እድለኛ ትውልድ ወይስ እድለኛ መንግስት
’’A good news is not a news at
all’’
(ጥሩ ዜና፣ዜና አይባልም) የሚለው የፈረንጆቹ ሚዲያ ባህል በኢቴቪ ቦታ የለውም:: በአንፃሩ ’’A true news is not a news at all’’(እውነተኛ ዜና፣ዜና አይባልም) የጣቢያው መሪ ቃል ይመስላል:: ዜናውም፣ ፕሮግራሙም፣ዶክመንተሪውም፣ መዝናኛውም፣ የልጆች ጊዜ ፕሮግራሙ ሳይቀር በአጠቃላይ ሁሉም ‹አደገ›፣ ‹ተወደሰ›፣ ‹ተደነቀ›፣‹ተመረቀ›፣ ‹እየጨመረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው› በሚሉ ቃላት የተሞላ ነው:: ምን አልባት በልማታዊ ሚዲያ እና በኒዮ/ሊበራሊስት ሚዲያ ያለው አንድ ልዩነት ይህ ይሆናል::
በዚህ ወር ውስጥ ልማታዊው ኢቴቪ “በኢትዮጵያ ያለው የሀብት ክፍፍል ፍትሀዊ ነው” ብሎ ዘገበ:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ባለፈው ሪፖርታቸው ያስተዋወቋትን ’’Gini Coffecient’’
የምትል የኢኮኖሚክስ ቃል በማብራራት ልማታዊዎቹ ተጠምደው ሰነበቱ::እኔም የገባኝን ያህል ገብቶኝ ይሁን ብዬ ተቀበልኩ:: ደግሞ ቀጥለው የስራ አጡ ቁጥር ቀነሰ ብለው በፐርሰንት አስቀመጡ:: ‹ጎሽ ተመስገን ነው› ብዬ ዘገባውን በልማታዊ እይታ ተቀብዬ ሲቪዬን ወደ ማሻሻል ገባሁ:: የተረጂዎች ቁጥር መቀነሱንም አብስሮን ነበር:: ለመምህሩም አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ የሚያስችል የደሞዝ ጭማሪ መደረጉንም በጥርጣሬም ቢሆን ተቀበልኩ::(ይህ ዜና ገጠር ያስተምር የነበረውን እና ከሊቢያዊው ቡአዚዝ በፊት በችግር ምክነያት ራሱን ያጠፈው መምህር ጓደኛዬን አስታወሰኝ:: የአካባቢው ገበሬዎች ማታ ማታ ቢራ ሲጠጡ ‹ምን በወጣን በአረቄ እንቃጠል?እንኳን እኛ መምህሩ ቢራ እየጠጣ› ይሉ እንደነበር አጫውቶኝ ነበር:: አይ ትንሽ ብትታገስ ጭማሪውን ታይ ነበር!) እነዚህን መሰል ብዙ ብዙ ልማታዊ ዜናዎችን እና ዶክመንተሪዎች ዝም በዬ፤ ብሶቴን ዋጥ አድርጌ ተከታትዬ አውቃለሁ:: አሁን ግን የተቀበረ እና የተዳፈነ ብሶቴን የሚኮረኩር ዘገባ ሊተላለፍ ሆነ:: “እድለኛ ትውልድ” ይላል ርዕሱ:: በእውነቱ ይህንን ፕሮግራም የሚከታተል የመንፈስ ጥንካሬ ስላልነበረኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ቴቪውን ዘግቼ ውስጤ የመጣውን ሀሳብ መጫር ጀመርኩኝ:: በህዝብ ጥያቄ ወይም ደግሞ በበረከት አዛዥነት ፕሮግራሙ ሲደገም ልማታዊው መንፈስ ወደ እኔ ከመጣ ያኔ አየው ይሆናል::
‹እድለኛ ትውልድ› ወይስ ‹እድለኛ መንግስት› ለመሆኑ የትኛው ትውልድ ነው እድለኛ? ምንስ አግኝቶ? ያገኘው/የሚያገኘው ነዋይ በምን ተለክቶ ነው እድለኛ ለመባል የበቃው? አባይ እስኪገነባ ድረስ እድለኛ አልነበረም ማለት ነው? እነዚህ እና ሌሎች መላሽም ሆነ ምላሽ የሌላቸው ጥያቄዎች አሉኝ:: የ28 አመት ሰው ነኝ:: ወጣት ነኝ አላልኩም:: ምክነያቱም የቱንም ያህል በጎ አሳቢ (optimist)
ለመሆን ብጥርም ከፊት ለፊቴ ተስፋ አልታይህ አለኝ:: እዚህ ወርቃማ ዕድሜ ላይ ስደርስም ከኋላዬ ምንም አስደሳች ነገር የለኝምና ሽማግሌም አልባል:: እንግዲህ እንደ እኔ ያለውን ግራ የገባውን ትውልድ የነእንትና ሎሌ ኢቴቪ ‹እድለኛ› እያለ ያሞኘዋል:: በጫት ሱስ አዕምሮው የሚያደነዝዘውን ትውልድ፣ ስደትን ብቸኛ አማራጭ ያደረገውን ትውልድ፣ ሀሳቡን በነፃነት ያለፍርሀት መግለፅ የሚያስፈራውን ትውልድ፡፡‹እድለኛ› አሉት! ተምሮ ተመርቆ ስራ አጥቶ የሚባዝን ‹እድለኛ› ትውልድ! የራሱን ስራ ለመጀመር ተደራጅቶ እና መንገድም ህይወትም ኢህአዲግ ነው ካላለ በስተቀር ዳገት የሚሆንበት ‹እድለኛ› ትውልድ! ራሱን በሳይኮሎጂ መፅሀፎች እና በፊልም ደብቆ የሚፈላሰፍ ‹እድለኛ› ትውልድ! በፌስ ቡክ እና በኳስ የተለከፈ ‹እድለኛ› ትውልድ! ሀገሬ ደስ ይበልሽ፤በ‹እድለኛ ልጆችሽ›!
ግን
ሀገሬ ደስ አይበልሽ፤ በ‹እድለኛው መንግስትሽ› አዎ እውነተኛ እድለኛው የኢህአዲግ መንግስት ነው:: በጣም እድለኛው ደግሞ መለስ! በእድለቢስ ትውልድ መሀከል፣ በራበው ህዝብ መሀከል፣ መልካም አስተዳደር እና ፍትህ ባጣው ህዝብ መሀከል ለ20 አመታት የነገሱት መለስ እንዴት እድለኛ አይባሉም? ኢትዮጲያዊ ወኔያችን ተሰልቦ፤ አንድ መሆን አቅቶን ለየብቻችን በየጓዳችን ብሶታችንን ስንጮህ፤ ከሁሉም በላይ የሰማዩ አምላክ ፍርዱን ሲያዘገየው እውነት ሎተሪው ለዛውም አንደኛው እጣ ማነው የወጣለት? የመለስ መንግስት ወይስ የኢትዮጵያ ወጣት?
የአባይ
ግድብ ለዚህ ትውልድ ምኑ ነው? እድለኞቹ መቼም በዚች አርዕስት አንቀፅ ቆጥረው፤ አዋጅ አገላብጠው (ከሌለም በአንድ ሌሊት ፈጥረው) በፀረ ልማታዊነት እንደማይከሱኝ አምናለሁ:: ለኢትዮጵያ አላልኩም፤ ለዚህ ትውልድ ነው ያልኩት:: ወንዙማ እንኳን ተገድቦ እና 6000 ሜጋ ዋት ኃይል አመንጭቶ ይቅርና እየፈሰሰም ክብሯ ነበር:: ግን እውነት የአባይ ግድብ ለዚህ ትውልድ ምን ትርጉም ይሰጣል? እድለኞቹ፤ አደራ ‘ምን ጥቅም’ ይሰጣል ብላችሁ እንዳታነቡት:: እውነት ግድቡ በዚህ ትውልድ ጊዜ ተገነባ እንጂ በዚህ ትውልድ አቅም ተገነባ? እስኪ ተመልከቱት፡፡ በአመት ውስጥ ተዋጣ ከተባለው ሰባት ቢሊዮን ብር አብዛኛውን ድርሻ ያዋጣው አሁንም የአባቶቻችን ትውልድ ነው:: የስራ አጥ ቁጥሩ ወደ 48% በተጠጋበት ጊዜ በስራው አለም የሚገኘው ‹ያ ትውልድ› ነው:: ያ ትውልድ ለራሱ ቦንድ ገዛ፣በልጆቹ ስም, በትምህርት ቤት ገዛ፣ በእድር አዋጣ፣ በቀበሌ አዋጣ:: እሱም ቢሆን ያለፍላጎቱ:: ወጣቱማ ስራ የለውም:: ስራ ፈጥሮ ልስራ ቢል እንኳ ቢሮክራሲው እና ሙስናው መች አላውሶት? ድሮስ እድለኛ ትውልድ አይደል?
ደግሞም
የተቀረው ወጣት አለ:: ስደትን የመረጠው:: ኢቴቪ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይን ጠቅሶ ባስተላለፈው ዜና ባለፉት 6 ወራት በህጋዊ መንገድ ወደ አረብ አገራት የሄዱት እህቶቻችን ቁጥር ሰማኒያ አምስት ሺህ ነው ብሎናል:: ቦንድ ሳይገዙ ማለት እኮ ነው የሄዱት! ለአባይዬ ሳያዋጡ! በህገወጥ መንገድ ከችግሩ ብዛት የተነሳ አባይን የሚያቋርጡትም ቢሆኑ ነፍሳቻውን እንጂ ሳንቲማቸውን ለአባይ አይለግሱም:: ‹የእከሌ ጫት ቤት እንዲሁም የማንትስ ሺሻ ቤት ከደንበኞቻቸው (ከወጣቱ) በሰበሰቡት ገንዘብ ይህን ያህል ቦንድ› ገዙ ሲባልም አልሰማን::
ታዲያ እውነት ግድቡ በዚህ ትውልድ ይገነባል ማለት ይቻላል?ወጣቱማ ሀገራዊ ስሜቱን ተነጥቆ የእድለኞቹን ዜማ እንዲያቀነቅን ተፈርዶበታል:: እስኪ ልብ ብላችሁ በወጣት እድለኞቹ የሚቀነቀነውን ዜማ አስተውሉ:: ‹በእኔ ግዜ አባይ በመገንባቱ እድለኛ ነ›፤‹ይህ ትውልድ የቁጭት ትውልድ ነው›፤ ‹በራሳችን አቅም ለመገንባት በመነሳታችን ልዩ ታሪክ ነው›፤ ‹የእኛስ ትውልድ መቼ ነው ታሪክ የሚሰራው፤ በአክሱም እና ላሊበላ እስከመቼ እንኮራለን እያልኩ ሁሌ አስብ እና እቆጭ ነበር› አላወቅሽ የአክሱም ታሪክ ሌላው እንዳይኮራበት ለአክሱማውያኑ ብቻ እንደተሰጠ! በጣም የሚያሳዝነው ይህ ዜማ ወደ ህፃናቶቹም መጋባቱ ነው:: ‹ዋናው ነገር አባይ ተገንብቶ ውሀ ስለያዘ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከድህነት አላቆ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት በአጭር ጊዜ ለማሰለፍ…..›ድሮስ ካድሬ ቄስ አጥምቋቸው፤ ምንአላባትም ካድሬ መምህር አስተምሯቸው የልጅነት ለዛቸው ‹ወያኔያዊ› ዜማ ቢኖረው ምን ይገርማል?
እውነት
የእድለኞቹ ዘፈን እንደሚለው ይህ ትውልድ የራሱን ታሪክ ሰራ? አባት እናቱ ከደሞዛቸው ተነጥቀው፤ ጥቂት ባለሀብቶች በተለያዩ ድርጅቶቻቸው ስም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለመቸር በተፎካከሩበት ሁኔታ ይህ ግድብ በዚህ ትውልድ ጊዜ እንጂ በዚህ ትውልድ ተሰራ ለማለት አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው:: አለበለዚያ ልክ እንደ ወጪ መጋራት እዳችን ቦንዱ ይገዛልን እና የታሪኩ አካል የምንሆንበትን ሁኔታ መንግስት ያመቻችልን:: የዛኔ ወጉ ደርሶን ‹ታሪክ የሰራ ትውልድ› እንባላለን:: የዛኔ ምንም እንኳ በዱቤ ቢሆን
የገዛነው ‹እድለኛ› የሚለው ቃል ይገባን ይሆናል:: ቢያንስ እንደ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብቶቹ በሙስና ከተገኘው ሀብት አይደለም የምንሰጠው:: ወይም እንደ ልማታዊዎቹ ከተረፈው ሀብታችን አይደለም የምንለግሰው:: አባይ ተገድቦ ኃይል ሲያመነጭ፤ ሀገራችን በፋብሪካ ስትሞላ፤ የስራ እድል ሲከፈትልን፤ ከሙስና የፀዳች ሀገር ስትኖረን፤ መልካም አስተዳደር እና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ሲኖር፤ ከሁሉም በላይ አሳታፊ
እና ዲሞክራሲያዊ መንግስት ሲፈጠር ከምናገኘው ገቢ የዛሬ ምናምን አመት እዳችንን እንከፍለዋለን::ይህ እስኪሆን ድረስ ግን የተሰደዳችሁት ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቼ፣ በሱስ ውስጥ ያላችሁት ወዳጆቼ እንዲሁም የራስህን ህይወት ያጠፋኸው ጓደኛዬ ቴዲ በእርግጥም እድለኞች ናችሁ! ምክነያቱም የአቶ መለስን ‹እድለኛ ትውልድ› የሚለውን ስድብ እና ፌዝ ከመስማት አምልጣችኋና::
No comments:
Post a Comment