Monday, June 10, 2013

ማስተዋል የተሞላበት የለውጥ ተሳትፎ ግድ ይላል !

ማስተዋል የተሞላበት የለውጥ ተሳትፎ ግድ ይላል !
ከፍጹም መንገሻ _ኖርዌይ
አገራችን ኢትዮጵያ በአጼ ሃይለስላሴ ጨቋኝ የፊውዳል አገዛዝ ቀጥሎም በአረመኔያዊ የደርግ ስርዓት አሁን ደግሞ ዘረኛ በሆነ የወያኔ ስርዓት አስከፊና እሬት እሬት የሚያሰኝ ጊዜያትን አሳልፋለች አልፎም የህዝቧን አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ የጣለ እና ጥያቄ ውስጥ የከተተ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች ። ህዝቧም በየሰርዓቱ የጠየቀውን የዲሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ሳይመለስለት ይልቁንም በዲሞክራሲ እና በፍትህ ስም እየገቡ ለባሰ ስቃይ እና አደጋ እየዳረጉት ረዘም ያለ ዘመናትን አሳልፏል።
አሁን ያለንበትን ጊዜ ካለፉት የመንግስት ለውጦች ተነስተን ስናየው ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ ያለውን አስከፊ እና ዘረኛ ስርዓት ገርስሳ ወደ ሚቀጥለው የስርዓት ለውጥ ለመሸጋገር ከጫፍ የደረሰችበት ጊዜ ላይ እንደደረሰች የሚያመላክቱ ነገሮች ይታያሉ። እዚህ ላይ ጊዜ የማይሰጠው ነገር ዘረኛውን ስርዓት ማስወገዱ ሆኖ ሳለ ከባለፉት ከድጡ ወደ ማጡ ለውጦች በመነሳት ደግሞ ወደ ተለመደው አስከፊ የስርአት ለውጥ እንዳንገባ ልብ ልንል ይገባል ።ይህን ለማድረግ ደግሞ የኛ የልጆቿ ብስለት እና አርቆ አሳቢነት ቁርጠኛነት አብሮነት እንዲሁም መስዋእትነት ከመቼውም በበለጠ አስፈላጊ እና ግዴታችን ሆኖ እናገኘዋለን ። እነዚህ ነገሮች በሌሉበት ሁኔታ ግን የወደፊቷን ኢትዮጲያ አቅጣጫ ለመወሰን አዳጋች ይሆናል። ይልቁንም በ1993ዓም በወያኔ መሰንጠቅ እንዲሁም በ1997ዓም የምርጫ ሽንፈት ተንገዳግዶ የተነሳው ዘረኛው ወያኔ አሁንም እንዳያንሰራራ ልንሰጋ ይገባል። አሁን ካለው ሁኔታ የሚያገግምበት ነገር ባይታይም።
በመጨረሻ ዘመን እኔ እየሱስ ነኝ የሚል እንደሚመጣ ሁሉ በእንደዚህ አይነት የለውጥ ጊዜያትም እኔ ነኝ የማውቅልህ ባዩ መብዛቱን እና በአንደበቱ አሳምኖ እኩይ ስራውን እስካሁን እንዳሳለፍነው ዘመን እንዳይተገብርብን በማስተዋል መጓዝ የኛው የኢትዮጲያውያን ሃላፊነት ይሆናል ።በተለይም በአሁኑ ሰዓት በሃገራችን የወደፊት ሁኔታ ላይ ለመወሰን ማስተዋልን በተሞላ ሁኔታ በተግባር መሳተፍ ግዴታችን ይሆናል። ይህም ከወደፊት ጸጸት እና ቁጭት ሊያድነን ይችላል ።
በዚህ ጊዜ በተግባር አደሚታየው በግለሰብ ደረጃም ሆነ በተቃዋሚ ደረጃ ካለነሱ አዋቂ የሌለ አስከሚመስል እና ትግሉ ልክ ዛሬ የተጀመረ አስከሚመስል ድረስ የሚሰሙት ነገሮች መጨመር ጀምረዋል ። ወደ መንግስት ፊታቸውን አዙረው የነበሩትም አንደማያዋጣ ሲያውቁ ወደ ህዝብ ፊታቸውን የመለሱ አስመስለዋል። ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ..............
ታዲያ በዚህ ወቅት በተለያዩ አስከፊ ስርዓቶች ግራ የተጋባው እና ትግስቱ ያለቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ነገሮችን መርምሮ እና ወደ ውስጥ ገብቶ ካላስተዋለ ምን አልባትም የእናታችን የኢትዮጲያን ዋይዋይታ አንዳናረዝመው እና ለረጅም ዘመናት አኩልነት እና ነጻነት የናፈቀውን ህዝብ መልሰን ወደ ማጡ አንዳናስገባው ሃላፊነቱ አሁንም የኛው የራሳችን መሆኑ መረሳት የሌለበት ተግባር ነው።
ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ሰአት በጣም አስፈላጊ ሆኖ ከሚታዩት ነገሮች አንዱ መደራጀት አንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም ። ታዲያ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ከማን ጋር ነው የምንደራጀው ? ማን ነው የሚያደራጀን ? ብሎ ማሰብ እና ለመደራጀት ያሰቡትን ድርጅት መመርመሩ ተገቢ ነው ። ለዚህ ያሰቡትን ድርጅት አላማ ማወቅ ብቻ ሳይሆን አፈጻጸሙን ጉዞውን? ለምን ?በማን? የመሳሰሉትን ጠለቅ ብሎ ማስተዋሉ ከወደፊት ጸጸት እና ተጠያቂነት ሊያድነን ይችላል ። አንዲሁም የወደፊቷን ኢትዮጵያ አቅጣጫ አብሮ በመወሰን ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ይህ ጊዜ በተመረጡ ንግግሮች እና በመሳሰሉ ነገሮች ብቻ የምንሳብበት ጊዜ ሊሆን አይገባም። ልብ ይበሉ ህዝብን በጣም በመናቅ የሚታወቀው ዘረኛው ወያኔ እንኳን መንግስት ሲሆን ከገጠር ድረስ በመግባት አለሁልህ ብሎ በተቃራኒው አንዳስለቀሰው እና እንዳሰቃየው ሁሉ አሁንም አለሁልህ በሚመስሉ ቋንቋዎች ብቻ መሳብ የለብንም። ማንም እኩይ ተግባሩን እንደማይነግረን ሁሉ በቃላት ጨዋታ ፈጽሞ ልንሰናከልም አይገባም።
ሃገራችን ኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን የሚያከብር እና የሚያስከብር ፣ ለሁሉም ዜጎችዋ እኩልነት የሚቆም ፣አንድነቷን እና ሉአላዊነቷን የሚያስጠብቅ፣ ለእያንዳንዱ ልጆችዋ የግለሰብ መብት የቆመ፣ በህዝብ የተመረጠ ስልጣንን የሚያስከብር ፣የእምነት ነጻነትን የሚያሰፍን ስርዓት ናፍቃለች! ትሻለች !
እርግጥ ነው ለነዚህ ነገሮች በጽናት የቆመስርዓት ያሻታል ። እኛ ውድ ልጆችዋ ይህንን ለውዲቷ ሃገራችን ለማበርከት እስከዛሬ በተለይም በአስራዘጠኝ ስድሳዎቹ መጨረሻ በፍጹም የሃገር ፍቅር ለሃገራቸው የተሰዉትን ሞዴላችን በማድረግ እና ይሕንን ዓላማ በጽናት ይዘው ከቆዩት ጎን በመቆም እንባዋን ማበስ ይጠበቅብናል። ይህንን ካላደረግን ደግሞ መቅሰፍቱ ለእኛ ለልጆችዋ መሆኑን ታሳቢ አድርገን በዚህ ጊዜ በማስተዋል በተግባር ለለውጥ አንሳተፍ ። ከነፈሰው ጋር አንዳንነፍስ አንጠንቀቅ ።
ዋናው እና ሊተኮርበት የሚገባው በዚህ ወቅት የእያንዳንዳችን ተሳትፎ በነገዋ ኢትዮጵያ አቅጣጫ ላይ ተጽዕኖ አንደሚያሳድር አውቀን ለውጥ አንደናፈቅን ሁሉ በተግባር እና በማስተዋል እንሳተፍ ። እየወደቀ ያለውን አስከፊ እና ዘረኛ ስርአት እስከ መጨረሻው ለመጣል ህብረታችን ይጨምር ። አካሄዳችንን ሁሉ በማስተዋል አድርገን ሁላችንም ለሃገራችንን አለሁልሽ እንበላት። ይህንን አስካደረግን ድረስ ከዘረኛው የወያኔ አገዛዝ መላቀቅ ብቻ ሳይሆን የወደፊትዋን ኢትዮጵያ ህልውና አስተማማኝ ልናደርገው አንችላለን ።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
fitsumethio122@gmail.com

No comments: