በወረቀት ላይ ተፅፎ የቀረ የኢህአዴግ የፕሬስ ህገ
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ የፕሬስ ነፃነት በአዋጅ 34/85 አረጋግጫለሁ በማለት ካስነገረ በኋላ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(3) ሀ እና ለ ላይ “የፕሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት ተረጋግጧል፡፡ የፕሬስ ነፃነት በተለይ የሚከተሉትን መብቶች ያጠቃልላል፤
ሀ. የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣
ለ. የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን ያካተተ” በሚል በግልፅ ተቀምጧል፡፡
በዚህም ምክንያት ዜጐች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚያገኙትን ሰብዓዊ መብት “ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብት” እና ዴሞክራሲያዊ የሆነውም ደግሞ የሚገለፁ ሐሳቦች የኪነ ጥበብ መንገድን ጨምሮ በማንኛውም መንገድ መግለፅ እንደሚችሉም በማከል፡፡ በተለይ በመገናኛ ብዙኃን የሚንሸራሸሩ ሐሳቦች በማንኛውም መልኩ የቅድመ ምርመራ( ሳንሱር ) ሥራ መከልከሉና ዜጐች መረጃ የማግኘት ዕድል መከበርም ጭምር እንዲሁ፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ከላይ የተጠቀሱት መብቶች በትንሹም ቢሆን የሰሩት እስከ ምርጫ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ድረስ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የነበሩ ነፃ ጋዜጦች (ፕሬሶች) የኢህአዴግን ብልሹ አሰራር በማጋለጥ፤ በነበረው ምርጫ ላይ ትልቅ ሚና በመጫወታቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡
እስከ ምርጫ 1997 ዓ.ም. መገናኛ ብዙኃን (የነፃው ፕሬስ) ቁጥር ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝና በቂ ባይሆኑም ብዙ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በመጨረሻም በበቀል ስሜት በተለይ የግሉ ፕሬስ መካነ መቃብር ተበጀለት፡፡ ጋዜጠኞችም ግማሾቹ ሲታሰሩ ቀሪዎቹ የስደት ሰለባ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡
በህገመንግስቱ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 4 “መገናኛ ብዙኃን ነፃ ስለመሆናቸው”በሚለው ስር ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ “የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት በህገ መንግስቱ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ ቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው፡፡” ይላል፡፡ ይህ ማለት ማንኛውም ግለሰብም ይሁን ተቋም ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንደማይችል በግልፅ ያረጋግጣል፡፡ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ቢሆንም፡፡
ሌላው የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን በሚመለከት በአዋጅ 590/2000 አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ “በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ላይ ገደቦች የሚጣሉት ህገ መንግስቱን መሠረት በማድረግ በሚወጡ ህጎች ብቻ ይሆናል”ይላል፡፡ ይህ ማለት ማንኛውም ህግ ሲወጣ ህገ መንግስቱን መሠረት ማድረግ መሆን እንዳለበት በግልፅ ያመለክታል፡፡
ነገር ግን በቅርቡ የመንግስት መስሪያ ቤት የሆነውና “ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት” አይመለከተኝም በሚል እሳቤ በተለይ የመገናኛ ብዙኃን (የፕሬስ) ነፃነት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29(3) ላይ የተቀመጠውን “የህትመት ሥራ ስታንደርድ ውል” በሚል አዲስ ህገ መንግስቱን በግልፅ የጣሰ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ ይህም “ህግን የተላለፈ ይዘትን አለማተም” በሚለው ስር ንዑስ አንቀጽ (1) ላይ “አታሚው (ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት) በአሳታሚው (በጋዜጣ፣መፅሔትና መፅሐፍ አሳታሚዎች) እንዲታተም የቀረበለት የፅሑፍ ስክሪፕት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ ለማመን በቂ ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው፡፡” ይላል፡፡ ይሄ ደግሞ በግልፅ ቅድመ ምርመራ(ሳንሱር) መሆኑን ያሳያል፡፡
የሚገርመው ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጋጭና የሚፃረር ማንኛውም ህግ፣ ደንብም ሆነ መመሪያ ተቀባይነት እንደሌለውም በህገመንግስቱ አንቀጽ 9(1) ላይ “የህገ መንግስት የበላይነት” በሚለው ስር ንዑስ አንቀጽ (1)
“ህገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው” ይላል፡፡ ማንኛውም ህግ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም” ተብሎ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
ምንም እንኳ በወረቀት ላይ ተፅፎ የቀረ ህገ መንግስት ቢሆንም፡፡ ከዚህ በፊት የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶ አዋጅን ጨምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የተለያዩ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ህገ መንግስቱን ሲጥሱ በተደጋጋሚ ቢታይም፣ የተወሰደባቸው ርምጃ ግን አልነበረም የሚል ሰሚ ያጣ አቤቱታ መኖሩ ባይካድም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እነሱ ከህግ በላይ በመሆናቸው እና ህገመንግስቱ ማስፈራሪያ እንጂ የዜጐች የጋራ የቃልኪዳን ሰነድ እንዳልሆነ በሚያሳብቅ መልኩ እየተንፀባረቀ ይገኛልና፡፡
ለዚህም ማስረጃነት በሀገሪቱ እውነት ህግ የሚከበርና ህገ መንግስት የሀገሪቱ የበላይ ህግ ቢሆን ኖሮ ብርሃንና ሰላም (የመንግስት መስሪያ) ቤት ሳንሱር የሚያደርግ አዲስ ውል ተፈጻሚ ሊያደርግ ባልደፈረ ነበር፡፡ነገር ግን ውሉ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስም ይምሰል እንጂ መመሪያው የተላለፈው ከአቶ መለስ ዜናዊ አሊያም ከአቶ በረከት ስምዖን እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይሄ ደግሞ በህግ ፈቅዶ በማተሚያ ቤት መከልከል ስጋ ሰጥቶ ቢላዋ እንደመከልከል ይቆጠራል፡፡
ሌላው በዚሁ ውል አንቀጽ 10(2) ላይ ደግሞ “አታሚው (ብርሃንና ሰላም) አሳታሚው የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል፡፡” ይላል፡፡ይሄም ግልፅ አይደለም፡፡ምክንያቱም ዋና አዘጋጅን ጨምሮ በህትመቱ ላይ የሚሳተፉት ጋዜጠኞችና አሳታሚው ቀድሞም ቢሆን የህግ ተጠያቂነት እንዳለበት በህግ ተደንግጓልና፡፡ ነገር ግን ብርሃንና ሰላም አዲስ ላመጣው ውል መልስ “ሃያ ጅቦ ሳታመሃኝ ብላ” አይነት ነገር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡አሁን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት እንደራሴ ሆኖ እየገበረ ያለው የኢህአዴግን አዲስ የታወጀውን የመጨረሻ ዘመቻ የሚያሳይ ይመስላል፡፡
የዴሞክራሲ ካባ፣ ዕርዳታና የጨለማው ጉዞ
ኢህአዴግ የቅንጅት ተወዳዳሪዎችን በተለይም ከፍተኛ አመራሮች ጋር የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችን ማሰሩ ከፍተኛ ዋጋ በማስከፈል አስደንግጦት ነበር፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሳይወድ በግድ የዴሞክራሲ ስርዓትን እገነባለሁ ብሎ መድረሻው ባይታወቅም በዴሞክራሲያዊ ካባ ስም ዕርዳታ ይቀበላልና፡፡ ከዚያም በበቀል የሄደበት ስሜት እንዳላዋጣው ሲረዳ የተሰደዱትን መመለስ ባይችልም የታሰሩትን የፖለቲካ አመራሮችን ሲፈታ ጋዜጠኞችንም ለቋቸዋል፡፡ ከተፈቱት አንዳንድ ጋዜጠኞችም በድጋሚ ጋዜጣ እንዳያሳትሙ ተደርገዋል፡፡ወደ ህትመት ስራ የገቡት ላይም አሳሪ ህግ ከማውጣት በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የማተሚያ ዋጋ እንዲጨመር መደረጉ አይዘነጋም፡፡
ቀስበቀስም በዴሞክራሲ ስም የሚመጣው እርዳታ እንዳይነጥፍ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን ከመሬት ተነስቶ ማሰር ስለማያዋጣ እንቅስቃሴያቸውን ለመገደብ የሚያስችል ህግ በማውጣት አማራጭ የሌለው መሆኑን በማሰብ ገዥው ፓርቲ ተግብሮታል፡፡ ለምሳሌ ከህገመንግስቱ ጋር የሚፃረሩ በርካታ አንቀጾች እንዳሏቸው የሚነገርላቸው “የነፃው ፕሬስ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፀረ ሽብርተኝነት እና የበጎ አድራጎት ማኀበራጽ አዋጆች” ከምርጫ 1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ የወጡ አሳሪ ህጎች ናቸው የሚሉ አልታጡም፡፡
ይሄንንም አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በተለይ ኢህአዴግ በሀገሪቱም ሆነ በህዝቡ ላይ በርካታ በደሎችን፣ ክህደትንና ሙስና ስለፈፀመ ከስልጣን ቢወርድ የሚመጣበትን መዘዝ በማሰብ ዜጐችን ከመካስ ይልቅ አመራሮቹ እስከ ፍጻሜ ለመቆየት ያወጡት ህግ እንደሆነ ይደመድማሉ፡፡
በነዚህም ምክንያት ኢህአዴግን ጠንቅቀው የሚያውቁና በእጅጉ የሚግደራደሩ ናቸው የተባሉና እስከዛሬም ድረስ የሚፈራቸው አንዳንድ የቀድሞው የቅንጅት አመራሮችም በሀገር ውስጥ “የዴሞክራሲ ሥርዓት አብቅቶለታል፣ ይሄንንም በምርጫ ተወዳድሮ መቀየር አይቻልም፣ ኢህአዴግ በምርጫ ቢሸነፍም ስልጣኑን የመልቀቅ ፍላጐት የለውም” በማለት ወደሌላ የትግል ስልት (ኢህአዴግ የመጣበትን) መንገድ የተከተሉም አሉ፡፡
ይሁን እንጂ ገዥው ፓርቲ በበኩሉ “የለም! በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ እየጣርኩ ነው፤ የመደበለ ፓርቲ ሥርዓት እውን እንዲሆንም እየሰራሁ ነው” ሲል በመሞገት በዴሞክራሲ ስም የሚመጣውን ዕርዳታ እንዳይነጥፍ የሚታገል ይመስላል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው “ህገመንግስቱ በአዋጅ እየተሸረሸረ እልቋል፤ የዴሞክራሲ ሥርዓትም ሆነ የመደበለ ፓርቲ ሥርዓት እያከተመ ምህዳሩ እየጠበበ ነው” በማለት ራሱ ኢህአዴግ የሚሰራውንና የሚናገረውን ዋቢ አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡
የአባሎቻቸውን መታሰርንም በማስታወስ፡፡
ከላይ ለተጠቀሱ ሐሳቦች ማጠናከሪያም የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችም በህገ መንግሥቱ የተፈቀዱ መብቶች በአዋጅ መሻራቸውንና መጭው ጊዜ አስፈሪ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ለምርጫ 2002 ዓ.ም ለኢህአዴግ ስጋት ናቸው የተባሉ ፖለቲከኞች ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በወቅቱ መታሰራቸውና የአዲስ ነገር ጋዜጣ ከምርጫው በፊት እንዲዘጋ በማድረግ ጋዜጠኞቹ ከእስር አምልጠው መሰደዳቸውንም የሚያስታውሱ አሉ፡፡
ስጋት ያንጃበበት ፍርሃት
የተፎካካሪ ፖለቲከኞች እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ፣ ማቆሚያ የሌለው የዋጋ ግሽበት፣ ሃይ ባይ የታጣለት የምግብ እና የሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ መናር፣ በነጋዴዎች ላይ ከልክ ያለፈ የግብር ጫና፣ የወጣቱ ሥራ አጥነት፣ የኢህአዴግ የጭፍን ጉዞ እና የቀጠናው አለመረጋጋት ለህዝቡ ትልቅ ስጋት መሆናቸውን የሚናገሩ አልታጡም፡፡ ይህም አውነትም “ጥቁር ሽብር” ይመስላል፡፡ በሀገሪቱም ባለው የገዥው ፓርቲ አፋኝነት በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር እጦት እና የኑሮ አለመረጋጋት መምህር የኔሰው ገብሬ፣ ታጠቅ ህሉፍ የጠባለ የመከላከያ ሠራዊት አባል፤ እና በቅርቡም ምኒሊክ አደባባይ (አራዳ ጊዮርጊስ) ፊት ለፊት ጨምሮ አንድ ዳዊት የሚባል የፖሊስ አባል ራሳቸውን ማቃጠላቸው “የጥቁር ሽብር” ሌላው ማሳያ እንደሆነ የሚገልፁም አሉ፡፡
ከዚህ በፊት ዜጐች “ነጭ ሽብር ቀይ ሽብር”በሚል የመጠፋፋት ፍልስፍና በሀገሪቱ መተግበሩን በማስታወስ አሁን ያለው ከዚህ የተለየ ይመስላል፡፡ ዜጐች ባለው ስርዓት ሲማረሩ ራሳቸውን ባሰቃቂ ሁኔታ ማጥፋት የሰዎች ያልተለመደ ዝምታ (በታመቀ ስሜት) መታየት፣ የርሃብ መበራከት ይህንንም በይፋ ያለመግለፅ፤ የምግብ ዋጋዎች መናር፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት (ፍ/ቤት፣ ፖሊስ፣ . . . እና ሌሎችም) የህዝብ አመኔታ ማጣት፣ የዜግነት ክብርና መብት ማጣት፣ የገዥው መንግስት አምባገነንነት እየጨመረ መሄድ፣ ሀገሪቱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይከታት የሚሰጉ አልጠፍም፡፡ ይህንንም በአፈናና በርሃብ የሚተገበር “የጦር መሣሪያ የሌለበት ሽብር ጥቁር ሽብር” ነው ይላሉ፤የነፃ አስተሳሰብ በር መዘጋቱንም በመግለፅ፡፡
አሁን ባለው የኢህአዴግ አካሄድ አገዛዙ ማብቃቱን በመጠቆም አመራሮቹ በተለያየ መንገድ ባለባቸው ሀገር የመምራት ብቃት ማነስና ተስፋ መቁረጥ የተነሳ ራሳቸውን ስልጣን ላይ ለማቆየት ሲሉ የተለያዩ አስከፊ ስልቶችን በመቀየስ ህዝቡ ላይ ርምጃ ሊወስዱም እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ሁኔታዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡
ለዚህም አማራጭ አድርገው ይወስዳሉ የተባለውም የአንዱን ማኅበረሰብ ባህልና ወግ ሌላው እንደናቀ አድርጐና አስመስሎ በመናገር፣ አንዱን የኃይማኖት ተከታይ በሌላው ላይ ማነሳሳትና ፍርሃት መፍጠር፣ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ ሌላውን ማስነሳት፣ ባለሃብት ነጋዴዎች ላይ ደግሞ ሌላ ባለሃብት ራሳቸው በመፍጠር ከንግድ ዓለም በተለያየ መንገድ እንዲወጡ ማድረግ እና አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የእርሻ ግብዓቶችን (ማዳበሪያና ዘር) በውድ ዋጋ ከኢህአዴግ የንግድ ድርጅቶች እንዲወስዱ በማስገደድ የሚወስዱት ርምጃ
ሊኖሩ እንደሚችል በመጠቆም፤ ይህም ከወዲሁ እየተተገበረ እንዳለና ወደፊትም ሊቀጥል እንደሚችል ይገመታል፡፡
በተለይ ለኢህአዴግ ስጋት ሆነዋል የተባሉት በጥቂቱ ባሉት ህጎችም ቢሆን እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጋዜጦች (ከመንግስት ውጭ) በቀጥታ ከመዝጋት ይልቅ ገዥው መደብ በማተሚያ ቤቶች አማካኝነት ከገበያ ውጭ ለማድረግና ለማስቀረትም እየታሰበ እንዳለ አንዳንድ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡
የነኚህ ሂደቶችም መንግሥት በመጪው ለሚካሄደው የአዲስ አበባ ምርጫና የህዝቡን የታፈነ ዝምታ ለመግታት ታስቦ ከወዲሁ አፋኝ ድርጊቶችን ሊፈፀም እንደሚችል ይገመታል፡፡ በተለይ ለኢህአዴግ ስጋት ይሆናሉ(ለኢትዮጵያ ያይደለ) ተብለው ከላይ የተጠቀሱት የሚተገበሩ ከሆነ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ መጥፎ (አስከፊ)ነው፡፡ ምናልባትም በሀገሪቱ ይታያል ተብሎ የሚታሰበው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ፍፃሜው ይሆንና ሀገሪቱ ያልታሰበ አዘቅት ውስጥ ልትገባ ትችላለች፡፡ ህዝቡም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ የሚያመሩ መንገዶች ከተዘጉና ወደ ሌላ የትግል ስልት ያመራና ታሪክ ሊደገም ይችል ይሆናል፤ግን ባይሆን ይመረጣል፡፡
ከላይ በተጠቀሱ ሐሳቦች ምክንያትም ሀገሪቱ ከፍጹማዊ አምባገን አገዛዝ “በምርጫ” ወደ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ እያመራች ነበር ቢባልም ቀጣዩ ጉዞ የባሰ እየሆነ እንደመጣ ይገመታል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ እየተጓዘች እንደሆነ እያመለከተ እንደሆነ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡ በተጨማሪም ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ወደ ጨለማ ጉዞ ውስጥ እየከታት ነው በማለት ስርዓቱን ተጠያቂ የሚያደርጉ ዜጐችም እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የቀረበው የኢህአዴግን አምባገነንት በግልፅ የሚያረጋግጥ እንደሆነ በመጠቆም በተለይ በነፃ አስተሳሰብ ላይ የተቃጣ ጥቁር ሽብርና በፕሬስ ላይ የታወጀው የመጨረሻው ዘመቻ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment