Tuesday, June 25, 2013

የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና የኢህአዴግ እድሜ ማሳጠሪያዎች

የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና የኢህአዴግ እድሜ ማሳጠሪያዎች

        የሕዝብን ዝምታ ከፍርሃት መቁጠር ነው፡፡ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝምታ ሊፈራው ይገባል፡፡ ሕዝቡ በተፈጥሮው ቻይ፣ በባህርይው ታጋሽ በሕልውናውም ከመጡበት እንደ አራስ ነብር ቁጡ ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ ፍቅር ሰጥቶ መብቱን መጠብቅ፣ ማስተዳደርና ማስተዋልን ይጠይቃል፡፡ ባለፉት መንግሥታት የተፈጠሩ የታሪክ ስህተቶችን ላለመድገም ከታሪክ መማር ብልህነት ነው፡፡ ለገዢዎቻችንም ደጋግመን የምንወተውተው ይህንን ነው፡፡ የህዝብን ድምፅ ሰሙ፣ ብሶቱን ተባሱ፣ ቀርባችሁ ችግሩን ተረዱ ነው የዘወትር ጩኽታችን፡፡ ሕዝብን በመናቅ የራስን አገዛዝ ዘመን ለማራዘም የሚደረገው ሩጫ ውሎ አድሮ መሪዎችን የከፋ አደጋ ላይ እንደሚጥልና አገርንም እንደሚጎዳ ከግብፅና ከሊቢያ ክስተቶች ልንማር ይገባል፡፡
   አንድ በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት በህዝብ ዘንድ እንዳይጠላ ካልተጠነቀቀመካሪ የሌለው ንጉስ . . .” እንዲሉ እድሜው ያጥራል፡፡ የህዝብን የልብ ትርታ በማዳመጥ የሚጠላውን የአገዛዝ አካሄድ ማሻሻል ተገቢነቱ አያጠራጥርም፡፡ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ኢህአዴግ በህዝብ ጫንቃ ላይ የሚያሳርፈው ጫና ከአመት አመት እየከበደ መጥቷል፡፡ ቅድመ 97 ምርጫ በነበሩት የኢህአዴግ አገዛዝ አመታት ሕዝቡ በደሉን በውስጡ አምቆ፣ ስሜቱን በምርጫ ካርድ (በድምፁ) ብቻ መግለፁ ለገዢዎቻችን የማንቂያ ደወል ይመስለኛል፡፡ በዚያን ዓመት ነበር ኢህአዴግ ያበቃለት፤ በአገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ የሰፈነ ቢሆን ኖሮ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሲደረግ ለማየት የታደልን 21ኛው /ዘመን ኢትዮጵያዊ ትውልድ እንሆን ነበር፡፡ የኢህአዴግ መሪዎችም ስማቸውና ግብራቸው ከመቃብር በላይ ሲዘከር ይኖር ነበር፡፡ ግና አልሆነም፡፡የሕይወት መስዋዕትነትን ከፍለን ያገኘነውን ሥልጣን በብጣሽ የምርጫ ወረቀት አንሰጥምበሚል አምባገነን አስተሳሰብ የህዝብ ድምፅ በአደባባይ ተሻረ፡፡
       ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛልእንዲሉ በምርጫ 97 ሕዝቡ በቅንጅት ማኒፌስቶና የምርጫ ቅስቀሳ ለምን እንደተማረከ መማር ለኢህአዴግ ይጠቅመው ነበር፡፡ የራሱንም ጓዳ እየፈተሸ ያሉበትን ችግሮች ግን መንቀስ አልቻለም፡፡ ዛሬም ከህዝብ ጋር የሚያቃቅረውን ፖሊሲ እየነደፈና የዴሞክራሲን ጭላንጭል በፅልመት እየጋረደ ራሱን ለአውራ ፓርቲነት ማብቃቱየውሃ ጠብታ አለትን ትሰረሰራለችእንዲሉ የኋላ ኋላ እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ብሶት ለመመለስ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
          ምርጫ ሲደርስ ኢህአዴግ እንደ እድር ነጋሪ በየሰፈሩ በሚያሰማራቸው ካድሬዎቹ (ዘመናዊ ቆራሌዎች) አማካኝነት ሕዝብን በአንቀልባ ለማዘል ይዳዳዋል፡፡ የጨረቃ ቤት የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሕገወጥ ግንባታዎች ሕጋዊ እንደሚሆኑና እንደሚፀድቁ ይለፍፋል፡፡ ወጣቶችና ሴቶች በጥቃቅን አነስተኛ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ይደረጋል፡፡ በየመስሪያ ቤቱ ህዝብ ለአቤቱታ ከመጣ ጉብ (ቂጥጥ) እየተባለ ይስተናገዳል፡፡ ብቻ ምኑ ቅጡ! ይሄ ሁሉ መራጩ ህዝብ ካርዱን እንዳይነፍገው ለመሸነጋገል ነው፡፡ የዶሮ ማታው አይነት የኮሶ ማጠጫ የማይተገበር ቃል ኪዳን፡፡ ምርጫው እንዳለፈ አፍንጫችሁ ላሱ ይላል፤ ከዚህ በኋላ፡፡ ካቢኔዎቹ አካፋና ዲጂኖ ያነገቡ ወዛደሮችን ከኋላ አስከትለው ሕዝቡ በችግር እየተጠበሰ የቀለሳትን ጎጆ በጠራራ ፀሐይ ይንዷታል፡፡ ያደራጃቸው ማህበራት በችግር ሲቆላለፉ እያየ ፊቱን ያዙራል፡፡ በየመስሪያ ቤቱ የሚስተዋለው ቢሮክራሲ ጭራሽ ብሶበት ሕዝብ ሲጉላላና ሲያጉረመርም ይታያል፡፡ ይህን ጊዜ ሕዝብ ቂም ያረግዛል፣ ጥርሱን ይነክሳል፡፡አይነጋ መሰሏት ...”እያለ ይዝታል፤ በቀጣዩ ምርጫ ካርድ በመንፈግ ሊበቀለው አያስብም ማለት የዋህነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዴሞክራሲ ባልሰፈነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ተቀናቃኞች በምርጫ አሸንፈው ስልጣን ለመያዝ ሲበቁ ማየት የሕልም እንጀራ እየሆነብን መጥቷል፡፡ ተስፋችንም እየጨለመ ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ቂም እንዳረገዘና እህህ እንዳለ ማዝገሙ የኢህአዴግን ተጠይነት እያጎነው መጥቷል፡፡
        የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና እድሜ ማሳጠሪያዎች ናቸው፡፡ በአንድ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ የመልካም አስተዳደር መስፈን ለገዢው አካል ዋስትናን ይሰጣል፡፡ ሕዝብ ባግባቡ የሚያስተዳድሩት፣ቀርበው ለጥያቄው ምላሽ የሚሰጡት፣ ዝቅ ብለው የሚያገለግሉት አስተዳዳሪዎች በየደረጃው ሲሾሙለት አሜን ብሎ በፍቅር ይገዛል፡፡ ኢህአዴግ ግን በዚህ ረገድ እጅግ የገዘፈ ችግር አለበት፡፡ ሹመኞቹ በብቃት ማነስ የእውር ድንብራቸውን ሲጓዙ እና በየቀኑ በሚደረጉ አሰልቺና ፀያፍ ግምገማዎች ካድሬዎቹ ከስልጣን ሲወርዱና ሲወጡ ማየት የዘመነ ኢህአዴግ ተውኔት ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ ከታችኛው እስከላይኛው መዋቅር ድረስ የሚታይ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በየደረጃው የሚያስቀምጣቸው የሕዝብ አስተዳዳሪዎች ነጋ ጠባ ህዝብን ለምሬት የሚዳረጉት ከሆነ ኢህአዴግ ዕድሜው እንደሚያጥር ሊገነዘብ ይገባል፡፡
         በሌላ በኩል የመልካም አስተዳደር ችግር ለሙስና በር የሚከፍት ይሆናል፡፡ በጥቅማ ጥቅም እየተደለሉ ፍትህን ማዛባት የከፋ አደጋ ያስከትላል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ በተቸገረበት በአሁኑ ሰዓት ጥቂት የኢህአዴግ ሹመኞች ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ የአገርን ሀብት እየተቀራመቱ ኑሮአቸውን ሲያደላድሉ ማየት እንደ ባህል እየተቆጠረ መጥቷል፡፡ ኢህአዴግም ሚስጥሩን አፍኖ እንጂ ሙስና ከቁጥጥሩ በላይ ሆኖበታል፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአለም አቀፍ ደረጃ የወጡ መረጃዎች እንዳመላከቱት በየጊዜው በባለሥልጣናትና በኢንቬስተሮች መካከል በሚሰሩ የረቀቁ ወንጀሎች እስከ 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአገር መውጣቱ ተዘግቧል፡፡ ይህ አስደንጋጭ አሀዝ ከመገታት ይልቅ በየአመቱ እየጨመረ መምጣቱ ሁኔታውን ውስብስብ አድርጎታል፡፡ ከዘመኑ ሹመኞች (ከቀበሌ እስከ / ማዕረግ ከተሾሙት) በሙስና ያልተነካካን ሰው ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ኢህአዴግም ሹመኞችን በሙስና ሰበብ በህግ ፊት የሚያቀርበው ግለሰቦቹ ፖለቲካዊ ችግር የሚፈጥሩ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይሄውም ሰሞኑን እየሰማን ያለው የሙስና ቅሌት ይሄ ደግሞ የገዢው መደብ በተለይም የአቶ በረከ ክፉ አመል እንደሆነ ከአቶ ታምራት፣ ከአቶ ስዬ አብርሃ የግፍ ውንጀላ መገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ትናንት በየአካባቢው የሚያውቀው የኢህአዴግ ሹመኛ ከብርሃን ፍጥነት በመጠቀ ሁኔታ ባለ ትላልቅ ፎቆችና ባለ ዘመናዊ መኪና ባለቤት ሲሆን ሲያየውምን ሠርቶ አገኘ?የሚለውን ጥያቄ እያነሳ ይገኛል፡፡ እውነት ለመናገር በስመ ታጋይና ተጋዳላይ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች እና ጀሌዎቻቸው ቁንጮ ኢንቬስተሮች መሆናቸው አነጋጋሪ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የህዝቡን አንጡራ ሀብት በመዝረፍ ባፍንጫቸው ቅቤ እየጠጡ የሚንደላቀቁ ሹማምንት ቅጥ ያጣ ኑሮ ሲኖሩ የሚያየው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነኝ ለማለት አይደፍርም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ለመሆን የሥርዓቱን የነቀዘና በሙስና የበከተ አካሄድ ለመታገል ግድ ይላልና፡፡ ሕዝቡ ተቃውሞውን በአደባባይ ማሰማቱ አይቀርም፡፡
           ዛሬ የሚታየው የኑሮ ውድነት በተለይም የምግብ እህል ዋጋ በፍጥነት ማሻቀብ ክስተቱ ዓለም አቀፉዊ (universal) ቢሆንም የእኛ ግን እጅግ የከፋ ነው፡፡ የዶላር ምንዛሪው በየእለቱ ሽርፍራፊ ሳንቲሞችን እየጨመረ በመሄዱ የዕቃዎች ዋጋም በየቀኑ እየናረ ሲሄድ ይስተዋላል፡፡ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ሲባል የሀገር ውስጥ ፍጆታን ግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ እያንዳንዷ የአገር ውስጥ ምርት ገበያ እየተፈለገላትና እየተለቀመች መላኳ የሕዝቡን ጦም አዳሪነት እያባባሰው ይገኛል፡፡ በምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ቋንቋ ብዙ ብር ጥቂት ምርትን ማሳደዱ ኢትዮጵያ ለድሆች መኖሪያ ሥፍራ እንደሌላት የሚያሳውቅ ይመስላል፡፡ ምናልባት ኢህአዴግ ድህነትን ለማጥፋት ድሀን ማጥፋት የሚል እኩይ ሚስጥራዊ ተልዕኮ ያነገበ ከሆነም አካሄዱ ዕድሜውን የሚያሳጥረው ነው፡፡
          አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ ደመወዝተኛው የወር ገቢውን በጅቶ ለመኖር አልቻለም፡፡ ደመወዙም እስከ ወር አጋማሽ አያደርሰውም፡፡ የሀገራችን የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ እንደሆነ ለአፍታ ቆም ብሎ ማስተዋል ገዢውን ፓርቲ ግድ ሊለው ይገባል፡፡ በኑሮ ውድነቱ ላይ ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ መወያየትም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ህዝቡ በረሀብ አለንጋ እየተገረፈና በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ እንኳን እየተሳነው ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ በቴሌቪዥን መስኮት ነጋ ጠባአድገናል፤ ተመንድገናል፤ ካደጉት አገሮች ተርታ ልንሰለፍ ተቃርበናል፤ ድህነት ታሪክ ሊሆን ነውእያሉ መለፈፍ ኢህአዴግን አያዋጣውም፡፡
    ከምርጫ 97 በኋላ በሚያስገርም ፍጥነት እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት ያሳሰበው ኢህአዴግ 2004 . ገበያን አረጋጋለሁ በሚል በስሜት ተነሳስቶ የወሰደው እርምጃ ችግሩን አባባሰው እንጂ ለድሀው የፈየደው አንዳች ነገር የለም፡፡ ሹማምነቱ ግን በቀበሌ ይከፋፈሉ በነበሩ የዘይትና የስኳር ምርቶች ኪሳቸውን አደለቡበት፡፡ ዛሬ የመጨረሻው ድሃ ኢትዮጵያዊ ምግብ የሆነችው ሽሮ እንኳን (ጥሬው እህል) አንዷ ኪሎ 38 ብር ገብታለች፡፡ ከዚህ በላይ የኑሮ ውድነት አለ እንዴ? ሽሮን ሲያታልሏት ፕሮቲን ነሽ አሏትየሚሏትን ሽሮ ለመመገብ ብርቱ ፈተና ሆኗል፡፡
          እስቲ ለአንድ አፍታ 97 . በፊት የነበረውን የሥጋ ዋጋ እናነፃፅር፡፡ ኢህአዴግ ራሱን ከኃይለ ሥላሴና ከደርግ መንግስታት ጋር ያነፃፅር የለም እንዴ፡፡ በዚያን ወቅት (97 ዓመት በፊት) በአዲስ አበባ ከተማ ኮተቤና ካራ አካባቢ አንድ ኪሎ ሥጋ 17 እስከ 30 ብር ይሸጥ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዛሬስ? ዛሬማ አንድ ኪሎ የሽሮ እህል እንኳን 38 ብር ገብቷል፡፡ ጋንማ የትኛው ኢትዮጵያዊ ሊበላው?  የጊዜው ሹመኞች ካልሆኑ በቀር፡፡
          ዛሬ የምዕራቡን አለም ዜጎች ጭምር በየአገራቸው ለአደባባይ አመፅ የጋበዘ አንገብጋቢ ችግር ነው፡፡ የሁሉም ነገር ምሳሌ አድርገን የምንጠቅሳቸው ያደጉት አገሮች በተለይም አሜሪካና እንግሊዝን የመሣሠሉትንም የሥራ አጥነቱ ችግር መፈናፈኛ አሳጥቷቸዋል፡፡ በየጊዜው አደባባይ እየወጡ በሚያካሂዱት ሰላማዊ ሠልፍ መሪዎቻቸውን ሲወርፉና አልፈው ተርፈው ሕንፃዎችንና ተሽከርካዎችን ሲያወድሙ እያየን ነው፡፡ መሪዎቹም ቢሆኑ ከዲሞክራሲያዊ አካሄዳቸው አንፃር የህዝቡን የገነፈለ ብሶት ማፈን አይችሉም፡፡
       ዛሬ የሚታየው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የነገ ፈታኝነቱ ከቶም አያጠራጥርም፡፡ አለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የህዝባችን ቁጥር እጅግ በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ የተማረው የሰው ሀይል ቁጥርም በዚሁ መጠን በእጅጉ ጨምሯል፤ ይጨምራልም፡፡ መንግሥታችን በውጭ እርዳታና ብድር ላይ በተመረኮዘ የሚገነባቸውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዛት እያደነቀና የቅበላ አቅማቸውም 100 ፐርሰንት በላይ መጨመሩን ያወጋል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ግን እነዚህ ተማሪዎች የነገ ምሩቃን መሆናቸው ግድ ነውና በየትኛው የሥራ መስክ ይሰማራሉ? ከትምህርት ተቋማቱ ግንባታ ጐን ምን የተመቻቸ የሥራ እድል ተፈጥሯል? በሌላ በኩል የገጠሩ ነዋሪ ወጣት ወደ ከተማዎች እየፈለሰ ሥራ ፍለጋ ሲንከራተት ሲታይ መጨረሻው ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ከወዲሁ ለመገመት አያዳግትም፡፡ ወደ አረብ አገራት በሞምባሳ፣ በጅቡቲ በሱዳን፣ በሞያሌ ወዘተ እየኮበለሉ የሚወጡ ወጣቶች በአገራችን ሥር የሰደደው የሥራ አጥነት ችግር የፈጠረው ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች በተለይም የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን (UNHCR) የኢትዮጵያ ስደተኞች ጉዳይ በብርቱ እንዳሳሰበው በጥር ወር መግቢያ ላይ በሚገባ ዘግቦታል፡፡ 2012 (..) . ከምሥራቅ አፍሪካ ተሰድደው ወደ የመን ከገቡት 103 ሺህ ስደተኞች መሀከል 75% (3/4) የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ይህም ማለት ከአራት (4) ስደተኞች መሀከል ሦስቱ (3) ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ነው፤ ያውም በየበረሀውና በየባህሩ ወድቀው የቀሩትን ሳያካትት፡፡  እንዲያም ብሎ በራሳቸው የውሸት ጎተራ በሆነው ኢቲቪ አሳይተው አሹፈውብናል። ከዚህ የምንረዳው የሥራ አጡ ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከመጠቆም ባሻገር ውሎ አድሮ የኢህአዴግ ፈተና ሊሆን ይችላል፡፡
       ሰዎች አስተውሉ በአንድ ጊዜ የተጨመረው የግብር ክፍያ ስንቱን ነጋዴ (በተለይም ትንንሽ ቸርቻሪዎችን) ምንኛ ያስደነገጠና ብዙዎቹ ንግድ ፍቃድ መልሰው ድርጅታቸውን ለመዝጋት መገደዳቸውን እናውቃለን፡፡ የግብር አተማመኑ በየአመቱ ከግብር ከፋዩ የገቢ እድገት ጋር አብሮ ማደግ ሲገባው በአንድ ጊዜ ከመቶ ወደ ሺህ ብሮች መሻገር አገርን የሚጐዳ አካሄድ ነው፡፡
       ለረጅም አመታት ስልጣን ላይ የሚቆዩ መሪዎች በቀናትና በወራት ውስጥ ዕድሜያቸው ሲያጥር ከሰሜን አፍሪካ አገራት ተምረናል አረ እንዲያውም የኛውም መሪ ሲያጥር አይተናል ቀጣዮም ኢህአዴግ ስለመማሩ ማወቅ ባይቻልም፡፡ የጥቂቶች በዙሪያቸው ተኮልኩለው ማሸቃበጥ በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ መሪ እንደሆኑ አድርገው የተዘናጉት ኮሎኔል ጋዳፊ እንደ ልባቸው የፋነኑባትን ዓለም በውርደት ሞት ተሰናበቷት፡፡ ኢህአዴግም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ካወቀ (ከተገነዘበ) ውሎ አድሯል፡፡ ዕድሜውን ለማራዘም በተለያዩ ጊዜያት የጣፋቸው ድሪቶዎች ጊዜያዊ ማዘናጊያና አቅጣጫ ማስቀየሻዎች ከመሆን ባለፈ የፈየዱለት ነገር የለም፡፡ ራሱን በቀጣይ ስልጣን ላይ ለማቆየት ሲል የሚያወጣቸው ሕጎችና መመሪያዎች የዜጎችን ህልውና በብርቱ ከመፈታተን አልፈው ምሬቱን በአደባባይ ለመግለፅ ወደሚገደድባት ደረጃ ሊያሸጋግረው ይችላልና ቆም ብሎ ያስብ፤አስተውሎ የሚራመድ ረጅም መንገድ ይጓዛልእንዲሉ፡፡

ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!


No comments: