Friday, June 28, 2013

የሚመሩትን ሕዝብ የሚፈሩ መሪዎች

የሚመሩትን ሕዝብ የሚፈሩ መሪዎች

        ዛሬ ካለው የአለማችን ተጨባጭ ሁኔታ የየትኛውም አገር መሪዎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የሚደረገው ጥበቃ እጅግ የጠነከረ ነው፡፡ ተራ ሰው በነበሩ ጊዜ እንዳሻቸው በህዝብ መሀከል የሚንቀሳቀሱ ሁሉ የሥልጣን ማማው ላይ ሲወጡ ዙሪያገባቸው በጦር መሣሪያ ይከበባል፡፡ በሚያልፉባቸው መንገዶች ወፍ እንኳን ዝር አትልም፡፡ በተለይ በሚመሩት ህዝብ የሚጠሉ መሪዎች ከሆኑማ ሽርጉዱ አይጣል ነው፡፡ ጠባቂዎቻቸው መርዝ እንደበላች ውሻ ሲክለፈለጉ ይታያል፡፡ በእርግጥ በህዝባቸው ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ዴሞክራት መሪዎች እንደልብ መንቀሳቀስ ቢችሉም ለደህንነታቸውና ለአገሪቱ ክብር ሲባል ተገቢው ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ የሚደረግላቸው ጥበቃ ግን የህዝብን የየዕለት ኑሮ የሚያስተጓጉልና በሽብር የሚንጥ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ራሱ በነፃነት የመረጣቸው በመሆኑ የሚመሩትን ሕዝብ አይፈሩም፡፡
           የሚመሩትን ሕዝብ የሚፈሩ መሪዎች ግን ዕድሜ ልካቸውን በሥጋት ይኖራሉ፡፡ ለህዝብ የመጡ ሳይሆኑ በህዝብ ላይ የወጡ አምባገነኖች ናቸው፡፡ ዜጎች አይደለም በአካል ሊያዩዋቸው ድምፃቸውን እንኳን መስማት አይፈልጉም፡፡ በተለይም 21ኛው ክፍለ ዘመን የአፍሪካ መርገም ሆነው የተነሱት መሪዎች በሚመሩት ህዝብ ዘንድ የማይታመኑና እነሱም የሚመሩትን ህዝብ የማያምኑ ህዝባቸውን በዴሞክራሲና በፍቅር ሳይሆን በጠብመንጃ አፈሙዝ መግዛት የሚቀናቸው ናቸው፡፡ ለዜጎች ህይወት ግድ የላቸውም፡፡ ደም በማፍሰስና በማፋሰስ ይረካሉ፡፡ የሕዝቦቻቸው መጎሳቆል ጉዳያቸው አይደለም፡፡
     አገራችን ኢትዮጵያ የዚህ እኩይ ዕጣ ፈንታ ተጋሪ ናት፡፡ በየዘመናቱ የተነሱት መሪዎቿ በጠብመንጃ እንጂ፣ መቼም ቢሆን በህዝብ ድምጽ ተመርጠው ሥልጣን ላይ አልወጡም ፡፡ ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ አልታደልንም፡፡ ዛሬም የምዕራቡን ዓለም ዴሞክራሲ ለመቀላወጥ ተገደናል፡፡ ያለፈውም ሆነ የዛሬው ትውልድ በመሪዎቹ ላይ እንዳቄመ፣ መሪዎቹም በህዝቡ መሀከል በነፃነት ለመንቀሳቀስ እንደሰጉ እስከ የት እንደምን ዘልቅ ግራ ቢያጋባም የነፃነት መሻታችንን እውን ለማድረግ በጽናት መታገልን ይጠይቀናል፡፡

       አቶ መለስ99.6% ህዝብ መርጦናልቢሉም ሕዝብ ወድዶ እንደመረጠው መሪ በህዝብ መሀከል ለደቂቃ እንኳን ለመንቀሳቀስ አይደፍሩም፡፡ ከቤተመንግስት ወጥተው እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ ድፍረቱም ሆነ ሞራሉ የላቸውም፡፡ የወያኔ መሪዎች ከአገር ሲወጡም ሆነ አዲስ አበባ ውስጥ ለሥራ ጉዳይ ሲንቀሳቀሱ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ይናወጣሉ፡፡ የፖሊስ ሞተሮችና መኪናዎች አዲስ አበባን በጡሩምባ ጩኽት ያተራምሷታል፡፡ የፌደራል ፖሊሶች አገር አማን ነው ብለው የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን እያዋከቡ በየሥርቻው ሲወሸቁ አሊያም ከአስፋልቱ ርቀው ፊታቸውን እንዲያዞሩ ሲያስገድዱ ይስተዋላል፡፡ ላለፉት 22 ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ በተለይም ከቤተ መንግስት እስከ ቦሌ አየር መንገድ የሚንቀሳቀሱ ዜጎችና አሽከርካሪዎች ይህንን ሰላማዊ መሰል ሽብር በማስተናገድ ተሰላችተዋል፡፡

No comments: