ነካ ነካ ፖለቲካ(የጠፋው ትውልድ)
የጠፋው ትውልድ በዘመነ ደርግ ፖለቲካ የሚጠቀስ ተሳትፎ አልነበረውም። “ተሰብሰብ” ሲባል ይሰበሰባል፤ “ንቃ” ሲባል ይነቃል፤ “ዝመት” ሲባል ይዘምታል አለዚያም ታፍሶ ይዘምታል፤ “ጫካ ግባ” ሲባል ይገባል አለዚያም ተገዶ ይወርዳል…። ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የዚህ ትውልድ ፖለቲካዊ ፍላጎት እና እምቅ አቅም ምን ሊሆን እንደሚችል የገመተ አይመስለኝም። “የብሔር ፖለቲካ” ጨዋታው ለሁሉም የፖለቲካ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሆን ሳያምኑም አልቀሩም። እነርሱ “ዴሞክራሲ” ሲሉና እኛ (የእኔ ትውልድ) ዴሞክራሲ ስንል ፈጽሞ ስለተለያዩ ነገሮች እናስብ እንደነበር የገባን ግን እየቆየ ሆነ፤ ለሁለታችንም። ለዚህም ነው ኢሕአዴግ እና ሌሎቹም ብሔር ተኮር ድርጅቶች በብሔረሰብ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ የሚያምኑ የትውልዱን አባላት እንኳን ማርካት ያልቻሉት። ምክንያቱም እነርሱ “የብሔረሰብ መብት” ሲሉ የምራቸውን ለዴሞክራሲ ይጠቅማል ብለው ነው፤ ኢሕአዴግና መሰሎቹ ደግሞ ገና እዚያ ገጽ ላይ አልደረሱም። በኢሕአዴግ የብሔር ፖለቲካ በመሳተፍ የመጀመሪያ ቅሬታ የደረሰባቸውም እነዚሁ የትውልዴ አባለት ነበሩ።
በሌላ በኩል የተቃውሞ ፖለቲካውን ጎራ የተቀላቀሉም የመረረ እውነታ ገጣሟቸዋል። እነዚህ ወገኖች በአንድ በኩል የኢሕአዴግ ዴሞክራሲ እነርሱ ከሚሉት የተለየ መሆኑን ቢያውቁም የአፈናው አይነትና መጠን ግን ከሚያስቡት ፈጽሞ የተለየ ሆኖባቸዋል። አንዳንዶቹም “ደርግ ሌላ ምን አደረገ?” ሲሉ መደመም ጀምረዋል። በሌላ በኩል በየፓርቲያቸው ውስጥ ያለው ድርጅታዊ ሕይወትም ቢሆን ሌላ የትግል ሜዳ ሆኖ ጠብቃቸዋል። ፖለቲካን እንዲሸሽ፣ ከቀረበም በጥንቸል ንቃት እንዲንቀሳቀስ በሚያሳምን ድባብ ውስጥ ያደገው ይህ ትውልድ የዘመነ ኢሕአዴግን ፖለቲካ ለመሸሽ ብዙ ጊዜም ማስጃም አያስፈልገውም ነበር። እንደለመደውም የፖለቲካ ጫማውን አውልቆ በቅርብ ተመልካችነት ተሰለፈ። ትኩረቱንም ወደ ሌሎች ዘርፎች አደረገ፤ ትምህርት፣ ንግድ፣ ቤተሰብ፣ ሃይማኖት፣ ስደት…። በዚህ ወቅት በፖለቲካዊ አቋሙ በማመናቸው ብቻ ኢሕአዴግን የተቀላቀሉ የዚህ ትውልድ አባላት እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው።
“የጠፋው ትውልድ” በወሳኝ የሕይወቱ ጊዜ ከፖለቲካው መጽሐፍ ከመጥፋት የተረፈው በመርጫ 97
ዋዜማ
ሆነ።
ቀደም
ሲል
እንዳልኩት የአንድ ትውልድ አባላት ሚና የጎላ እንጂ ብቸኛ ሊሆን የሚችልበት ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ ሊኖር አይችልም። በዚሁ እይታ ምርጫ 97ን ከሞላ ጎደል የዚህ ትውልድ አዲስ “አብዮት” አድርጎ መውሰድ ስሕተት አይመስለኝም። ይህ ማለት ከ“ያ ትውልድ”ም ይሁን ከ“አዲሱ ትውልድ” ለዚህ አዲስ የፖለቲካ ጅማሮ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ አልነበሩም ማለት አይደለም። የምርጫ 97ን ወሳኝ መልእክቶች እና ሥራዎች በመሠረቱ የቀረጹት የዚህ “የጠፋው ትውልድ” ፖለቲካዊ ፍላጎቶች እና ምኞቶች ናቸው። የ“አዲሱ ትውልድ” የመጀመሪያ አባላትም ቢሆኑ የዚሁ መንፈስ ተቋዳሾች ሆነዋል። ይህን መልእክት በሚገባ ማንጸባረቅ የቻሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ጎልተው ወጥተዋል።
ምናልባት ይህ ታሪክ ሲነሳ ብዙ ጊዜ ቀድሞ የሚታወሰው “ቅንጅት” ነው። ሆኖም በብሔረሰብ ቢደራጁም “ጥያቄው በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ በመቀራረብ መፈታት ይችላል” የሚሉት ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘታቸው መረሳት የለበትም። ይህ ደግሞ በመሠረቱ ብዙዎች “ቅንጅት”ን ለመደገፍ ያበቃቸው ምክንያት ሌላ ገጽታ እንጂ ፍጹም ተቃራኒ አይደለም። ቅንጅት ውስጥም ይሁን ከደጋፊዎቹ መካከል “የብሔረሰብን ጥያቄ” የማይቀበሉ ወይም እውቅና የማይሰጡ ሰዎች ይኖራሉ፤ አብዛኛው የዚህ ትውልድ አባል ግን የኢትዮጵያን አንድነትና የብሔር ጥያቄን ፈጽሞ የማይታረቁ ጉዳዮች አድርጎ አይመለከትም። በዚህ መነሻነት የሚቀርቡት መፍትሄዎች ሊለያዩ ይችላሉ፤ ቁም ነገሩ ግን ብዙው ሰው አጀንዳዎቹን የተረዳበት መንገድ ነው። በመፍትሔ አማራጮች ላይ መለያየቱ የዴሞክራሲን አስፈላጊነትና ተቀባይነት ማግኘት የሚያሳይ ይሆናል። “ቅንጅት”ን የብሔረሰቦችን ጥያቄ እውቅና የማይሰጥ አድርገው የሚያቀርቡት ኢህአዴግን የመሰሉ ጠባብ ድርጅቶች እና አንዳንድ የራሱ የቅንጅት ጭፍን አባላት ብቻ ይመስሉኛል። ከዚያ ውጭ በሕዝቡ ውስጥ የነበረው “የቅንጅት መንፈስ” የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የነጻነት፣ የመቻቻል እና የመተማመን እንጂ የመጠራጠር፣ የጥላቻና የመናናቅ አልነበረም። እንዲዚያ ባይሆን ኖሮ የራሱ የህወሓት/ኦህዴድ/ብአዴን… አባላት ሳይቀሩ ለ“ቅንጅት” ድምጻቸውን ባለሰጡ ነበር።
ይህንን እውነታ “የጠፋው ትውልድ” ከደረሰበት ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረሰባዊ ደረጃ አንጻርም ማየት ወደ ተመሳሳይ መደምደሚያ ሊያደርሰን ይችላል። የትውልዱ አባላት በትምህርትና በእውቀት፣ በሥራ/ገቢ እና በማኅበራዊ ኑሮ ወሳኝ የሚባል ተሰሚነት ለመፍጠር ጊዜ አግኝተዋል። ይህ ተጽእኖ በወላጆቻቸውም ሆነ በልጆቻቸው/ታናናሾቻቸው ላይ መንጸባረቁ የማይቀር ነው። የትውልዱ ፖለቲካው ምልከታ በቀኝም ይሁን በግራ የተሰለፉትን የፖለቲካ ጎራዎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማስተናገድ የሚሞክር በመሆኑ በቀላሉ ለማጣጣል የሚመች አልነበረም። አሁን አሁን ሳየው ግን በቅንጅት ውስጥ ሳይቀር ይህ መንፈስ ዘልቆ ያልገባቸው “ትልልቅ”ም “ትንንሽ”ም ሰዎች ነበሩ። የ“ቅንጅት መንፈስ” ግን የዚህ ትውልድ አንድ ሁነኛ የፖለቲካ ፍላጎት ነጸብራቅ ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል እገምታለሁ፤ ግምት ነው።
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ
ኢትዮጵያ
በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment