Wednesday, June 26, 2013

ኢህአዴግ በየዕለቱ የጭቆና ቀንበሩን በሕዝብ ጫንቃ ላይ እያከበደው መጥቷል፡፡


   ኢህአዴግ በየዕለቱ የጭቆና ቀንበሩን በሕዝብ ጫንቃ ላይ እያከበደው መጥቷል፡፡


        ዛሬ ዓለማችን ከደረሰችበት የሰልጣኔ ደረጃ አንፃር አምባገነን መሪዎችን ከሥልጣን ለማውረድ የትጥቅ ትግል በአንድነት እምነት አማራጭና አስተማማኝ አይደለም፡፡ አይታሰብም፡፡ በሠላማዊ ትግል የሚገኘው ድል ተመራጭ/አስተማማኝና ዘላቂ ነው፡፡ የተባበረ ሕዝብ ሁል ጊዜ አሸናፊ ነውና፡፡ ወጣቱን ትውልድ ለለውጥ ኃዋርያነት ማዘጋጀት ከምንም በላይ ተመራጭ ነው፡፡ በማንኛውም አገር ሥልጣን የጨበጡ አምባገነኖች በሕዝብ ኃይል ሳይገደዱ ሥልጣን እንደማይለቁ እሙን ነው። በተከፋፈለ የሕዝብ ኃይልም ገዢውን ክፍል ለማንበርከክ አስቸጋሪ ፡፡ ስለዚህ ነፍጥ አልባ /ሠላማዊ/ ትግልን ውጤታማ ለማድረግ ከጥቃቅን ነገሮች መጀመር አስፈላጊ ነው፡፡
       አገራችን ኢትዮጵያ በኢህአዴግ ፍፁም ጨካኝና አፋኝ አገዛዝ ሥር ከወደቀችበት ከዛሬ 22 ዓመት ጀምሮ ሕዝቦቿ የግፍ ፅዋን እየተጎነጩ በመኖርና ባለመኖር መሀከል እየተንገታገቱ እስከ መቼና እስከ የት ይዘልቃሉ? የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ሕዝብ ሕገመንግሥታዊ መብቶቹን እንዲያስከብር ለሠላማዊ ትግል ማነሳሳት ነው፡፡ ዜጎች በውስጣቸው የነገሰውን ፍርሃት አስወግደው በሚገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ በሚደርስባቸው የሰብአዊና ደሞክራሲያዊ መብቶች ረገጣ የተቃውም ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ በየዕለቱ የጭቆና ቀንበሩን በሕዝብ ጫንቃ ላይ እያከበደው መጥቷል፡፡ የዜጎችን የመኖር ሕልውና በብርቱ እየተፈታተነውየሕዝቡ የተቃውሞ ስሜትም ከዳር እስከ ዳር ፍፁም ተመሣሣይ መሆኑን ኢህአዴግ ልብ ሊለው ይገባል፡፡ ሕዝቡ በአንድ ድምፅ እምቢኝ፣አሻፈረኝ ብሏል፡፡ የኢህአደግ አባላት ወይም ካድሬዎች እንኳን ሳይቀሩ የድርጅታቸውን ፀረ-ሕዝብ አካሄድ በመድረክ ያወገዙበት ስብሰባ ነበር፡፡ መልሱ ቁጣ ማስፈራራትና ማውገዝ አይደለም፡፡ መልሱ የሕዝብን ውሳኔ ተቀብሎ ወደ ሕሊና መመለስ ነው፡፡ መልሱ ለብዙሃኑ ፍላጐት ተገዢ መሆን ነው፡፡
            ዛሬ ሕዝቡ እየደረሰበት ባለው ተደራራቢ ተፅዕኖ በተለይም፡-
  • ·         የመሬት ሊዝ አዋጁ ንብረት አልባ ባደረገው ወቅት
  • ·         የኑሮ ውድነቱ በየቀኑ እየጨመረ በመምጣቱ የሚላስ የሚቀመስ ምግብ ባጣበት ወቅት
  • ·         የአገሪቱን ሀብት ጥቂት የኢህአዴግ ሹመኞች ሸሪኮኮቻቸው በሚቀራመቱበትና ሃገሪቱ እስከ 11.7 ቢሊዮን  የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ወደ ውጭ እንዲሸሽ በተደረገበት ባሸሹበት ሁኔታ መሆኑ፡፡
  • ·         የአገሪቱ ሠፋፊና ለም የእርሻ መሬቶች ለውጭ ባዕዳን በጠራራ ፀሐይ በሚቸበቸቡበትና ድርጊቱ ዓለም አቀፍ    ውግዘትን ባስከተለበት ወቅት  መሆኑ
  • ·         የተማረው ወጣት ኃይል በሥራ እጦት ምክንያት የቤተሰብ ጥገኛ ለመሆን በተገደደበት ወቅት፣
  • ·         ወጣቱ ትውልድ አገሩን ጥሎ ወደ ባዕድ አገር ለእንግልት ኑሮ መሰደዱ ባየለበት ወቅት፣
  • ·         ንፁሃን ዜጎች በሕግ ሽፋን በአሸባሪነት እየተፈረጁ ዘብጥያ በሚወርዱበትና ፍርድ ትርጉም በአጣበት በአሁኑ ወቅት ተስፋ በመጨለሙ፡፡
  • ·         ድርቅና ረሃብ አርብቶ አደሩንም ሆነ አርሶ አደሩን ባጎሳቆለበትና የቤት እንስሳቱ በሚያልቁበት በአሁኑ ሰዓት ያለው ብቸኛ አማራጭ ፍፁም ሠላማዊ እና ህገ-መንግሥታዊ መብቶችን ማዕከል ባደረገ የትግል አካሄድ ኢህአዴግን ከሥልጣኑ ማውረድና በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠ መንግሥት ማቋቋም ብቻ ነው፡፡

 የዚች ሀገር ሁለንተናዊ ችግርና ፈተና እንዲያከትም ከተፈለገ መፍትሄው ይህ ብቻ ነው፡፡


ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: