Sunday, June 16, 2013

የሀገር ሸክም ከመሆን አለኝታ መሆን

             የሀገር ሸክም ከመሆን አለኝታ መሆን         

         የወረቀት ጋጋታ የፖቲካ መድኃኒት ሊሆን አይችልም፤ የህዝብንም ሰቆቃ ይታደጋል ተብሎ አይታሰብም፡፡በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች አሉ፡፡ ስላሉት ችግሮች መባባስ ተጠያቂው ማነው? ገዥው ፓርቲ? ተቃዋሚዎች? ምሁራን ወይስ ህዝቡ ራሱ? እውነቱን ለመናገር መጠየቅ ካለባቸው ሁሉም አካላት ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም አሁን በሀገሪቱ ለተፈጠረው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ እያንዳንዳቸው አስተዋፅዖ አበርክተዋልና፡፡
         የበቀልና የመጠፋፋት ትውልድ ደግሞ በምስኪኖችና የዋህዎች መስዋዕትነት፣ በኢህአዴግ ስም ስልጣን ላይ በመውጣት የአንድ እናት ልጆችን መተላለቅ የበቀል ሐውልት በመትከል አዲስ ፀያፍ ታሪክ አሁን ባለው ገዥው ፓርቲ ተሰራ፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችም 17 ዓመቱን የትጥቅ ትግል ለማካካስ በሚል 22 ዓመት በሀገር መሪነት ወንበር ላይ ሆነው እንኳ በፈፀሙት በቀል የረኩ አይመስልም፡፡ በዚህም የጠባቧ ዋሻ የደደቢት በረሃው አስተሳሰብ፣ በሰፊዋ ኢትዮጵያ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የሚገርመው ኢህአዴግ ከደርግና ከአፄ /ሥላሴ በህዝብ የተጠሉ ድርጊቶችን ከሀገር ውስጥ፤ከውጭ ደግሞ ቅኝ ገዥ የነበሩትን የእንግሊዝን ከፋፍለህ ግዛ (Divide and rule) እና የጣሊያንን ሴራ ይዞ በመተግበር የሚስተካከለው ያለ አልመሰለኝም፡፡
           ከአፄ /ሥላሴ ከወረሳቸውና በህዝብ ከተጠሉት መካከል ህዝብ (ግለሰብ) የመሬት ባለቤትነቱን ተነጥቋል፡፡ በኢህአዴግ ደግሞ በህግ ማዕቀፍ በአዋጅ የመሬት ባለቤት የሆነ ግለሰብ የገዥው መደብ አመራር ካልሆነ በስተቀር የለም፡፡ የንግዱን ሁኔታ ስንመለከት በአፄ /ሥላሴ ዘመን ለፊውዳሉ ስርዓት የቀረቡና የንጉሱ ቤተሰቦች የሀገሪቷን ንግድ ተቆጣጥረው ነበር፡፡ ለምሳሌ ማተሚያ ቤት (ብርሃን ሰላም) ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ፣ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ ዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች እና ሌሎችም፡፡ በኢህአዴግም የንግድ ስርዓቱ በግለሰብ ነጋዴ አሊያም በመንግስት የሚመራ ገበያ ሳይሆን በኢህአዴግና አጋሮቹ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለቤቱ በውል ያልታወቀው በትግራይ ህዝብ ስም የሚነገድበትና በወ/ አዜብ መስፍን የሚመራው ኤፈርት ድርጅቶችና ዲንሾ፣ ጥረት፣ ወንዶ የመሳሰሉ ግዙፍ የንግድ ኩባንያዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ገበያውን በማመስና የተለያዩ በመንግስትና በጥረታቸው ያፈሩ ግለሰብ ነጋዴዎችን የገበያ ውድድር በመዝጋት ከንጉሱ ስርዓት ይመሳሰላል፡፡
           ከደርግ በኢህአዴግ የተወረሰው ደግሞ አምባገነንነት ሲሆን የሚለየው በሱፍና በካኪ ልብስ አሊያም በስም ብቻ እንጂ በግፍ አፈፃፀም ድርጊቶቻቸው አንድ ናቸው፡፡ ሁለቱም ነፃ አስተሳሰብን አይፈቅዱም፣ ሁለቱም መለኮት (አምላክ) ነኝ ከማለት በስተቀር የዚህች አገር ፈላጭ ቆራጭ እኛ ነን ባዮች ናቸው፡፡ ሁለቱም አምባገነንነትን ህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ በመክተት፣ አዋጆችን በማውጣት ህዝቡን በማስፈራራት፣ በመፈረጅና በማሰር አንድ ናቸው፡፡ በመግደልም ቢሆን ሁለቱም በአፈሙዝ ሥልጣን የያዙ በመሆናቸው እጆቻቸው በሀገር ልጅ ደም የተጨማለቀ
ነው፡፡ እዚህ ላይ እኔ ለሀገር ሳይሆን ለስልጣን ስል ሰዎችን በግፍ አልገደልኩም፣ ንፁህ ነኝ የሚል ከሁለቱም ስርዓቶች አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የገደሉትና የጨፈለቁት ቁንጫና ቲማቲም ሳይሆን የሰው ልጅ ነውና መቼም ቢሆን ከህዝብ አይሰወርም፡፡
      ሌላው ኢህአዴግን ከእንግለዝ ቅኝ አገዛዝ ጋር የሚያመሳስለውየከፋፍለህ ግዛሴራ ሲሆን ይህም ጐጥንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለመሪዎቹ ያለውም ጠቀሜታ ህዝቡን በቋንቋና በጐሳ በመከፋፈል እርስ በእሰርስ እንዲጋጩ በማድረግ የቤት ሥራ መስጠትና ባተሌ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያም ህዝቡ ህብረት ወይም አንድነት የሚል ጥያቄ እንዳያነሳና ስለዜግነትና ሀገር እንዳያስብ ማድረግ ሌላው ስልት ነው፡፡ ለዚህም ከቀበሌ መታወቂያ ካርድ ይጀምራል፡፡ ይሄ በኢህአዴግ እንግሊዝ በገዛቻቸው ሀገሮች የተገበረችው በኢትዮጵያም ያውም 21ኛው ክፍለ ዘመን ተደግሟል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የቀበሌ መታወቂያን ብንመለከት ዜግነት የሚል ጠፍቶ ብሔር በሚል ተተክቷል፡፡ ይሄንን ማንም በእጁ ያለ ማረጋገጥ ይችላል፡፡ ይሄም የሚሞላውና የሚፈፀመው በኢህአዴግ እንጂ በህዝቡ ፍላጐት አይደለም፡፡
           ከጣሊያን የተወረሰው ደግሞ በአድዋ ጦርነት ሽንፈት ከተከናነበች በኋላ ጣሊያን የበቀል ሴራ ስልት ጀምራ እንደነበር የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ለምሳሌ ጣሊያኖች የሰፈሩበት ቦታ ያሉትን ነዋሪዎችእናንተ ከሁሉም ታላቅ ናችሁየሚልና በኃይማኖትና ጐሳ የመከፋፈል ሴራ በማድረግ ህዝብ ማጋጨት ተፈፅሞ ነበር፡፡ ይሄንንም ኢህአዴግ ደግሞታል፡፡ የሚገርመው ለምን እንደሆነ ባይታወቅም ኢህአዴግ ለራሱም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ነገርን መኮረጅና ማምጣት የሰማይ መና ያህል ርቆበታል፡፡ ክፉ ነገሮችን በመኮረጅና በመተግበር ግን ከዓለም የሚቀድመው የለም፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያዩ አዳዲስ ክፉ ነገሮች በመተግበርና ህዝብን በማመስ፣ የህዝብን ህልውና የሚፈታተኑ ድርጊቶችንና አዋጆችን በመተግበር ሀገሪቱን የዓለማችን የክፉ ድርጊቶች ፖለቲካ ቤተ ሙከራ በማድረግ ለተቃዋሚዎችም እያስተላለፈ ይገኛል፡፡ በዚህም ሀገሪቷ የህዝብን ችግርና ሰቆቃ በካባና ስም በመቀያየር ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡
            ተቃዋሚዎች ጋር ስንመጣ ደግሞ ፖለቲካ ሳይገባቸው ወደ ፖለቲካው የገቡ፣ ማውራት እንጂ
መተግበር የማይቀናቸው፤ እርስ በርስ ተተብትበው በመጠላለፍ ካባቸው ፖለቲከኛ ውስጣቸው ባዶ የሆኑና ለህዝቡ ከንቱ የተስፋ ዳቦዎች አሉ፡፡ እነኚህም የህዝቡን ሰቆቃ ዕድሜ በማራዘምና የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ በማባባስ ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡
            አንዳንድች ተቃዋሚ የሆኑና የራሳቸው ፕሮግራምና ደንብ ኖሮአቸው ተግባራቸው የሚቃወሙትን ሆነው የሚገኙም አይጠፉም፡፡ለምሳሌ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጥ የትምህርት አቅምም ሆነ የአመራር ብቃት የሌላቸው ህዝብን እያገለገሉ ሳይሆን በህዝብ እየተገለገሉ ሰርተው የማያሰሩ የቢሮ ጡረተኞች በብዛት አሉ፡፡ እነኚህ ሰዎች በገበያ ዋጋ ተወዳድረው መስራት ስለማይችሉ የተሳሳተ መረጃ በማስተላለፍ ሀገር የሚያምሱ ዕዳዎች ናቸው፡፡ እነኚህ ሰዎች ለተማረው አሊያም ብቃት ላለው/ ላላት ከማስተላለፍ አጥፍተው መጥፋት ይመርጣሉ፡፡ ለበላይ አመራርም ታማኝ በመምሰል ጭራ እየቆሉ የሚሙለጨለጩ ሳሙናዎች ናቸው፡፡ ስራቸው ሁሉ መልካምና ፍፁም ጥሩ እንደሆነ ይደሰኩራሉ፡፡ አመራሮችም ከአዲስ አስተሳሰብ ጋር ከመላመድና ከመሄድ 1960ዎቹ ውስጥ የነበረውን አመለካከት 2000ዎች ውስጥ ያንፀባርቃሉ፡፡ ይሄ በስፋት ልክ እንደ ኢህአዴግ ሁሉ ተቃዋሚዎች ጋርም ይስተዋላል፡፡ በአምባገነንነቱ ኢህአዴግን እየወቀሱ ራሳቸውም የግል ፍላጐታቸውን በህዝብ ትከሻ ተንጠልጥለው ለማራመድ ሲሉ የመሪነቱን ወንበር ከአቶ መለስ ዜናዊ ባላነሰ መልኩ የሙጥኝ እንደ መዥገር የሚሉ እንዳሉ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ሌሎቹ ሰርተው የማያሰሩ ወንበሩ ላይ ተኝተው የፓርቲ ጡረተኞችም አሉ፡፡ ይህን ስል ግን ዕድሜያቸው የገፋና የሀገር ስሜትና ተቆርቋሪነት ኖሮአቸው የሚሰሩትን ማለቴ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ የፖለቲከኞች (expired date) ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡አንዳንዱ ደግሞ የሚሰሩ አባሎቻቸውን በጥርጣሬ በማየት፣ በመፈረጅና እንቅፋት በመሆን የእነሱን ሥንፍና እና የአቅም ማነስ እንዳይጋለጥ አላሰራ የሚሉም አይጠፉም፡፡ እነኚህም ከኢህአዴግ ባላነሰ የህዝብን የሰቆቃ ጊዜ የሚያራዝሙ ናቸው፡፡
            ለሀገርና ለህዝብ ጥቅምና መብት እንታገላለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ቢሆኑ ቢሮ ተቀምጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከማንጋጋት በተግባር ወደ ህዝብ ወርደው ከህዝቡ ጋር ሊሰሩ ይገባል፡፡ በዚህም የሚከፈል መስዋዕትነት ካለ ለመቀበል በቁርጠኝነት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ አይ ቢሮ ተቀምጠን እንሰራለን እያሉ የሚፈሩም ካሉ ለሚሰሩት መልቀቅ፣ የሚሰሩትንም ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ አለበለዚያ ሌላው በከፈለው መስዋዕትነት ስልጣን ላይ ለመቀመጥ መሞከርከእጅ አይሻል ዶማዓይነት ነገር ነውና ጊዜ ሳይሰጠው ሊታሰብበት
 ይገባል፡፡ በተጨባጭ ሀገሪቱ ለውጥ ትሻለችና፡፡
           ፊደል ቆጥረዋል የተባሉ ምሁራንም ቢሆኑ በህዝባቸውና በሀገሪቷ ሀብት ከመቀለድ ያለፈ እዚህ ግባ የሚባል አስተዋፅዖ ሲያበረክቱ አይታዩም፡፡ አይደለም በፖለቲካና ማህበራዊ ህይወት በሚሰሩበትና በሚጠቀሙበት ሙያ እንኳ ለትውልድ አርዓያ መሆን የሚችሉ እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነኚህ ምሁራን ሙያቸው በማይገባው ሰው ሲደፈጠጥ ከማጉረምረም ባለፈ ድሮ የተማሩትንና የሸመደዱትን መልሶ ከመገልበጥ የዘለለ ለምን ሲሉ አይታዩም፡፡ እንዲህ ዓይነትምሁራንደግሞ ለሀገር እዳዎች ናቸውና ቢያንስ ለሞያቸው ሲሉ ሊቆረቆሩና ሊሰሩ ይገባል፡፡
            እዚህ ላይ አንዳንድ በዕድሜ አንቱ የተባሉ ለወጣቱ ግን ምሳሌ መሆን ያልቻሉምሁራንላሳደጋቸውና ለወለዳቸው ገበሬ እንኳ ሲበደልና ሲጨፈለቅ ሲያዝኑለት አይታዩም፡፡ ምሳሌ ያልሆኑለትን ወጣቱን ሲረግሙና አቃቂር ሲያወጡ ይታያሉ፤ ዕዳዎች፡፡ የሚገርመው ደግሞ አንዳንድ ለወገንና ለሀገር ተቆርቋሪ የሆኑ ጐልማሳ ፖለቲከኞችን እየተደበቁበርቱ አይዟችሁ፣ ከጐናችሁ ነንሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ለምን ፊት ለፊት ወጥተህ አሁን ያልከውን ከህዝቡ ጋር አትደግመውም? ሲባልልጆቼን ላሳድግ፣ ቤተሰብ አለኝየሚል መልስ ሲሰጡ ይሰማል፡፡ ተመልከቱ ሀገሪቷ ምስቅልቅሏ እየወጣልጆቼን ላሳድግይላል፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት ወላጅ እውነት ለልጆቹ አስቧልን? የልጆቹ መኖሪያ ሲፈርስ የት ይሆን ልጆቹ የሚያድጉት? እዚህ ላይ ፍርሃት በቤተሰብና በልጆች ስም መደለል አዋቂነት አይደለም፡፡ የዳር ተመልካች በመሆንም የሌላ ታሪክ ለመዘብዘብ ግን የሚቀድማቸው የለምና እውነት ለልጆቻቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለሀገራቸው የሚያስቡ ከሆነ የሀገር ሸክም ከመሆን አለኝታ መሆንን ቢመርጡ ለክብራቸውም ሆነ ለታሪካቸው ይበጃል ባይ ነኝ፡፡ አሁን በሀገሪቱ ላለውና ለተፈጠረው ምስቅልቅልም እጃቸው እንዳለበት ሊያውቁት ይገባል፡፡
            ሌላው የህዝቡ ሚናን ብንመለከት በፍርሃት ተሸብቦ በኢትዮጵያ ያልታየ ታሪክ ሲፈጥር ይታያል፡፡ በዚህም ሀገሪቷ በቴሌቪዥን ስትበለፅግ በተግባር ስትማቅቅ ጉንጭን ተደግፎ በየጓዳው ማጉረምረሙን ግን ይችልበታል፡፡ የሚገርመው ህዝቡ ራሱ ያለበትን የሰቆቃ ህይወት ከመረዳት ይልቅ የቴሌቪዥን መስኮት ብልፅግና ሲደሰኩር ይታያል፡፡ ግን ደግሞ እቤቱ ለብቻው ያጉረመርማል፣ ይበሳጫል ከዚህ ባለፈ ሁሉ በእጁ ሆኖ ይለምናል፡ ይሄንን ነው መፍራት፡፡ የሚገርመው በምርጫ ወቅት 3 ወራት ሆዳቸው ሙሉ ጓዳቸው ባዶ የሆኑ የሌሎች መጠቀሚያ የሆኑም እንዳሉ ቤት ይቁጠረው፡፡ በመጨረሻም ቤሳቤስቲን ሳያገኙ የኑሮ ውድነቱ ከቀን ወደቀን እንደ ክረምት ደመና ሲጫናቸው ይታያል፣ ምርጫው ካለፈ በኋላም የመረጥኩት ለዚህ ነው? ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰዎች አሁንም አልገባቸውም ማለት ምክንያቱም እነሱ በፈቃዳቸው የምርጫ ወቅት መጠቀሚያ ካርድ እንጂ እንደዜጋ ሲታሰቡ አይታይምና፡፡ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ሰው ያውም መብቱንና ክብሩን በ3ወርና በሳምንት ሆዱ የሚቀይር ከሆነ ጥፋተኛው ራሱ እንጂ ተደልሎ የመረጠው አካል አይደለምና፡፡
             የሚገርመው ገዥውንም ሆነ ተቃዋሚዎችን ወዳልሆነ አቅጣጫ ሲጓዙ ማስተካከል የሚችልበት አቅም እያለው ኃይሉን ግን መጠቀም አልቻለም፡፡ ለመብቱም ሌላ ሰው እንዲጮህለት እና እንዲታገልለት ይፈልጋል፡፡ እውነታው ግን እያንዳንዱ ለመብቱ እራሱ እንጂ ሌላ እንዲታገልለት ማሰብ ከሰውነት ጐዳና የመውጣት ያህል  ነው፡፡ እዚህ ላይ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህፃናትን ያካትታል ማለት አይደለም፡፡ እነሱን በሚመለከት ወላጆቻቸው ናቸው ዕዳ ያለባቸው፡፡ ይህ ማለት ለብሔራዊ ውትድርና ሲጠየቅ ቀሚስና ሻሽ ለብሶሴት ነኝእንዳለውና ሁልጊዜ በየዓመቱ ጊዜ ቆሞ የጠበቀ ይመስል ዕድሜያቸው ሲጠየቅ አንድ ዓይነት ዕድሜ የሚናገሩትን ሰነፎች አይመለከትም፡
             በአጠቃላይ በገዥው ፓርቲ፣ በተቃዋሚዎች፣ በምሁራንና በህዝቡ መካከል ትልቅ የታመቀ የለውጥ ፍላጐት ይንፀባረቃል፡፡ ነገር ግን ሁሉም በፍርሃት ተውጧል፡፡ ተቃዋሚዎች ጋር ስንመጣ ደግሞ ወንበር ላይ ተቀምጠው የሚጦሩና የቢሮ ውስጥ ፖለቲካ የሚያራምዱ በህዝብ ስም የሚነግዱ በተግባር ግን ባዶ የሆኑ አሉና ህዝቡም ለይቶ የራሱን አስገዳጅ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ይህ ማለት ጦርነት፣ ብጥብጥ፣ ሁከትና ዝርፊያ ይፈፀም ማለት አይደለም፡፡ በተግባር ሊያታግላቸው ያልቻለውንና ሰርተው የማያሰሩ የሀገር ሸክም የሆኑ ፖለቲከኞችም የህዝብን የሰቆቃ ዕድሜ ከማራዘም ተቆጥበው ቁርጠኛ እንዲሆኑ የመለየትና የማጥራት ሥራ መስራት አለበት፡፡ ፖለቲከኛውም ከፍርሃት ተላቆ በመድፈር እውነተኛ ታጋይ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አለበለዚያ እቤቱ መቀመጥ አለበት፡፡ ሀገሪቷም እየተጓዘችበት ያለው ሁኔታ ለውጥን የሚጠይቅ ነውና ኢትዮጵያን የዓለማችን የፖለቲካ ቤተሙከራ ከማድረግ ልንታደጋት ይገባል፡፡
            ማንም ሰው ቢሆን ለውጥ ከፈለገ በተግባር ከጓዳ ወጥቶ መንቀሳቀስ አለበት፣ የተበታተኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችም 93 አሊያም 65 ድርጅትነት ቢያንስ በሚያሰማማቸው ተስማምተው የሀገርንና የህዝብን ጥቅም በማስጠበቅ ወደ አራት/አምስት በመምጣት ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይሄ ደግሞ የህዝብንም ድምፅና ሐሳብ ከመበታተን ይታደጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየቢሮ መብዛት የዴሞክራሲ መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ሲባል አንድ አምባገነን ይምራ ማለት ሳይሆን ፖለቲከኞች ወደ ውህደት ማምራት አለባቸው ለማለት ነው፡፡ ለዚህ ሁሉም ለለውጥ መድፈር አለበት፡፡ ማንም መኖርን ስለወደደ ከመሞት አያመልጥም፤ ሞትን ስለፈራም ዘለዓለም አይኖርም፡፡ የአንዲት ቀን የነፃነት ህይወት ሺህ ዓመት የሰቆቃ ዕድሜን ታስንቃለችና፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዜጋ ነፃነትን ሲሰብክ ቅድሚያ ራሱ ነፃ መውጣቱ አለመወጣቱን በመፈተሸ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ፣ ለነፃነቱም መድፈር አለበት፡፡
 
ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!


No comments: