Saturday, July 6, 2013

‹‹የምንሞትለት እንጂ የምንገድልበት አላማ የለንም››

‹‹የምንሞትለት እንጂ የምንገድልበት አላማ የለንም››


በደሴ ከተማ በአረብ ገንዳ መስጊድና በደቡብ ወሎ እንዲሁም በአማራ ክልል ደረጃ መንግስታዊውን እስልምና (አሕባሽ) ከፊት በማጀብ እና በደሴ ለበርካታ ሙስሊሞች ፊትና ሆነው የቆዩት ሼኽ ኑሩ የተባሉ ግለሰብ ሐሙስ ምሽት ጥቃት ተፈጽሞባቸው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ግለሰቡ ከመግሪብ ሰላት በኋላ ማንነቱ ባልታወቀ አካል ነው በጥይታ ጥቃት የተፈጸመባቸው፡፡ ድምጻችን ይሰማ የግለሰቡ ሕይወት ማለፉን ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን በትናንትናው እለትም የቀብር ስነ ስርአታቸው በዚያው በደሴ ከተማ ተፈጽሟል፡፡ 

ከግለሰቡ ግድያ ጋር በተያያዘ መንግስት በርካታ ሰዎችን ማሰር የጀመረ ሲሆን በዚሁ ሰበብም የደሴን ሙስሊም ለተጨማሪ ችግር ለመዳረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ከመንግስት አካሄድ መረዳት እንደተቻለውም ይህንን ወንጀል በደሴ ሙስሊም ላይ በማሳበብ በዚህም የሃይማኖት አክራሪነት እያለ ደጋግሞ ለሚናገረው አጀንዳ ግብአት ለማድረግ ማሰቡን ነው፡፡ ሆኖም ሙስሊሙ ህብረተሰብም ሆነ የደሴ ሙስሊም በዚህ አይነቱ የመንግስት አካሄድ ሊታለል የማይችል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡በዚህ አይነት ርካሽ ወንጀል ላይ ሰላማዊውን ሙስሊም ህብረተሰብ ተጠያቂ ለማድረግ ማሰብ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ሼኽ ኑሩ ምንም እንኳ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለሕገ መንግስታዊው የሃይማኖቱ ነጻነት መከበር የሚያደርገውን ትግል በሌላ አቅጣጫ በመሆን በማወክና ከመንግስት ጎን ቆመው ሙስሊሙን ህብረተሰብ ሲወጉ የቆዩ ሰው ቢሆኑም፣ እንዲሁም የደሴ ሙስሊም ከአመት በላይ ለቆየበት አሰቃቂ ሁኔታ እና ፊትና ተጠያቂ ሆነው ሊቀርቡ ከሚችሉ ግለሰቦች ሼኽ ኑሩ አንዱ ቢሆኑም የትግላችን መርህ ሰላማዊ ብቻ በመሆኑ ወደ ሀይል ድርጊት ገብቶ ግለሰቡን ችግር ላይ ሊጥል የሚችል የህብረተሰባችን ክፍል የለም፡፡ በእስከአሁኑ ሂደታችንም አልተከሰተም፡፡ የትግላችን መሰረታዊ ባህሪ የሆነው ‹‹የምንሞትለት እንጂ የምንገድልበት አላማ የለንም›› ዛሬም መሰረቱን ይዞ በመጓዝ ላይ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን፡፡

ሆኖም መንግስት ሼኽ ኑሩን የሃይማኖት አክራሪነትን ሲዋጉ የኖሩ ግለሰብ ብሎ በመግለጽ እና ‹‹በአክራዎች ተገድለዋል›› የሚል ሀሳብ በማንጸባረቅ እየሄደበት ያለው መንገድ አሳፋሪና ሙስሊሙ ላይ በደሉን አጠናክሮ ለመቀጠል መንገድ እየጠረገ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ከግለሰቡ ግድያ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎች ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የቆየ ሲሆን መንግስት ተመሳሳይ ሰዎች ላይ አደጋ በመጣል ሙስሊሙን ተጠያቂ ለማድረግና ለሚፈጽማቸው ሕገ ወጥ ተግባራት ሕጋዊ ምክንያት ማግኛ መንገድ አድርጎ ሊጠቀምበት እንደሚችል ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ 

ከዚህ ቀድም ለተመሳሳይ አላማ የአንዋር መስጂድ ኢማምን ለመግደል መንግስት አሲሮ ከድርጊቱ በፊት መረጃው በመገኘቱ የመንግስት ሴራ ሊከሽፍ መቻሉ የሚታወስ ሲሆን ከፍተኛ የመጅሊሱ ባለስልጣናትም ላይ ተመሳሳይ ወንጀል ለመፈጸም እቅድ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ከሟች ሼኽ ኑሩ ጋር በተያያዘም የመንግስት ሚና የለም ብሎ መናገር የሚቻልበት ሁኔታ የሌለ ሲሆን መጪውን ረመዳን በሰላምና በእርቅ ለማሳለፍ እየተዘጋጀ ያለውን ሙስሊም ለማወክ የተሸረበ ሴራ መሆኑን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ የሼኽ ኑሩ አስከሬን ምንም አይነት የአስክሬን ምርመራ ሳይደረግለት በአፋጣኝ ስርአተ ቀብሩ እንዲፈጸም መደረጉም ጥያቄያችንን ተገቢ ያደርገዋል፡፡ በግለሰቡ ላይ የተወሰደው ድርጊት መጣራትና መንግስትም ራሱን ተጠያቂ ለማድረግ ሊዘጋጅ እንደሚገባም ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ 

No comments: