በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ኢንቨስተር መንግስት ነው ሲል የአለም ባንክ አስታወቀ
ኢሳት ዜና:- ባንኩ በገንዘብና የ ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አነሳሽነት ያጠናቀረውን ሪፖርት በሸራተን አዲስ ይፋ ሲያደርግ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም በከፍተኛ መጠን ኢንቨስት ያደርጋሉ ከሚባሉ ሦስት መንግሥታት መካከል እንደሆነ ፤በ አንፃሩበግል ዘርፉ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት የ ኣለማችን ስስድስተኛው ዝቅተኛ ኢንቨስትመንት መሆኑን አመልክቷል፡፡
እንደ ሪፖርተረ ዘገባ፤ የባንኩ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጉዋንግ ቼንግና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር አብርሃ ተከሰተ በተገኙበት በሸራተን አዲስ ይፋ የተደረገው የዚህ ሪፖርት ዋነኛ ትኩረት መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ሚና የሚመለከት ነው።
ሪፖርቱ፤ በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እየጨመረ የመጣው የመንግሥት ኢንቨስትመንትን በጥልቀት የመረመረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ኢንቨስትመንት ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነውን ድርሻ የሚወክል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም በሰፊው ኢንቨስት እያደረጉ ከሚገኙ መንግሥታት ተርታ ተመድባለች፡፡
እንደ ሪፖርቱ በኢንቨስትመንት ረገድ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚበልጡት ሁለት አገሮች፦ ተርክሜኒስታንና ኢኳቶሪያል ጊኒ ናቸው።
ይህ የመንግስት ድርሻ የግል ዘርፉን ያለ ቅጥ በማቀጨጭ የመጣ መሆኑንም የባንኩ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በሪፖርቱ እንደተመለከተው በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንቨስትመንት ምጣኔው ከመጨረሻ ወደ ላይ ስደስተኛ ደረጃን ነው የያዘው፡፡
የመንግሥት ዘርፍ ኢንቨስትመንት- ከግሉ ዘርፍ ጋር ሲነፃፀር ሦስት እጥፍ መሆን መቻሉ፤ ሌላው በአትኩሮት የተነገረ ጉዳይ እንደነበር ከሪፖርተር ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
የዓለም ባንክ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው የ10.7 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ከቀጠለ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ለመሠለፍ ከአሥር ዓመት በላይ ላይፈጅባት እንደሚችልም መዘገቡ ተመልክቷል።
No comments:
Post a Comment