Friday, June 21, 2013

የኢህአዴግ የልማት ፕሮፖጋንዳ

                 የኢህአዴግ የልማት ፕሮፖጋንዳ
          ለኢህአዴግ ልማት ማለት ፕሮጀክቶችን መጀመር በራሱ፣ማገባደድና ማጠናቀቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) የልማት ፕሮፖጋንዳ የተመሠረተው በዚህ ላይ ነው፡፡ ግልገል ጊቤ ፕሮጄክት ተጀመረ፣ሥልሳ በመቶ ተጠናቀቀ፤ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ በቀደም ተመርቆ ተከፈተ፡፡ ጊቤ 3 ፕሮጀክት 46 በመቶ ተከናወነ፤ የአባይ ፕሮጀክት 20 በመቶ ተከናወነ፤  ለአዲስ አበባ የባቡር መስመር ግንባታ የቻይና መንግሥት ብድር መስጠቱን /ሚኒስትር /ማርያም ደሳለኝ ገለፁ፡፡ ለአርሲ ገበሬዎች 200,000 ኩንታል ማዳበሪያ በብድር ተከፋፈለወዘተ.ወዘተ፡፡ ጋዝ ጋዝ የሚል አሰልቺ ፕሮፖጋንዳ!
         ችግሩ ያለው ኢህአዴግ ልማት ምን አንደሆነ አለማወቁ ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ልማት ማለት አራት ፍሬ ነገሮችን ያካተተ ፅንሰ ሃሣብ ነው፡፡ አራቱ የልማት መሠረቶች ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ የሀብት ቋት (resource pool)፣ፍትሐዊ የመሬት ድልድል፣ጥራቱን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና ፍትሐዊ፣ትክክለኛ የብድር ሥርዓት ናቸው፡፡ እነዚህ የልማት መሠረቶች በኢኮኖሚክስ የምርት መገኛዎች ተብለው ከተሰየሙት ከመሬት፣የሰው ኃይልና ካፒታል (Land, labor/enterprise and capital) ጋር የተቆራኙ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የእነዚህ ሁሉ የሀብት መሠረቶች (ቋት) ስለሆነች፣የእሷን ህልውና ሳንጠብቅ ስለ ኢትዮጵያ ልማት ማውራት አንችልም፡፡ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ሕልውና ጥያቄ እንዲነሳበት አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቷን እያጠፉት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትልቅ የሀብት ንዑስ ቋት የነበረችዋን ኤርትራ ከነወደቦቿ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም ብሎ አስገንጥሏል፡፡ ይህን በማድረጉ በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሣራ ከማድረሱም በላይ፣የቀረችዋም ኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያንን ሳያማክር ራሱ ባረቀቀው ሕገ-መንግሥት መሠረት ለጐሣ ክልሎችየመገንጠል መብት ሠጥቻለሁበማለቱ እያካሄድኩ ነው የሚለው ልማት ራሱ የማን ልማት እንደሆነ ለማወቅ ያስቸግራል! “የትግራይ ነፃ ሪፓብሊካንልማት ነው ወይስየኦሮሚያ ነፃ ሪፐብሊካንልማት የሚያካሂደው?!
        ለዚህም ነው ኢህአዴግልማት!ልማት!” እያለ ከማደንቆሩ በፊት እየካሄደ ያለው የማን ልማት እንደሆነ በግልፅ ማሳወቅ አለበት ብለን የምንከራከረው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለውን የጋራ ቋታችንን ኢህአዴግ ስለተረተራት ሀብቷ በየአቅጣጫው እየፈሰሰ ነው ፡፡ (በቅርቡ የኢህአዴግ ባለሥልጣናትና ደጋፊዎቹ 8.5 ቢሊዮን ዶላር ከሀገር እንዳሸሹ የተገለፀውን ያስታውሷል!) በመሆኑም፣ አንድ ነገር በጣም ግልፅ እየሆነ መጥቷል፤ኢህአዴግ አካሄዳለሁ የሚለው ልማት የኢትዮጵያ ልማት አይደለም! ሁለተኛው ነጥብ፣ለኢህአዴግ ልማት ማለት ጥቂት የመንግሥት የልማት ሥራዎችን መጀመር፣ማገባደድና ማጠናጠቅ ከሆነ፣በዚህም ረገድ የልማት ውጤቱ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን በኢትዮጵያ ተንሠራፍቶ ካለው የሥራ አጥነት መጠን አኳያ፣ከጥቃቅን እስከ ትላልቅ ሥራዎች በአንድ ጊዜ እስከ ሁለት መቶ የልማት ፕሮጀክቶች ተወጥነው ተግባራዊ ሊሆኑ ሲችሉ፣ወደ ሰው ኃይል ገበያው በየዓመቱ የሚገቡትን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሠራተኞች ለማስተናገድ ደግሞ በየዓመቱ እስከ አርባ (40,000) የቢዝነስ ፕሮጀክቶችን ማከናወን ይቻላል! ይህ ሊሆን የሚችለው ግንአብዮታዊ ዴሞክራሲእናልማታዊ መንግሥትየሚል አባዜ በተጠናወተው የኢህአዴግ መንግሥት ሥር ሳይሆን፣በተለይ ለግሉ የኢኮኖሚ ክፍል ከፍተኛውን የልማት ሚና በሚሰጥ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት አስተዳደር ብቻ ነው! ኢህአዴግልማታዊ መንግሥት? ማለት ምን እንደሆነ አያውቅም፡፡ ትክክለኛው የልማታዊ መንግሥት ትርጉም ራሱ መሥራት የሚገባውን ሁሉ እየሰራ ግን ለግሉ የኢኮኖሚ ክፍል አስፈላጊውን ሁሉ አመቺ ሁኔታ (enabling environment) የሚፈጥር መንግሥት ማለት ነው፡፡ በዚህ መልክ የተቀረፀ መንግሥት ልማታዊ ሳይሆን ኮሚውኒስት መንግሥት ነው! የዚህ ዓይነት መንግሥት ደግሞ በተለይ ከሶቭዬት ሕብረት መፈራረስ በኋላ አሁን የሰው ልጅ በደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ተረጋግጧል! በአልባኒያው ኮሚኒስት ፓርቲ አምሳል የተቀረፀው ማሌሊት ተሸፋፍኖ ከተደበቀበት ምድር ቤት በጓሮ በር እየገባ ይሆን እንዴ?!
            ሌላው የልማት መሠረት ፍትሐዊ የመሬት ድልድል መሆኑ ከላይ ተገልጿል፡፡ ይህ ንድፈ ሐሳብ ሶሻሊስታዊ ወይም ኮሚውኒስታዊ ሊመስል ይችላል፤ ግን ለፍትሐዊ ካፒታሊዝም ዕድገት ራሱ አስፈላጊ ነው፡፡ ካፒታሊዝም ማለት በነፃ ገበያ በነፃ መወዳደር ማለት ከሆነ፣የማንም የሥራ ውጤት ያልሆነውና ተፈጥሮ የለገሰን መሬት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሳይከፋፈል፣ዜጐች እንዴት በእኩልነትና በነፃ መወዳደር ይችላሉ? በሌላ አገላለፅ፣በጠመንጃ ኃይል አሥር ጋሻ መሬት የያዘ ነፍጠኛ ባላባት አንዴት ግማሽ ሄክታር ማሳ በጭሰኝነት ከያዘ ምስኪን ገበሬ ጋር በነፃና እኩል እየተወዳደረ ነው ማለት እንችላለን? ለዚህም ነው፣መሬት ላራሹብለ ሠላማዊ ሠልፍ የወ! የደርግ መንግሥት የባላባቱን ሥርዓት አፈራርሶ፤ግን ይመራበት የነበረው አይዲኦሎጂ ሶሻሊዝም ኮሚውኒዝም ስለነበር፣መሬት የመንግሥት ሀብት ነውበሚል መርህ ለገበሬው የጠቀሜታ መብት (use rights) ብቻ ነበር የሰጠው፡፡ እንግዲህ፣ከአይዶሎጂው አኳያ በወቅቱ ይህን ስህተት ነው ለማለት አያስደፍርም ነበር፡፡ ከሶቤት ሕብረት መፍራረስ በኋላ ግን የአይዶሎጂው ዋና አእምሮአዊና ሚሊተሪ ምሶሶ (Intellectual and military power) ስለወደቀ፣ በተግባራዊ ስኬታማነቱ የታወቀው ካፒታሊዝም የበላይነቱን እንደሚይዝ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነበር፡፡ እናም፣ኢህአዴግመሬት የመንግሥት ብቻ ነውየሚለው የትኛውን የአይዲኦሎጂ መሠረት ይዞ ነው? ይህን ጉዳይ በተመለከተ ኢህአዴግ ምንም ዓይነት ንድፈ ሃሳባዊ መሠረት የለውም! ኢህአዴግ መሬት የመንግሥት ብቻ ነው ያለው የደርግ መንግሥት በጠቀሜታ መብት መልክ ለሕዝብ ያከፋፈለውን መሬት ከሕዝብ ነጥቆ ለራሱ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ለውጭ ኒዎኮሎኒያሊስት ኃይሎች በማከፋፈል ዘመናዊ ፊውዳሊዝምን እንደገና ሊጭንብን አስቦ እንደሆነ እስካሁን የወሰዳቸው ርምጃዎች በቂ ማስረጃዎች ናቸው! በየከተማው ግንባር ቦታዎች ከድሃው ሕዝብ ተነጥቀው ለኢህአዴግ ሁነኛ ሰዎች እየተሰጡ (በሊዝ ሽፋን) በከተማ ልማት ሰበብ ትላልቅ ፎቆች ተሠርተዋል!? እየተሰሩም ነው! በገጠር ደግሞ ገበሬውን በማፈናቀል ጭምር ሰፋፊ መሬቶች ለዘመኑ ኒዎኮሎኒያሊስት ኃይሎችና ወኪሎች በርካሽ ዋጋ እየተቸበቸቡ መሆናቸውን በአሁኑ ጊዜ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡ በአጭሩ፣ጥቂት የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ኒዎኮሎኒያሊስቶች መሬታችንን ተቀራምተው እኛን መሬት አልባ እያደረጉን ነው! የኢኮኖሚ ባርነትና ጭሰኝነት እንደገና እየተጫኑበን ነው!
            ሦስተኛው የልማት መሠረት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና መሆኑም ከላይ ተገልጿል፡፡ እንደሚታወቀው የሀብት ማፍሪያዎች መሬት፣የሰው ኃይልና ካፒታል ናቸው፡፡ የሰው ኃይል ካልተማረና ካልሰለጠነ የማምረት ችሎታውና አቅሙ እጅግ ውሱን ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ እንደሚለው ሳይሆን፣የሶሻል ሳይንስ ትምህርቶች በተለይ የፖለቲካ ሳይንስና ኢኮኖሚክስ ወሳኝነት አላቸው፡፡ ትክክለኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ካልተዘረጋ በስተቀር ሌሎች ሙያዎችና ትምህርቶች ሁሉ የሚያስገኙት ውጤት ከሚጠበቀው በታ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ በሌላ በኩል፣የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ፈፅሞ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ግን ይህን መሠረታዊ መርህ ወደ ጐን በመተው፣ለይስሙላ በየአለበት የሚገትራቸውን የዩኒቨርስቲ ሕንፃዎች ከሞላ ጐደል የራሱን ካድሬዎች ማሠልጠኛ አድርጓቸዋል! በመሆኑም፣አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎች ያፈራ ሲሆን፣የልማታዊ መንግሥትን ትርጉም በደንብ የማያውቁ ኢኮኖሚስቶች ደግሞ በአደባባይ እንዲዋሹ በልዩ ስኬል ወፍራም ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው! የሐሰት አሓዛዊ መረጃዎችን እያቀነባበሩ ኢኮኖሚው 11.5 በመቶ አድጓል የዋጋ ንረቱ የዕድገት ውጤት ነው  የገንዘብ መጠን መብዛት የዋጋ ንረት መንስዔ ሆኖ አያውቅም (አሁን አሁን እውነቱ አፍጦ ሲመጣ /ሚኒስትሩ ጭምር ይህንን እያመኑ ነው!)በኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ዓመታት ረሀብ የለም (ግን የወቅቱ ድርቅ ባስከተለው ረሀብ ምክንያት በየቀኑ አሥር ሕፃናት እንደሚሞቱ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ያመለክታል)፤የዋጋ ንረቱ የመጣው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በመብዛቱ ነው፤ለውጭ ዜጐች (ኢንቨስተሮች) መሬት የሰጠነው፡፡ ገበሬውን ሳናፈናቀል ነው፤ወዘተእያሉ ሽምጥጥ አድርገው ይዋሻሉ!
          ሦስተኛው የሀብት ማፍሪያ ካፒታል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ መሬት ራሱ እንደ ተፈጥሮአዊ ካፒታል (natural capital) ሊቆጠር ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አዲስ የገንዘብ ካፒታል (ወደ ቁሳዊ ካፒታል ሊቀየር የሚችል) የሚገኘው በራስ ቁጠባ ገንዘብ እና ከባንክ ብድር ነው፡፡ የራስ ቁጠባ ገንዘብ የሚፈለገውን ቁሳዊ ካፒታል (physical capital) ለማግኘት ስለማይበቃ ዋናው የገንዘብ ካፒታል ምንም የባንክ ብድር ነው፡፡ ይሁንና ይህንንም ኢህአዴግ በከፍተኛ ደረጃ ተቆጣጥሮታል፡፡ የመንግሥት ባንኮች (ብሔራዊ ባንክ፣የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣የልማት ባንክና ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ) ሙሉ በሙሉ በኢህአዴግ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣በኢትዮጵያ ትልቁ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር የሚሰጠው በአብዛኛው በኢህአዴግ ትዕዛዝ (directed credit) ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢህአዴግ መበልፀጊያ ድርጅት መሆኑን ለመረዳት የትላልቅ ተበዳሪዎችን ስም ዝርዝር ማየት ብቻ ይበቃል! በነፃ ገበያና በነፃ ውድድር ሥርዓት የባንክ ብድር መስጠት ያለበት በአዋጪነት እና በብድር ማስያዥ (Feasibility and collateral) መርሆዎች ነው፤ ኢህአዴግ ግን በትዕዛዝ ራሱ ብድር የወስዳል፤ደጋፊዎቹ ብድር እንዲያገኙ ትዕዛዝ ይሰጣል!
            ለማጠቃለል፣ኢህአዴግልማት ሲል፣የጋራ የሀብት ቋት (resource pool) የሆነችዋን ኢትዮጵያ ተርትሮናበመገንጠል መብትሽፋን ሀብቱ በየአቅጣጫው እንዲፈስ አድርጐ ስለሆነ፣እያካሄድኩ ነው የሚለው ልማትየኢትዮጵያ ልማትለመሆኑ ማረጋገጫ የለም! የደርግ መንግሥት በጣለው መሠረት ላይ ፍትሐዊ የመሬት ድልድል በማድረግ ፈንታ ከዜጐች የመሬት ይዞታቸውን በኃይል እየነጠቀ ለጥቂት አባላቱና ደጋፊዎቹ በመስጠቱ፣ሕዝቡን መሠረት ያደረገ ልማት (broad-based development) ሳይሆን እያካሄደ ያለው፣ዓይን ያወጣ የጥቂቶች ዝርፊያና ምዝበራ ነው! በተመሳሳይ፣ኢህአዴግ የዘረጋው የትምህርት ሥርዓት የትምህርት ጥራትን የሚያዳክም እንደመሆኑ፣ውጤቱየተማሩ ሥራአጦችንማብዛት ሆኗል! ካፒታልንም በተመለከተ፣ከላይ እንደተገለፀው ነው፡፡ በመሆኑም፣ኢህአዴግ እያካሄደ ያለው ልማት ሳይሆን ዝርፊያ ነው! በውጭ ዕርዳታ የተሠሩትና እየተሠሩ ያሉት ጥቂት መሠረተልማቶች ይህንን ሀገር አቀፍ ግዙፍ የዝርፊያ ተግባር ለመሸፋፈን ጭምር ያገለግላሉ፡፡ የኢህአዴግ የልማት ፕሮፖጋንዳ የሚያነጣጥረውም እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴለቪዥን ድርጅት በየቀኑ ለሚያሰራጨው ጋዝ-ጋዝ ለሚል የልማት ፕሮፖጋንዳው እነዚህን እንደ አቢይ ግብዓት ይጠቀምባቸዋል! በሀገራችን እውነተኛ ልማት የሚካሄደው ልማት ኢትዮጵያዊና ሕዝባዊ ሲሆን ብቻ ነው! ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ኢህአዴግ ለአለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ያዋቀረው የዝርፊያ ሥርዓት ሲፈራርስ ነው! የኢህአዴግ የልማት ፕሮፖጋንዳ እንደቆርቆሮ የሚጮህ ቱልቱላ ነው!


ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: