላለፉት 22 ዓመታት ሙሉ ምንም ስራ እንዳልሰሩ በራሳቸው አንደበት መስክረዋል፡፡ በዚህም እስካሁን ድረስ የቀድሞው // በነበሩ ጊዜ ሁሉ ካድሬዎቹ ሳይሰሩ ደመወዝ ይከፈላቸው ስለነበረ ያለአግባብ ይበሉ የነበረውን ደመወዝ ቢመልሱ መልካም ነበር፡፡
       ለነገሩ እነርሱ የቱንም ያህል ራሳቸውን አሳንሰው ቢገልጹ ያቀዱትን ዓላማ ከማሳካት አንጻር ግባቸውን መተዋል፡፡ በወቅቱ እነርሱ ህዝቡንና ተቃዋሚውን በማዘናጋት የኢህአዴግን ህልውና ማስቀጠል ዋና ዓላማቸው ስለነበረ በዚህ መልኩ ህዝቡን በማዘናጋቱ ረገድ ትልቅ እመርታ ኣሳይተዋል፡፡ ምንም እንኳ እኛ ተቃዋሚዎች ቀድሞውንም እነርሱ ሳይደክሙ የተዘናጋን ቢሆንም ቅሉ፤ በዚህ መልኩ እያንዳንዱ ካድሬ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ድርጀቱን አሁን ባለው መልኩ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ ድርጅቱ ባለበት ከቀጠለ ደግሞ ካድሬዎቹ ያለጠያቂ መቀጠል ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ህገመንግስቱ //ሩን በተመለከተ ምንም እንዳይል በማድረግ ስህተት የተፈጸመ ቢመስልም ዋናው ዓላማ ግን የኢህአዴግን የበላይነት ከማስጠበቅ አንጻር ትልቅ ስራ ሰርቷል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በተቃዋሚው በኩል የሚሰሩ ስህተቶች ተቃዋሚውን ከመጥቀም አንጻር ሳይሆን እርስ በርስ ከመጠፋፋት አንጻር እየሰሩ ስለነበረና አሁንም እየሰሩ ስለሆነ ለኢህአዴግ ሰፊ የመጫወቻ ሜዳ ያለተቃናቃኝ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ይህ የተቃዋሚዎች የተሳሳተ አካሄድ ለኢህአዴግ ረጅም ዓመታት ያለተቀናቃኛኝ እንዲገዛ ከማድረጉ በተጨማሪ ወደፊትም በዚህ መልኩ ረዘም ላለ ዓመታት እንደማይገዛ ምንም ዋስትና የለም፡፡
      ሌላው የወያኔ ስህተት ከነበረው ውስጥ አንዱ ከህግ ውጭ የጠቅላይ ሚንስትሩን አስከሬን ሳይቀብር ለሁለት ሳምንት ያህል ማስቀመጡ ሲሆን በዚህ ስህተቱ ወያኔ ብዙ ፕሮፓጋንዳ ሰርቶበታል፡፡ በርካታ ሰዎች ከእርሳቸው በቀር ሌላ ሰው እንዳልነበረ እንዲረዳ አድርጎ የምርጫ ቅስቀሳ አድርጎበታል፡፡ በጠባቧ የቴሌቪዥን ስክሪን ጥቂት ደጋፊና ካድሬዎችን ምስል በማሳየት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳዘነ በማስመሰል የፕሮፓጋንዳ ትርፍ ለማግኘት ሞክሯል፡፡ ዓለም አቀፍ ህብረተሰብንና አንዳንድ ተቃዋሚዎችን ሳይቀር አሳስቶበታል፡፡ ስህተትን ለትርፍ ይጠቀሙበታል ማለት ይህ ነው፡፡ ወያኔ በዚህ ስራው ትልቅ ትርፍ አትርፎበታል ማለት ይቻላል፡፡ የሀገሬው ህዝብ ተቃዋሚዎችን እንዲታዘብ ሲያደርግ ኃያላኑ ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሌለ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል፡፡
     በተቃዋሚው ጎራ ያሉት በአሁኑ ሰዓት ከመሰባሰብ ይልቅ አዳዲስ ፓርቲዎች እንደአሸን መፍላቱን ተያይዘውታል፡፡ ይህ የፓርቲዎች በየቀኑ እንደአሸን መፍላት አምባገነናዊ ስርዐቱ በሰፈነባት ሀገራችን ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ በሆኑት ሀገራት የኮበለሉት ሳይቀር የተጠናወታቸው በሽታ ነው፡፡ የተቃዋሚው ጎራ በራሱ የተከፋፈለ ሀሳብ ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡ ገሚሱ ያለውን መንግስት በመደገፍና ለአምባገነናዊ አገዛዙ ድጋፍ በመስጠት ተቃዋሚ የሚለውን ዓርማ በመሸከም ብቻ የህዝቡን መከራና ሰቆቃ ሲያባብሰው ይታያል፡፡ ገሚሱ ደግሞ በትክክል ይቃወማል፤ እርስ በርሱም ይቀዋወማል፡፡ በዚህም እርስ በርሱ ሲቀዋወም አንድ ዓላማና ግብ ቢኖውም አንዱ አንዱን የሚያጠፋ ስራ እየሰራ በተቃራኒው ገዢው መንግስት እንዳሻው እንዲሆን በማድረግ የህዝቡን የመከራ ጊዜ ያራዝማል፡፡
      ጉንዳኖች ትንንሽ ነፍሳቶች ናቸው፡፡ ትልቁን ወንዝ ግን ተያይዘው ይሻገሩታል፡፡ ጉንዳኖች ወንዝ ሲሻገሩ አንዱ ጉንዳን አንዱን ጉንዳን ነክሶ በመያዝ እየተቀጣጠሉ ወንዙን መሻገር ይጀምሩና የመጀመሪያው ጉንዳን ወንዙን መሻገሩን ሲያውቅ ከወንዝ ወዲያ ማዶ ያለውን አፈር ወይም ቅጠል ነክሶ በመያዝ
የልተሻገረውም እንዲሁ ይነክስና ድልድይ ይሰራሉ፡፡ ሌሎች ጉንዳኖች ከስር በተዘረጋው የጉንዳኖች ድልድይ በሰላም ይሻገራሉ፡፡ ድልድይ የሆኑት ጉንዳኖች ወንድሞቻቸው ከተሸገሩ በኋላ መሻገር ይጀምራሉ፡፡ ሁሉም ግን ወንዙን አይሻገሩም፡፡ ከተቃዋሚው ጎራ ድልድይ የሚሆን ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉም መሻገር ይፈልጋል፡፡ አንዱ አንዱን አይዝም፡፡ ብቻ መሻገር ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ አንዱ አንዱን ይዞ ተያይዞ መሻገር ሳይሆን እያንዳንዱ በራሱ ብቻውን መሻገር ስለሚፈልግ እንዲሁ ባሉበት ይቀራሉ፡፡ አንዳንዶችም በጎርፍና በውሃው ሙላት ይወሰዳሉ፡፡
      የሀገራችን የተቃዋሚዎች ያለመስማማት በሽታ እንደወረርሽኝ ከሀገር ቤት አልፎ በተሰደዱበት ሀገር ሁሉ መዝመቱ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ታዋሚዎች ባለመስማማታቸው ይህን ሁሉ ዓመት ኪሳራ እንጂ ትርፍ ባያስገኝላቸውም ለትርፍ ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ በኪሳራ መንቀሳቀሱን ተያይዘውታል፡፡ አንዳንዶቹ በእርግጥ ምን እንደሚቃወሙም ማወቁ ይከብዳል፡፡ እዚህ ሀገር ቤት ገዢው ፓርቲ የሚሰራውን በዘር የመከፋፈል ዘዴ እነርሱ በስደት ሀገር ሆነው ሲያራምዱት ይታያል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ በእርግጥ ከገዥው ፓርቲ ስውር ካድሬዎች ተልዕኮ አይሆንም ብሎ መጠራጠር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እርስ በርስ በዘር መከፋፈላችን ለአንድነታችን ገደል ነውና በዘር ተከፋፍለን የምንታገል ከሆነ እንዴት አንዱ አንዱን አምኖ አጠገቡ ሊቆም ይችላል፡፡ ስለዚህ ምናልባት ይህ ዓይነቱ አካሄድ ለተጨማሪ አመታት በአምባገነኖች ከመጋት ዉጪ ጥቅም የለውም፡፡ ከአለመስማማት ወደ አለመስማማት በሄድን ቁጥር ተጠቃሚው ወያኔና ወያኔ ብቻ ይሆናል ባይ ነኝ፡፡
     ለዚህ መፍትሄው ተቃዋሚዎች እንደጉንዳን ከውጭም ከውስጥም ያለነው እርስ በርስ መያያዝ እና ገዳም እንደሚደረገው ጎበዝ በጉልበቱ ሽማግሌና ደከማ በጸሎቱ እንደሚባለው በውጪ ያለነው ዲያስፖራ በገንዘቡና በሀሳቡ በውጪው ዓለም ኃያላኑ በአምባገነኑ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳር በማድረግ መተጋገዝ ሲሆን ሀገር ቤት ያለው በቀጥታ አቋምን በማስተካከል ህዝቡን በማደራጀት ወደፊት በመሄድ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ከግብጾች ብዙ ልንማር ይገባል አለበለዚያ እንደዚህ ዓይነት መንግስት የቅብርጥሶ ፓርቲ ብሎ በሀገር ቤትውም ሆነ በውጪ ያለው መሰረት የሌለው ፓርቲ ይዞ መሄዱ ለልጆች መጫወቻነት ከሚክቡት የእንቧይ ካብ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡
    ሽንገላና የአፍ ወለምታን መከተል እስካልቆሙ ድረስ ውጤት ስለማይመጣ ዝም ብሎ መቀመጡ የተሸለ ነው፡፡


ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: