Monday, June 24, 2013

እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምንናፍቀው ዲሞክራሲ

             ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምንናፍቀው ዲሞክራሲ
የኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲን እንደሚሻ፣ መልካም አስተዳደር እንደሚያስፈልገው እና ከእንግዲህ አምባገነናዊ አገዛዝን እንደማይፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ በጨዋ ደንብ መልዕክት ያስተላለፈበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የኢህአዴግን ጨቋኝ ስርዓት “እምቢ” ያለበት የፍርሃትን ካባ ከላዩ ላይ ገፎ በነፃነት ብርሃን ተስፋን የሰነቀበት፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ በህዝቡ ላይ የደረሰው አረመኔያዊ ግፍን የቀላቀለ እርምጃ ያሳደረው የፍርሃት ድባብ ምን የወፈረ ምን የደደረ ቢመስልም ግንቦት ሰባት የፈነጠቀችውን የነፃነት ጐህ ለመሸፈን አልቻለም፡ ፡ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላማዊና ስልጡን የነፃነት ጥያቄ ተወደደም ተጠላ፣ የነፃነት ቀን እስከ ሚደርስበት ቀን ድረስ ግንቦት ሰባት ሁለት አይነት መልዕክት ታስተላልፋለች፡፡ አንደኛው መልዕክት በቀጥታ ለአምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት “አፈናው፣ ግፉ፣ ሙስናው ያብቃ” የሚል ሲሆን፤ ይቺ ቀን እውነተኛውን የስብዕና ነፃነት የተለማመድንባት ነበረች፡፡ ሁለተኛው መልዕክት ደግሞ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ “አጐንብሶ፣ ተጨቁኖ፣ እየተበዘበዙ መኖር ያብቃ” የሚል ነው፡፡ ሚያዝያ 30/1997 በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለቅንጅት ያለውን ፅኑ ድጋፍ መስቀል አደባባይ ተገኝቶ የገለፀበትና ዓለምን ያስደመመበት ዕለት ነው፡፡ ግንቦት 7/1997 ዓ.ም ደግሞ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ወደ የምርጫ ጣቢያው የተመመው ህዝብ ኢህአዴግ “ስልጣን በቃህ!” ያለበትና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የጠነከረ ወገናዊነቱን የገለፀበት በመሆኑ ለዘላለም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ የነፃነት ቀን ሆኖ ይታሰባል፤ ኢትዮጵያውያን በነፃ ምርጫ መንግሥታቸውን ለመምረጥ የደረሱ፤ ስልጡን ህዝብ መሆናቸውንም የሚገልፅ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ገዢው ፓርቲ ያነገበውን ነፍጥ ተማምኖ የህዝብን ድምፅ ቢያፍንም ሥርዓቱ ፍፁም አምባገነን መሆኑን ለአለም ህዝብ ማሳወቅ ተችሏል፡፡ ኢህአዴግ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ተሸናፊነቱን በፀጋ ተቀብሎ ህዝብ ለመረጠው ፓርቲ ስልጣን ማስረከብ ሲገባው አሻፈረኝ ማለቱና እስከ ዛሬም በስልጣኑ ላይ መቆየቱ ገዢው ፓርቲ የለየለት አምባገነን መሆኑን እንደሚያሳይ እሙን ነው፡፡ እንደ ቀበሮ ባህታዊ የዴሞክራሲ ለምድ የለበሰው ኢህአዴግ በግንቦት ሰባቱ ምርጫ ማንነቱ ገሀድ ወጥቷል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርዓት ያለውን ጥላቻ ያለ አንዳች ሀይል አስገዳጅነት በድምፅ መስጫ ካርዱ ገልፃጻል፡፡ በዚህም የኢህአዴግ ጎራ በከፍተኛ ድንጋጤ የራደበትና በታሪኩ ለአሳፊሪ ሽንፈት የተዳረገበት ወቅት እንደነበር የማያስታውሰው ኢትዮጵያዊ አይኖርም፡፡
        ህወሓት /ኢህአዴግ የደርግን አምባገነናዊ መንግስት ለመጣል ለ17 ዓመታት ነፍጥ አንግቦ የተዋጋው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን እንዳልሆነ ከምንም በላይ ከ97 ዓ.ም ምርጫ ይበልጥ ጉልህ ምስክር የለም፡፡ ሥርዓቱ የለየለት አምባገነን በመሆኑ የሕዝብን ድምፅ ረግጦና ከምርጫው ውጤት ውዝግብ ማግስት አያሌ ዜጎችን በጥይት አረር ገድሎ ዛሬም ቤተመንግስቱን የሙጥኝ እንዳለ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ከግንቦት 7 ቀን የምርጫ ሂደት ኢህአዴግ መማር አልቻለም፡፡ “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉ የዴሞክራሲውን ጭላንጭል በፅልመት መጋረጃ ከመከለል አልፎ ራሱን በአውራ ፓርቲነት ሰይሟል፡፡

የሥርዓቱ መሪዎች አስተዋይ ቢሆኑ ኖሮህዝብ ለምን ድምፁን ነፈገን? ስህተቶቻችን ምን ምን ነበሩ?” እያሉ ራሳቸውን (ውስጣቸውን) መፈተሸ ይገባቸው ነበር፡፡ የሕዝብን ድምፅ ረግጠው በጠመንጃቸው ጉልበት ሥልጣን ላይ እንደወጡ ልቦናቸው እያወቀ ከዕለት ዕለት ክንዳቸውን በጉልበትና በሃይል አፈርጥመዋል፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታትም በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ በሙስና በመዘፈቅ አገሪቱን ልትወጣው ወደ ማትችለው ማጥ ውስጥ ይዘዋት እየሰመጡ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍርሃት ተሸብቦ እነሱን ተከትሎ አረንቋ ውስጥ መስመጥ እንደሌለበት ከግንቦት መማር ይገባዋል፡፡  ግፉ ማክተም አለበት፤ ጭቆናው ልክና ቅጥ ሊኖረው ይገባል፡ ይህ አምባገነን መንግሥት በሕዝብ ትግል ሊወገድ ይገባዋል፡፡ ሁልጊዜ ዋይታ፣ ሁልጊዜ ሰቆቃ፣ ሁልጊዜ ከመኖሪያ ቀየ መፈናቀል መቆም አለበት፡፡ በመጨረሻም እሮሯንና ብሶታችን ያከትም ዘንድ የዚች አገር ዜጎች አንድ ሆነን እንታገል፡፡ አንድነት ኃይል ነውና ለነጻነታችን  ክብርና ዋጋ እንስጥ፡፡
ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: