የህዝብ ብሶት መፈንጃ ምክንያቱ አይታወቅም
ከ1997
ዓ.ም ምርጫ በኋላ ኢህአዴግ ማርሽ እንደቀየረ ይታወቃል፡፡ ይሄም ማርሽ ቅየራ በግልፅ እንደታየው ከጭላንጭል ዴሞክራሲ ወደ ለየለት የአምባገነንነት ስርዓት፤ ከመድብለ ፓርቲ ወደ አንድ ፓርቲ የአፈና ነፃ ሚዲያን ወደ ማይፈለግ ስርዓትነት ተሸጋግሯል፡፡ እንደዚህ አይነቱን የማይጠቅም አክሮባት (U-Tern) መስራት እነ አቶ በረከት “ከናዳ የማምለጥ ሩጫ” እያሉ ይመፃደቁበት እንጂ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ እውነትም ሩጫው ፓርቲያቸው የገቡትን ቃል ባለመፈፀማቸው ከተነሳባቸው የህዝብ ቁጣ ለማምለጥ ነበር፡፡ ሩጫቸው ጠንካራ ስራ ሰርተው ከናዳ ለማምለጥ ብቻ ሳይሆን ጭላንጭሉን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ብልጭ ያለውን መድብለ ፓርቲ፣ እየተንገዳገደ ያለውን ነፃ ፕሬስና በጥንካሬ ለሀገራቸው እየሰሩ ያሉ ተቃዋሚዎችን የማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ ሩጫቸው የአንድ ፓርቲን የበላይነት በግድ የማሸከም ነው፡፡ ውድድር የሚባለውን የማጥፋት ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ገዥው ፓርቲ እየተከተለ ያለው አቅጣጫ ጠቅለል ተደርጐ ሲታይ ከላይ ከገለፅናቸው ክብ መስመሮች የሚወጣ አይደለም፡፡ ዋና ግቡም በውድም ሆነ በግድ ጠቅልሎ የመግዛት ነው፡፡
የኢህአዴግን
ባህሪ ጠንቅቀን እናውቃለን የሚሉ ልሂቃን በተደጋጋሚ እንደገለፁት ሲጀመርም ፓርቲው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አልታገለም፤ ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት እንዲረጋገጥ አልታገለም፡፡ የታገለው ለስልጣንና ለስልጣን ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ኢህአዴግና አመራሩ ገና ወደ ስልጣን ሳይመጡ የአልባኒያ ኮሚኒዝም ተከታይና አቀንቃኝ ነበሩ፡፡ በቀላሉ የማይፋቅ የኮሚኒስት አስተሳሰብ ባለቤት የሆኑት የገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት የዓለም ሕዝብ ድጋፉን የቸረው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከጉሮሮአቸው የሚወርድላቸው አልሆነም፡፡ አሁን እያየን ያለነው አፈናም የዚህ ውጤት ነው፡፡
የትግራይን ነፃ ሪፐብሊክ ለመመስረት ተብሎ የተጀመረው ትግል የመሐል አገሩን ማዕከላዊ መንግስት በመቆጣጠር ሲጠናቀቅ “ነፃ አውጭ ነኝ” የሚለው ኢህአዴግ ሁለት መንታ መንገድ ላይ ቆመ፡፡ አንደኛው ሲጠመቁበት የኖሩትን የፈራረሰው የሶቪየት ህብረቱ ሶሻሊዝም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ የበላይነቱን እየተቆናጠጠ ያለው ካፒታሊዝም ነው፡፡
ይሄው
በልዕለ ሃያሏ አሜሪካ የሚመራው ካፒታሊዝም ወደ በትረ ስልጣኑ ለመጣው ነፃ አውጭው ንጉስ ዶላርና አልዋጥላቸው ብሎ እየተናነቃቸው ያለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ሰብዓዊ መብት መጠበቅ የሚሉትን ቀላቅሎ ሰጣቸው፡፡ ስለዚህ የአልባኒያ ኮሚኒዝም ተከታይ የነበሩት ኮሚኒስት ታጋዮች በአንዴ ማልያ ቀየሩና “ዴሞክራት” የሚል አዲስ ማልያ ለበሱ፡፡ ሶሻሊስትነቱ መሳቢያ ውስጥ ተከተተ፡፡ ለይስሙላ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት ለኮፍ፣ ለኮፍ ተደረጉ፡፡
“ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንደሚባለው መሆኑ አልተገለጠለትም እንጅ! “ዴሞክራት” የሚለው ማልያ ለይስሙላ እንደተለበሰ ልብ ያላለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገሩን የምር ዴሞክራሲያዊት ሊያደርግ ተነቃነቀ፡፡ በ1997 ዓ.ም የታየውም ይሄው እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ፍላጐት ነው፡፡ ከላይ እንደገለፅነው “ብትደርሷት አፍንጫችሁን ላሷት! ” የተባለውና ወደ ስውር ዘመቻ የተገባው ሀቀኛ ተቃዋሚዎችና በፅናት እየሰሩ ያሉ አንዳንድ ነፃ ጋዜጦች የገዥው ፓርቲ መደበኛ ጠላት ተደርገው የተወሰዱት፤ ኢህአዴግም አውራ ፓርቲ እንደሆነ የተሰማው ከ1997 በኋላ ነው፡፡ ወደ ድሮው ዘመን የተመለሰውም ከዚሁ ምርጫ በኋላ ነው፡፡ በተለይ ከ97 በኋላ ገዥው ፓርቲ እንደስትራቴጂ እየተከተለ ያለውን ህግ እያጣቀሱ መፈረጅ፤ ነፃ ጋዜጦችን ማጥፋትና ሀቀኛ ተቃዋሚዎች ላይ ስም በመለጠፍ ከህዝብ ለመነጠል የሚያደርገውን ደባ በሀገር ላይ እንደተቃጣ ደባ በመቁጠር እንቃወማለን፡፡
ከምር
ራሱ ኢህአዴግ ለታይታም ቢሆን የሚያነበንበው ህዳሴና መካከለኛ ገቢ ያላትን ኢትዮጵያ እንድናይ ከተፈለገ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ጋዜጦች ላይ የሚያካሂደውን ዘመቻ በማቆም በአስቸኳይ ወደ ውይይት መምጣት ይገባዋል፡፡ ስውርና ግልፅ ዘመቻውንም ማቆም አለበት፡፡ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ ማድረግ ወይም እስር ቤት ማጐር ከጥቅሙ ጉዳቱ የበዛ ነው፡፡ የህዝብን የነፃነት ስሜትም ማፈን አይቻልም፡፡ ትውልድ ካልቆመ በስተቀር ሊዳፈን አይችልም፡፡ ሊቆም ደግሞ አይችልም፡፡ “ሚስማር አናቱን በመቱት ቁጥር ይጠብቃል” እንደሚባለው ስርዓቱ ላይ ጥላቻ ከማትረፉና በደል የሚፈፀምባቸው የበለጠ እንዲበረቱ ከማድረግ ውጭ ጥቅም የለውም፡፡ ለሀገርም አይጠቅምም፡፡
በተለይ
መንግስት በርካታ ሃላፊነቶች ተጭነውበት እያለ በማይጠቅም ግልፅ ዘመቻ ተጠምዶ ሲገኝ ያሳስባል፡፡ ለዚህም አብነት የሚሆነንን ምሳሌ እናንሳ፡፡ በመጀመሪያ የኢህአዴግ የንድፈ ሀሳብ መጽሄት በሆነቸው “አዲስ ራዕይ” ላይ ሊያጠፋቸው የፈለጋቸውን ዜጎች ያሰፍራል፡፡ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በእነ አይጋፎረምና አዲስ ዘመን ላይ በግለሰብ ስም አጥፊና ፈራጅ ፅሁፍ ይቀርባል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ውይይት ሆኖ ይቀርባል፡፡ ማሳረጊያውም “በሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ግለሰቦች በህዝብ ትብብር በቁጥጥር ስር ዋሉ” በሚል የኢቴቪ ዜና ይሆናል፡፡ ድራማው እንደዚህ ነው፡፡ ይሄ በጣም አደገኛና አሳሳቢ አካሄድ በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን፡፡ ይሄን የማሳደድና የማጥፋት ዘመቻ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ከዚህ በፊትም ከላይ በገለፅኩት መንገድ የታሰሩ የፖለቲካ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ ትናንት የበርካታ አንባቢያንን ቀልብ ገዝታ የነበረችው “አዲስ ነገር” ጋዜጣ የተዘጋችውና አዘጋጆችም ለሀገራቸው ብዙ መስራት እየቻሉ የተሰደዱት ከላይ በገለፅነው አይነት ቅንብር ነው፡፡ የአውራምባ ታይምስ አዘጋጅ ከመሰደዱ በፊት በአዲስ ዘመን ገፅ ሦስት ላይ “ይታሰር” የሚል ፅሁፍ ቀርቦበት ነበር፡፡ በኬንያና በሱዳን የተሰደዱ ጋዜጠኞችም በርካታ ናቸው፡፡ ይሄ ለአንድ ገዥ ፓርቲ ምን አይነት እርካታ እንደሚሰጠው ባይገባኝም ዘመቻው አሁንም ቀጥሏል፡፡ ከላይ በገለፅኩት አካሄድ ነጻ ሜዲያ ላይ ዘመቻው ተጧጡፏል፡፡ በመንግስት ጋዜጦች እነዚህ ፅሁፎች በግለሰብ ስም ይውጡ እንጅ ከጀርባ ተቋም እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ያየነው ይሄንን ነው፡፡ ዝም ብሎ ካለቦታው ለማይመለከተው ሁሉ “ሽብርተኛ” የሚል ስም መለጠፉና ማን አለብኝነት የስርዓቱ መገለጫ እየሆነ ነው፡፡ አሁንም ሌሎች ላይ የተከፈተው ዘመቻና ፍረጃ እጅግ ያሳስበናል፡፡ የተነቃበትና የማይጠቅመው የኢህአዴግ ግልፅ ዘመቻ ሊገታ ይገባዋል፡፡
ከመሬት
እየተነሱ “ሽብርተኛ! ሽብርተኛ” እያሉ ለስልጣን ያሰጉኛል የሚሉት ላይ ሁሉ ጣትን መጠቆም መዘዙ ለራስም ሊተርፍ ይችላል፡፡ የህዝብ ብሶት መፈንጃ ምክንያቱ አይታወቅም፡፡ ለሌሎች በቆፈሩት ጉድጓድ ማን እንደሚገባ አይታወቅምና፡፡
No comments:
Post a Comment