Friday, August 30, 2013

ኢህአዴግ የክስ ማስረጃ ሰበሰበ

ኢህአዴግ የክስ ማስረጃ ሰበሰበ



የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር በኢቲቪ ያደረጉትን 

ክርክርተመለከትኩ።በክርክሩ ተቃዋሚዎች ብልጫ ወስደው ታይተዋል። አሳዛኙ 

ነገር ኢህአዴግ ይህን መድረክ ያዘጋጀው፦” የክስ ማስረጃ ለመሰብሰብ” መሆኑ ነው።

- ምርጫ 97ትን ተከትሎ በታሰሩት የቅንጅት መሪዎች ላይ ዐቃቤ ህግ አቅርቧቸው 

ከነበሩት የክስ ማስጃዎች ብዙዎቹ የቅንጅት አመራሮች በምርጫ ቅሰቀሳው ጊዜ 

በአደባባይ ከኢህአዴግ ጋር ቁጪ ብለው ሲከራከሩ የተናገሯቸው ነገሮች ነበሩ። 


-አንዷለም አራጌ የአንድነት ፓርቲ አመራር ሆኖ መመረጡን ተከትሎ ከጓደኞቹ ጋር 

ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ።ከዚያም በ2000 ው የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ 

በኢቲቪ በተዘጋጀው የክርክር መድረክ ላይ ፓርቲውን ወክሎ በመቅረብና መድረኩ 

ነፃ እንደሆነ በማሰብ ሁላችንም የምናስታውሰውን ጠንካራ የተቃውሞ ንግግር 

ተናገረ። በዚያ ንግግሩ ፦”ኢህአዴግ እየተከተለ ያለው አሠራር፦ “ተቃዋሚዎች 

እግር እስኪያወጡ እጠብቃለሁ፤ማውጣት ሲጀምሩ እግራቸውን እቆርጣለሁ የሚል 

ነው” ያለው አንዷለም ፤ብዙም ሳይቆይ ያው ያለው ነገር በሱም ላይ ደረሰ። እስር 

ቤት ተወረወረ። በዚያም ፊቱ እስኪበልዝ ድረስ ክፉኛ ተደበደበ።

-እስክንድር ነጋ ከልጆቹ ተነጥሎ በታሰረበት፣ ንብረቱ በተወረሰበትና ቤተሰቡ 

በተመሰቃቀለበት በዚህ አስከፊ ሁኔታ ሳይቀር የስርዓቱ ደጋፊዎች የዛሬ 10 ዓመት 

አካባቢ በጋዜጣዎቹ ላይ በነፃነት በተስተናገዱ፣ ከሚዛናዊነት አንፃር ተመሣሳይ 

አፀፋዊ ምላሽ በቀረበባቸው እና በሌሎች ተሳታፊዎች ይጻፉ በነበሩ ጽሁፎች 

ደጋግመው ሢከሱት ስናስተውል፤ የታሰረበት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ይገባናል።

“የቂም በቀል ፖለቲካን በሚያቀነቅኑ እንደ ኢህአዴግ ዓይነት ፓርቲዎች ገዥ 

በሆኑበት አገር፤ በነፃ ፕሬስ ላይ የሚጻፉ ጽሁፎችም ሆኑ በነፃ የፖለቲካ ክርክር 

መድረኮች ላይ የሚደረጉ ንግግሮች እየተጠለፉ ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚዎችን 

ለመክሰሻ(ለመምቻ) መዋላቸውን ይቀጥላሉ።

እንደውም አጋነንክ ካላላችሁኝ እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር 

መድረክ የሚዘጋጀው፤በእንቅስቃሴያቸው ኢህአዴግን ስጋት ላይ የጣሉ ፓርቲዎችን 

ለመክሰስ ማስረጃ ሲጠፋ ይመስለኛል። ከአሁኑ ክርክር ምን ክስ እንደሚወጣ 


በቅርቡ ጠብቁ።ግን …ግን…. ዲሞክራሲያዊ ባህልን ከማጎልበት እሳቤ በመነሳት 

በሚዘጋጁ የፓለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ ላይ የሚደረጉ ሙግቶች ለክስ 

ማስረጃ የሚቀርብበት ሌላ አገር ያለ ይሆን?

ከቂም በቀል ፖለቲካ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አይወለድም!

No comments: