ወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ይኑረው
ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ማንኛውንም ዓይነት እውቀት ለመቅሰም የሚያስችል ቀልጣፋና ብሩህ አእምሮ፣ ለምርታማነት ተግባር ሊውል የሚያስችል ጉልበትና በቀላሉ የማይዝል አካላዊ ጥንካሬ ያለው ነው፡፡ በዚያው ልክ በአግባቡ ካልተያዘ በስተቀር ከወጣትነቱ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ በተያያዘ ምክንያት በተለያዩ አደጋዎች በቀላሉ ሊጋለጥ የሚችል ነው፡፡
የወጣቱ ዝንባሌ የብዙ ጉዳዮች ድምር ውጤት ነው ብዙ ጊዜ በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዜጎች መካከል ጥቂቶቹ ጥፋት በሚፈፅሙበት ወቅት ወጣቱን እንዳለ የማውገዝና የማማረር አዝማሚያ ጎልቶ ይንፀባረቃል፡፡ የዘቀጠ፣ ደካማ፣ የሀገር ፍቅር የሌለው፣ ለሰዎች ክብር የማይሰጥ፣ በንቀት የተወጠረ ወዘተ ትውልድ እያሉ የወጣቱን ባሕሪይ መጥፎ ምስል የሚሰጡ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡
የእነዚህ ተቀፅላ ስሞችን በሚያናፍሱ ሰዎች አብዛኛው ወጣት አቅሙንና እውቀቱን በመጠቀም ተፈጥሮዊ ዝንባሌውንና አገራዊ ራዕዩን እንዳያሳካ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን አገሪቷን እየመራ ያለው ገዥው ስርዓት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ወጣቱን ረግጦና ከፋፍሎ ለመግዛት የተለያዩ ስልቶችን የሚጠቀመው የኢህአዴግ ስርዓት በአገራዊ አጀንዳዎቹ ላይ ገለልተኛ በማድረግና አካዳሚያዊ እውቀቱንም የላሸቀ በማድረግ የፈረንጅ ባህል ተከታይ እና በተለያዩ ሱሶች በቀላሉ ተጠቂና ተጋላጭ እያደረገው ይገኛል፡፡ ይሄ አይነቱ ሰይጣናዊ አመለካከት ትውልድን ከመግደል ጀምሮ በአገራዊ ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ ወጣት እንዳይፈጠር ሆን ብሎ እየሠራበት ይገኛል፡
ለወጣቱ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት፣ ጤንነቱን የጠበቀ ዘላቂ ህልውናውን የሚጠቅም የሥራ ዕድል፣ የዴሞክራሲና የልማት አጀንዳ ቀርፀውለት፣ የረባ ነገር ሳይሰሩ ትላንት ወጣት የነበረው እንዲሁ በከንቱ ጎልማሳ እየሆነ ዘመንን ዘመን እየተካው መኖር የተለመደ ሆኗል፡፡ በአለም ውስጥ ካሉት አገራት እንደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሁሉንም አይነት ዕድል የተነፈገባቸው ለመከራና ስቃይ ብቻ የተጋለጡ አሳዛኝ ስለ መኖራቸው ያጠራጥራል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉት ወጣቶች የስርዓቱን እድሜ ማራዘሚያ ተደርገው በርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ጊዜቸውን እንዲያሳልፉ የተፈራደባቸው ይመስላሉ፡፡ የአገራችን ወጣት ጦርነት የሚለበልበው፣ ርሃብ የሚጨርሰው፣ እስርና ግርፋት የበዛበት፣ አገሩን ጥሎ መሰደድ ያንገሸገሸው የመማርና ስራ የማግኘት የዜግነት መብቱን የተገፈፈበት፣ ለበሽታና ለተለያዩ አደጋዎች የተጋለጠ በዓለም ላይ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ተፈጥሮአዊ አቅሙንና ለጋ አእምሮውን ተጠቅሞ ሕገ መንግስታዊ ክብሩንና ሰብዓዊ መብቱን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ እንዳይችል ሀሳቡን በነጻነት ለመግለፅና ሕገ መንግስታዊ የሆነውን ሰላማዊ ተቃውሞውን እንዳይገልጽ ለትንታኔ በማይመች ሕግ በመቆላለፍ ቅርቃር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሽብርተኝነት ሕግ ከብዙ በጥቂቱ አመላካች ነው፡፡ ይህ በወጣቱ ላይ እየተሰራበት ያለውን ደባ የስርዓቱን መሰሪ የጥፋት መንገድ የሚያጋልጡና የተሻለ ሀሳብ አለን ለሚሉ ወጣቶች የተዘጋጀ መጣያ መሆኑን የኢህአዴግ ስርዓት ለወጣቱ ያለው አመለካከት ማሳያ ነው፡፡ ለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብታቸው ዘብ የቆሙ ወጣት ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ላይ የተቃጣው ድርጊት ስርዓቱ በወጣቱ ላይ የከፈተው ዘመቻ ከመሆኑም በላይ ስርዓቱ የሚያራምደው የተሳሳተ የፖለቲካ ድምር ውጤት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
“መብቴ ተነካ፣ ጥቅሜ ተጓደለ፣ ነጻነቴ ተገፈፈ›› የሚሉትን ወጣቶች ሳያዳምጡ እንዲሁ ከማንኛውም የውይይት አጀንዳ ውጭ አድርገው የረሱትን ወጣት ዳር ድንበር ሲደፈር የአገር አንድነት ሲናጋና መውጫ መግቢያ ሲጠፋ ብቻ ‹‹አገር ተረካቢ ወጣቱ፣ የአገር ተስፋ ወጣቱ፣ የአገር መከታ ወዘተ›› እያሉ ከወረቀት ያላለፉ ተረት ማሞካሸት በኢህአዴግ ቤት የተለመደ ነው፡፡
ብዙውን ጊዜ የወጣቱ አብይ ፍላጎቶች በዴሞክራሲና ሰባዓዊ መብቶች የታነፀ ስርዓትና የተረጋጋ ሰላም ማግኘት፣ ጤናው የተጠበቀ ዜጋ መማርና እውቀቱን ማስፋቱ በሙያው ስራ ማግኘት የመሳሰሉት ከብዙ ጥቂቶቹ ፍላጎቶቹ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች አለመታደል ሆኖ በሁሉም ሁኔታ ፈተና ውስጥ ለመኖር ቢገደዱም ከዚህ ለመውጣት የሚያስችል የህይወት አማራጭ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሞትን፣ ራሃብን፣ ስደትን፣ መሃይምነትን፣ በሽታን ጦርነትን፣ የመብት ረገጣን እየኖሩበት ስለሆነ ጉዳቱን በሚገባ ያውቁታል፡፡ ይህንን አገራዊ ውርደት ተሸክሞ መቆየት ጥሩ የህይወት አማራጭ እንዳልሆነ ይረዱታል፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ከዚህ የተሻለ ህይወት እንዲኖር ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ለማህበረሰብ ፍላጎት መሳካት በምናደርገው እልህ አስጨራሽ የሰላማዊ ትግል ላይ በተናጠል ሳይሆን የተደራጀ አቅም በመፍጠር በሚደረገው ሰላማዊና ሕገ መንግስታዊ ጥያቄ ፊት መቆም ስንችል ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ወጣቱ አቅሙንና ጉልበቱን ተጠቅሞ ትግሉን መቀላቀል ያለበት ከየትኛው ጊዜ በላይ አሁን ነው፡፡ ሁላችንም የድርሻችንን በመወጣት በተባበረ ክንድ የአገራችን ተስፋ እናለምልም የምንግዜም ሀሳቤ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment