Saturday, June 15, 2013

ሀገሪቷን ለመምራት ስልጣን ብቻ በቂ አይደለም።

              ሀገሪቷን ለመምራት ስልጣን ብቻ በቂ አይደለም።
          ኢህአዴግ መራሹ መንግስትም ስርዓት ለውጦ ሲመጣ ካለፉት ስርዓቶች የተሻለና የተለየ ነገር ይዞ ይመጣል የሚል ጭላንጭል ተስፋ ነበረን። በንጉሱና በወታደሩ የአገዛዝ ዘመን የታዩት የፖለቲካ ህመሞች እንደማይደገሙ ቃል ተገብቶም ነበር። የሆኖ ሆኖ ብዙም ሳይቆይ ችግሮቹ አንድ በአንድ ወደ መድረክ ተመለሱ እንጂ። ረሀብ፣ መከራና ጦርነት ቦታቸውን መልሰው ያዙ። በተለይ ቀድሞውኑም የገደዱት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅፋቶች በመባባሳቸው ህዝቡን ለከፍተኛ የኑሮ ቀውስና በሀገሩም ጉዳይ ‹›አለሁኝ›› ለማለት እንዲሰጋ አስገደዱት። የአብዛኛውም እጣ ፈንታ መሰደድ ሆነ።በሀገሬ አጣሁት ያለውን ነፃነት ለማስመለስና ገፋኝ ያለውን ስርዓት ለማጋለጥ ይመቸኛል ያለውን ከባቢም አመቻቸ።
          ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ሰርቶ፣ ከብሮና በማንነቱ ኮርቶ ለመኖር የተረጋጋና ሰላማዊ የፖለቲካ ስርዓት ያስፈልጋል፡፡ ግጭትና መቆራቆዝ የተጠናወተውን ፖለቲካችንን ከውጪ ሆኖ ለመመልከት ግድ የሆነበት የሚፈልገውን በማጣቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጋራ ንብረታችን ናት። የኛም፣ የወያኔዎችም የተቃዋሚዎችም፣ የዲያስፖራውም የሁሉም። ይህንን ደግሞ ማንም ሊሰጥና ሊነፍግ መብቱ አይደለም። በገዢው መንግስትና በውጭ ሀገራት በሚገኙ ተቃዋሚዎች መካከል የሚፈጠሩ ልዩነቶች መነሻቸው ይህችን ሀገር እኔ ባስተዳድራት ከአንተ የተሻለ ለውጥ አመጣለሁ በሚል ነው። ህዝቡ ካለበት አረንቋ ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት የእኔ መንገድ ያዋጣል ነው የውዝግቡ አንኳር፡፡ ይህ ደግሞ የሀሳብና የአስተሳሰብ ልዩነት ነው። የልዩነቱ መፍትሄም ራሱ ሀሳብ ነው። ወይ አድነኝ ወይም ላድንህ፤ ወይ አርመኝ ወይም ላርምህ ለመባባል የሶስተኛ ወገን ገላጋይነት አያስፈልግም፡፡ የችግሩ ባለቤቶች በቂ ናቸው፡፡ ታሪካችን እንደሚያስተምረን ከሆነ የፅንፈኝነት ውጤቱ የህዝብ ስደትና የሀገር ሰላም አለመረጋጋት ነው፡፡ ዛሬ ሰልጥነዋል የምንላቸው ሀገራትም በሁለት ባላንጣዎች መካከል የሚነሱ ችግሮችን አንዱ አንዱን በማሳደድ ሳይሆን በመግባባትና አማራጭ መፍትሄዎችን በመፈለግ ጉዳዩን ያጠናቅቁታል።
          ይህ የሰለጠነ ባህል ለዚህች ምስኪን ሀገርም እንደሚያስፈልጋት በፅኑ ምናለ ለዚህም መንግስት የመሪነቱን ቦታ ወስዶ በሀሳብና በእውቀት ላይ መሰረት ያደረጉ ትችቶችን ለመቀበል ትከሻውን ማስፋት ይጠበቅበታል። እውነት እኔ ጋር ብቻ ነች በማለት ሌሎችን መግፋት ወያኔ እየገነባሁት ነው ከሚለው የዴሞክራሲ መንገድ አንፃር ስህተት መሆኑን ለመናገር ምስክር መጥራት አያስፈልግም። ሀገሪቷን ለመምራት ስልጣን ብቻ በቂ አይደለም። ጉልበትም በቂ አይደለም፡፡ኃላፊነትም ጭምር እንጂ፡፡ ሀሳ በነፃነት ለመግለፅ የሚያስችል ሰላም ዲሞክራሲ እና ከዘረኝነት የጸዳ  መንግስት ያስፈልጋል ብዬ እናምናለን።


ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!




No comments: