Friday, June 28, 2013

ተምሮ መንከራተት እስከመቼ?

      ተምሮ መንከራተት እስከመቼ?
        የአንድ ሀገር የትምህርት ፖሊሲና አቅጣጫ በትምህርት ስርዓቱ አልፈው የሚወጡትን ተማሪዎች ሙያዊ ብቃት ይወስናል፡፡ የተማሪው የግል ጥረት እና የሚማርበት አካባቢ ሁኔታ በተማሪው ሙያዊ ብቃት ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ የትምህርት ስርዓቱ የሚያፈራቸው ተማሪዎች ማንነት ላይ ጉልሁን አሻራ ያበረክታል፡፡ በሌላ አነጋገር በአንድ ስርአተ ትምህርት ተቀርፀው የሚወጡ ተማሪዎች ስኬትም ሆነ ውድቀት የትምህርት ስርዓቱን ውድቀትና ጥንካሬ ያሳያሉ፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ተግባራዊ ያደረገው የትምህርት ስርዓት ልምሻነት ብዙ ማሳያዎችንና ንድፈ ሀሳባዊ ትንታኔዎችን መስጠት ቢቻልም፣ ስርአቱ እያፈራ ያለውን የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሩቃን ሙያዊ ብቃትና ተፎካካሪነት የትምህርት ፖሊሲው ኪሳራ ማመላከቻ ነው፡፡ በምጣኔ ሀብት፣ በምህንድስና ወይም በስታትስቲክስ የሰለጠነ ምሩቅ በሰለጠነበት ሙያ የማይሰራ ከሆነና ተደራጅቶ ሲሚንቶ እንዲሸጥ ወይም ኮብል እስቶን ፈልፍሎ እንዲደረድር ከተደረገ አሊያም በሰለጠነበት ሙያ ለመቀጠር ለአመታት ከተንከራተተ፣ የትምህርት ስርዓቱን ልምሻነት አስረግጦ ያሳያል፡፡
        በመሠረቱ የአንድ ሀገር የትምህርት ስርዓት ሀገሪቱ ያላትን የሰለጠነ የተማረ የሰው ሀይል ፍላጐት እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ሀይል ክፍተት ከግምት የሚከት መሆን ይገባዋል፡፡ በሀገሪቱ የማይፈለግ ወይም ከሚፈለገው በላይ የሚሰለጥን ምሩቅ ማፍራት ብቻውን እንደስኬት መታየት የለበትም፡፡ መንግስት በርካታ ዩኒቨርስቲዎችን የማስፋፋቱን ያክል ዩኒቨርስቲዎቹ ስለሚያስፈልጋቸው መምህራንና የትምህርት መረጃዎች ቆም ብሎ ማሰብ ተስኖታል፡፡ በመሆኑም ደረጃቸውን ያልጠበቁ ዩኒቨርስቲዎችን በማስፋፋት የቁጥር አምልኮውን ተያይዞታል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎቹ ቁጥር ማደጉ በራሱ እንደ እድገት ሊታይ እንደማይገባው እናምናለን፡፡ ጥራት ከሌላቸው ተቋማት ሙያዊ ብቃት ያላቸውን ምሩቃን መጠበቅ ያስቸግራል፡፡ በመሆኑም መንግስት የተማሪዎችን ተወዳዳሪነት ለማስጠበቅ የከፍተኛ ተቋማትን ጥራት ማስጠበቅ ይጠበቅበታል፡፡
       መንግስት በየዓመቱ ለተመራቂውም ሆነ ለማንኛውም ሥራ ፈላጊ ዜጋ ከሞያው፣ ከእውቀቱና ከልምዱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የሥራ መስክ የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡ ተመራቂ ወጣት ምሁራንም በተመረቅንበት ሞያ ተመጣጣኝ ሥራ ይሰጠን ብሎ መጠየቅ የዜግነት መብት ነው፡፡ ሥራ አይናቅም፤ ሥራ ክቡር ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ማለት ግን 15 ቀን ሥልጠና ዜጐች ሊሰማሩበት በሚችል ሥራ መስክ ላይ 16 ዓመት ተምሮ በዲግሪ የተመረቀ ባለሞያ ማሰማራት ግዴታ አይደለም፡፡ አገራችን የተማረ ዜጋ የተትረፈረፈባት አገር አይደለችም፡፡ ወጣት ምሁራንን መንግስት በአግባቡ ሊይዛቸው ይገባል እንላለን፡፡

        አንድ አገር የመጀመሪያው ትልቁ ሀብቷ ዜጐቿ ናቸው፡፡ የዜጐቿን እውቀት፣ ጉልበትና ልምድ አደራጅቶና አስተባብሮ ለአገር ልማትና ዕድገት ሊያውለው ይገባል፡፡ በኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን እንደተመለከትነው ግን ወጣት የዩኒቨርስቲ ምሩቃንን እውቀትና ችሎታ ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ከማዋል ይልቅ እያደራጀ ለሥልጣኑ ማራዘሚያ ተጠቅሞባሞባቸዋል፡፡ ሥራ ለማግኘት ከፈለጋችሁ አባሌ የመሆን ግዴታ አለባችሁ ብሎ አስገድዷል፡፡ ኢህአዴግነትን ከኢትዮጵያዊነት በላይ እንደሆነ ለማስመሰል ሞክሮአል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎችም የዚህ ስርዓት ሰለባ ናቸው፡፡ ይህ እዚህ ላይ መቆም አለበት፡፡ ወጣቱ በነፃነት የመደራጀት በዜግነቱ በሰለጠኑት ሙያና በመረጠው ሥራ መስክ የመሠማራት መብት አለው ብለን እናምናለን፡፡

No comments: