Friday, June 28, 2013

ታጋይን በማሰር ትግሉን ማሰር አይቻልም!!!

ታጋይን በማሰር ትግሉን ማሰር አይቻልም!!!
        ‹‹ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም›› የሚል ፅኑ መፈክር በማሰማት በበርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ወደ ስልጣን የወጣው የኢህአዴግ መንግስት መፈክሩን በመዘንጋት ታሪክ ራሱን ይደግማልእንደሚባለው ያለፉትን ገዥዎች ታሪክ እየደገመ ይገኛል፡፡
       ደርግ ራሳቸውን ‹‹ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ ወንበዴ፣ ሽፍታ›› የመሳሰሉ ስሞችን እየሸለመ ለማጥላላት እንደሞከረው ሁሉ ኢህአዴግም ከጣለው አምባገነን መንግስት ምንም ሳይማር ‹‹ህገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ›› እና አሁን ደግሞ ‹‹ሽብርተኛ›› በማለት ዘላለማዊ ሆኖ በመቆየት በመሻት የሰላማዊ ትግሉን ፈር ለማስለቀቅ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የሆኑትንና ጋዜጠኞችን በማሰርና የፈለገውን ፍርድ በመስጠት እፎይታ ለማግኘት ሲሞክር እያስተዋልን ነው፡፡
         የኢህአዴግን አገዛዝ ከደርግ የሚለየው ደርግ በአደባባይ ገድሎ ሲፎክር ኢህአዴግ ደግሞ ህግ አውጥቶና ህግ ጠቅሶ ሞት ይበይናል፡፡ በአደባባይ መግደልና በሚስጥር መግደል ሁለቱም የወንጀል ልዩነት የላቸውም፡፡ የዜጎችን ነፃነት ቀምቶ፣ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ እያሸማቀቁ ተቃዋሚዎችንም የተለያየ ስም እየለጠፉና እያሰሩ መኖር ጊዜውን ጠብቆ በወንጀለኝነት እንደሚያስጠይቅ ካለፉት ታሪኮቻችን አይተናል፡፡ አሁን የምንለው ኢህአዴግ ካለፉት የታሪክ ኪሳራዎች በመማር ታጋይን በማሰር ትግሉን ማቆም እንደማይቻል ተገንዝቦ የፖለቲካ እስረኞችን በአስቸኳይ በመፍታት ሰላም ማውረድ አለበት፡፡
          ኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ እንደሚስፈልጋት እሙን ነው፡፡ ይሄ ደግም የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚዳፈሩና ህዝቦቿን ለአደጋ የሚያጋልጡ የውጭ ጠላቶችን ለመከላከልና ለመቅጣት ያገለግላል፡፡ በሃገራችን እሆነ ያለው ግን ሌላ ገፅታ ያለው ነው፡፡ የፀረ- ሽብር ህጉና የደህንነት መስሪያ ቤቱ በመተባበር በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ያጠቁበታል፡፡ የገዥውን ፓርቲ የስልጣን ጥቅም ይነካሉ ተብለው የሚታሰቡ ኢትዮጵያውያን ገለል እንዲሉ ይደረግበታል፡፡ በሃገራችን ይሄው ህግ እየተጠቀሰባቸው እንደ ቀልድ ‹‹በሽብርተኝነት
ተጠርጥረው›› እየተባለ ወደ እስር ቤት የሚወረወሩት በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግስት ህጉን ለተቀናቀኞቹ እንደ ማጥቂያ መሳርያ እየተጠቀመበት ነው ብለን እናምናለን፡፡
           በነ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ስም የተከሰሱ ኢትዮጵያውያንና በታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ የተበየነው ከስምንት ዓመት እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያመላክተን ገዥው ፓርቲ እየተከተለው ያለው አቅጣጫ አደገኛና ሃገሪቱን ወደ መጥፎ ሁኔታ የሚከት ተግባር እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹የፀረ-ሽብር ህጉ›› እና ‹‹ሽብርተኛ›› የሚለውን ጨዋታ በማቆም እንዲሁም ከተቃዋሚዎች ጋር በመወያየት አፋጣኝ እርምጃዎች መውሰድ ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም ገዥዎች ህግ ጠቅሰው ሲፈርዱ ህዝቡ ምን እንደሚላቸው ጆሮ ሰጥተው በመስማት እውነቱን ለማየት መሞከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግስት ህዝብን ማዳመጥ ውዴታው ሳይሆን ግዴታው ነው፡፡
       እንደ እኛ እምነት ታጋይን በማሰር ትግሉን ማቆም ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ትውልድ እስከቀጠለ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል፡፡ብዙ አንዷለዓሞች ብዙ እስክንድሮችም ይፈጠራሉ፡፡ ለዚህ ነው ማሰርና ማሳደድ ፈፅሞ መፍትሄ አይደለም የምንለው፡፡ ይልቁንም ስልጡን የሆነውንና ሌላውም ዓለም የሚጠቀምበትን የመነጋገር መንገድ መከተል ይገባል፡፡ ዛሬም ነገም ወደፊትም ችግር የሚፈታው ህዝብን በማዳመጥና በመነጋገር ብቻ ነው፡፡
         ኢህአዴግም አሮጌውን የማሳደድና ስም የመለጠፍ መንገድ እርግፍ አድርጎ በመተው፤ ትእቢትና ከንቱነትን ወደ ትህትና በመለወጥ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የሚያስማማውን መንገድ ቢከተል ከውርደት ይድናል ብለን እንገምታለን፡፡
ታጋይን በማሰር ትግሉን ማሰር አይቻልም!!!


ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: