ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባዎ
• በሚኒስትር ማዕረግ ሦስት ምክትል ከንቲባዎች ይሾማሉ እየተባለ ነው
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣይነት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ በሚሾም አንድ ከንቲባና በሚኒስትር ማዕረግ በሚሾሙ ሦስት ምክትል ከንቲባዎች እንደሚመራ ምንጮች ጠቆሙ፡፡
ምንጮች እንደሚሉት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ለከተማው ከንቲባ ሆነው የሚሾሙት አቶ ድሪባ ኩማ ናቸው፡፡ አቶ ድሪባ በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት ሚኒስትር ሲሆኑ፣ መሰንበቻውን ከወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ጋር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየታዩ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በሚኒስትር ማዕረግ የከተማው ቀጣዮቹ ምክትል ከንቲባዎች የሚሆኑት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩርያ ኃይሌ፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ናቸው ሲሉም ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
ነገር ግን ወ/ሮ አዜብ በየትኛውም ቦታ መሾም እንደማይፈልጉ እየገለጹ መሆናቸውን ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ሪፖርተር በዚህ የመዋቅር ለውጥና ሹመት ጉዳይ ማረጋገጫ ለማግኘት ለአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ቢያቀርብም፣ እየተካሄደ ያለውን ሥራ በዝርዝር መግለጽ ባለመፈለጉ አልተሳካም፡፡
ምንጮች እንደሚያብራሩት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ ቢሮዎችን በኃላፊነት የሚመሩት ዕጩ ተሿሚዎች በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ እንደሚሾሙ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር የሚፈቅደው አንድ ምክትል ከንቲባ በመሆኑ፣ ከአንዱ ዕጩ ተሿሚ በስተቀር ሁለቱ ተሿሚዎች በምክትል ከንቲባ ማዕረግ እንደሚሾሙ አመልክተዋል፡፡
ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ይህንን ያደረገበት ምክንያት አዲስ አበባ ላይ የተጀመሩና በቀጣይ የሚጀመሩ የልማት ሥራዎች ሰፊ በመሆናቸው፣ ይህንን የሚሸከም የአስተዳደር የሥልጣን እርከን ማደራጀት ያስፈልጋል በሚል ነው፡፡
የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጀማል ረዲ መዋቅሩንና አሿሿሙን ባይገልጹም፣ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባን የሚያስተዳድረው የሰው ኃይል በከፍተኛ ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ በማደግ ላይ ያለች ከተማ ብትሆንም፣ በከተማዋ ውስጥ አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡ ኅብረተሰቡ አምርሮ ከሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መካከል የመኖርያ ቤት እጥረት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር፣ የትራንስፖርት እጥረትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የከንቲባ ኩማ ደመቅሳ አስተዳደር እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ተግባራትን ቢያከናውንም አዲስ አበባውያን ሊረኩ አልቻሉም፡፡ ኢሕአዴግ የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ መወሰኑን በሚያመለክት ደረጃ ለአዲስ አበባ ከተማ ትኩረት እየሰጠ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ይናገራል፡፡
ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮቹን ከፌደራል ወደ አዲስ አበባ በሚያዝያ ወር በተካሄደው ምርጫ አማካይነት ቢያዛውርም፣ በእነዚህ ሹማምንት ምክንያት የተፈጠረውን የፌዴራል መንግሥት የአመራር ክፍተት የመሙላት ሌላ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል፡፡
No comments:
Post a Comment