ፍትህ እና ነፃነት ትናንትም፣ዛሬም፣ ነገም
ወያኔ የቀድሞዎቹን የአገዛዝ ሥርዓቶች ተክቶ መንበሩን ሲቆጣጠር በፅሁፍ፣ በቃልና በተግባር ከቀድሞዎቹ የተሻለና በእጅጉ የሚለይ ፖለቲካዊ አውድ ይዞ እንደመጣ የብዙዎች እምነት እንደነበርም የሚካድ አይደለም። አዲሱ የኢህአዴግ ስርዓት የቀድሞዎቹ አገዛዝ ሥርዓቶች ግፍና ብሶት የወለደው በመሆኑ ወደ መድረኩ ሲመጣ ለአዲሱ ትውልድ የሚሆን ሁሉን አመቻማች፣ ህገ-መንግስታዊና በነፃነት የተዋቀሩ ተቋማትን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መታሰቡ ምክንያታዊ በመሆኑ በራሱ ስህተት አልነበረም።
ትውልዱ የሚገባውን አገራዊ ተጠቃሚነት እንደ ዜጋ የማግኘት መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ኣምናለሁ። ኣምናለሁ ሲባል ማመን ብቻም አይደለም፤ እምነቱን ውሃ ሲወስደው እያየን እንዳላየ አይቶ ማለፍንም ስህተት ነው ብዬ ስለማምን፣ ችግሮቹን እና የችግሮቹን አመንጪዎች ህጋዊ በሆነ አግባብ መሞገት የዜግነት አንዱ ግዴታ ነው እላለሁ።
ሁሉም ትውልድ የራሱ አሻራ ያረፈበትን ታሪክ ፅፎ ያልፋል። አንዳንዱ የጦርነትን፣ ሌላው ደግሞ የልማትን ገድል ይፈፅማል። የጦርነትን ገድል የፈፀሙት የአሁኖቹ ባለስልጣናት ነባሩ ትውልድ የጣለባቸውን የታሪክ ኃላፊነት እና የዘመን መንፈስ መሸከማቸው ስህተት አልነበረም የሚል እምነት አለን። በጊዜው ስህተት ነው ብለው የሚያምኑት ስርዓቱ እንዳይናጋባቸው ይሰጉ የነበሩ የመንፈስ ተገዳዳሪ ባለሥልጣናት እንጂ የእነዚህ አርበኞች ደጋፊ የማህበረሰብ ክፍሎች አለመሆናቸው ግልፅ ነው። ነገር ግን የትውልድ ጥያቄ የነበረውን የነፃነት መንፈስ ተሸካሚዎቹ ተግዳሮቶቹን አንድ በአንድ ተቋቁመው የዛሬውን የፍትህ ማስጠበቂያ እርካብ ሲቆናጠጡ አስቀድሞ በእነርሱ ላይ የግፍ ትዕዛዝ ይሰጥበት በነበረው ዙፋን ላይ ቀጣዩን ትውልድ ማዋከብን የዕድሜ ማራዘሚያ ማድረጋቸውን አጥብቄ እቃወማለሁ።
የዚህ ትውልድ ገድል ጦርነት አይደለም። ጊዜውም፣ ሁኔታውም አጠቃላይ ዘመኑም ከትናንትናው የተለየ ነውና። ስለዚህም የዚህን ትውልድ መንፈስ ተሸክመን ዘመንን ለማሻገር፣ ትውልዱ ብሶቱን እንደቀድሞው አባቶቹ ከጠመንጃ አፈሙዝ ይልቅ ህጋዊና ሰላማዊ ወደሆነው ትግልና የብዕር ጠብታ ማሸጋገር አለበት ብዬ በማመኔ፤ በዚህ መንገድ በሚመጣ ማናቸውም ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እስከመጨረሻው እፀናለሁ። ነገስታቶቹ ስራችን እረፍት ቢነሳቸውም እኛ እረፍት ለመውሰድ ጊዜያችን ገና ነው ብዬ ኣምናለሁ፡፡ የተሸከምነውም መንፈስ ፍትህ እስኪያገኝ ድረስ ከአደባባዩ ገለል እንድንል እሺ አይለንም። ያየሁትን እናገራለሁ፣ የሰማሁትን እፅፋለሁ፣ ኢ-ፍትሃዊ አሰራርን እቃወማለሁ፣ ለእናት አገራችን ይጠቅማል የምላቸውንማናቸውንም ነገሮች ያለምንም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ለመስራት በፅናት እቆማለሁ። ፍትህ እና ነፃነትን የሚሰጥና የሚነሳ የማናቸውም አድሏዊ አገዛዞች ቤታቸው ቤታችን አይደለም የሚል የጋራ አቋም አለኝ።
በእኔ እምነት የዚህ አገር ነፃነትና ዳር ድንበር ለማስከበር ፍትሃዊ አሰራር እንዲሰፍን ከታገሉ ውድ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ከከፈሉት ዋጋ ያነሰም የበዛም ነፍስ የለንም። ለአገር መሞት፣ ለአገር እና ለህዝብ አለኝታ መሆን ክብር እንጂ ውርደት አይደለም። ትውልድ የሚሸከመውን መንፈስ ተሸክመን፣ ነፃነት እና ፍትሃዊነት ለሚሻው ውድ ሃገራችን አለኝታ በመሆናችን እንኮራለን እንጂ አንሸማቀቅም። ነገም የእኛ ፍፃሜ እንደ ቀደሙት ወንድሞቻችን ቢሆን ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን በአገራዊ ጉዳይ መወያየት መነቃቃት በመጀመር የራዕያቸው ውጤት በመሆን፣ ሌሎች እልፍ አዕላፍት ኢትዮጵያውያን ለእውነትና ለህዝብ ጥቅም ሊነሱ እንደሚችሉ እምነቴ ነው።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment