Monday, August 26, 2013

ዘረኝነት ምንድን ነው?

ዘረኝነት ምንድን ነው?

ማስተዋል ለማያቅተው
race



አንዳንዴ፣ ጊዜና ሁኔታውን ከጠበቁ አንድ ሁለት ቃላት፣ ከሺ ዓ/ነገሮች የበለጠ በአእምሮ ውስጥ ይገቡና እውነቱን ቁጭ ያደርጉታል።
አውሮፓውያን መቼም በዘረኝነት የተጠመቁበት ጊዜ አለፎና ተመክሮዋቸውን ሰብስበው ለራሳቸው፣ በተለይ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ፣ በሰላም ለመኖር ይሞክራሉ፤ የኋላኋላ ተባብረው፣ ቀደም ሲል ደግሞ ቢያንስ በየራሳቸው መንግሥታት ሥር። በተለይም ጀርመን ስለዘረኝነት ተመክሮ ያውራ ቢባል፣ ይህ እንደማይሳነውና እንደሚችል ማንንም አያጣላም። ይህም ሆኖ ግን አሁንም ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር፣ ከዚህ በሽታ ነጻ ነው ማለት አይደለም። ስለሆነም በስፖርት ሜዳ ላይ ሁሉ በተለይም እግርኳስ ጨዋታ ላይ ይህ የዘረኝነት በሽታ ደጋግሞ ይንጸባረቃል። አልፎ አልፎም ከአፍሪቃ በመጡ ወይንም እዚህ በተወለዱ ጥቁር ተጫዋቾች ላይ የዘረኝነት ስድቡ ሲበዛ፣ አእምሮ ያለው ዳኛ ጨዋታውን አልመራም ብሎ እስቲያቋርጥ ድረስ ሁሉ ያጋጥማል። በቅርቡ እንደሆነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ፣ በአንድ የጠዋት የቴሌቪዥን የስፖርት ሪፖርት ላይ እንደተዘገበው፣ አንድ የክለቡ ባልደረባ የሆነው ተጫዋች፣ አንድ ጀርመን ሀገር የተወለደ ጥቁር ጓደኛው ላይ የሚሰነዘረውን ዘረኝነት አስመልክቶ፣ በፌስቡክ(Facebook) ላይ፣ ለአስነዋሪዎቹ የዘርኝነት ስድቦቹ እንደሚከተለው ይመልሳል
„እናንት ቅጥ ያጣችሁ ተሳዳቢዎች፣ ለመሆኑ፣ የናንት የአእምሮ ልካችህ (አይ ኩ/ IQ)፣ እኔ ጥዋት ጥዋት ዳቦዬን ከማሞቅበት መሳሪያ (Toaster) ያነሰ እንደሆን ታውቃላችሁ!? „ ፣ ሲል ሳያሽሞነሙንና ዙሪያ ገደሉን ሳይሄድ እቅጩን ነገራቸው።
በደቂቃ ውስጥ ይህን ያነበቡም የሰሙም፣
"እነዚህ ዘረኞችን እንደዚህ እቅጩን ካልነገሯቸው አደብ አይገዙም"፣ ሲሉ፣ በ ሺ የሚቆጠሩ ጓደኞቹና ከስፖርትም ሆነ ከሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የሚገናኙ ሰዎች ሁሉ፣
"እግዚአብሄር ይስጥህ! እንደዚህ እውነቱን ሳታድበሰብስ መናገርህ !"፣ ብለው ደገፉት አመሰገኑት አጀቡት!
ከዚያም ውይይቱ ደርቶ፣ ይህ አስተዋይ ሰው፣ እስፖርተኛው፣ እንዲህ ሲል ደመደመና ውይይቱን ዘጋው።
„ዘረኝነት፣ የአቋም፣ የሀሳብ ልዪነት አይደለም! „2
„ዘ ረ ኝ ነ ት፣ ወ ን ጀ ለ ኝ ነ ት ነ ው!“ ብሎ አሳረፈን!
ይህ ትልቅ ሀ ቅ ነው! ከብዙ የሚያንከራትት ትንተናና ታሪክ ያላነሰ እውነቱን ፍጥጥ አድርጎ የሚያሳየን ነው!
ዛሬ በኛ የኢትዮጵያ እውነታ ውስጥ ያለውና አቆብቁቦ መረን ሊለቅ የተሰናዳው እውነትም ይህ ነውና፣ ይህን የሚያራምዱትም ሆነ በዚህ ፈር ተጉዘው፣ ከየትም መጡ፣ ፈለቁ፣ ሄዱ፣ ቆዩ፣ ከማንም በለጡ አስናቁ፣ ሥልጣን ተከናነቡ አጡ፣ ኖሩ አሸነፉ ተሸነፉ፣ ተጎዱ ጎዱ፣ በዘረኝነት ተጠምቀው፣ ዛሬ ሀገሪቱን ለመዓት፣ ህዝቡን ለመታላለቅ የሚደግሱ ሀይሎች፣ ይህን ሀቅ፣ ነገ ዛሬ ሳይሉ እንዲያውቁት ይገባል። ይህ እውነታ እሩቅ አይደለም፤ ከትላንት ወዲያ ዓለም አይቶታል፤ ትላንት አፍሪቃ ቅምሶታል! ዛሬም በመጠኑ በየአምባው የሚፈጸመው፣ የሚነገረው፣ የሚዛተው፣ ያደባባይ ምስጢር ነው፣
ዘረኝነት የአቋም ልዩነት አይደለም!
አዎ! ዘረኝነት ወንጀል ነው!
ይህ የወንጀል እሳት ከመቀጣጠሉ በፊት፣ አስተዋዩ ኦባንግ ሜቶ እንዳለው፣
ዋስትናችን እርቅ ብቻ ነው!
“እኛ የእሳት አደጋ ብርጌድ የለንምና ዋ!!‘‘
ስለሆነም፣ በዚህ አኳያ፣ ከሁሉም ወገን ያገባኛል፣ ይገባኛል የሚለው ያስተውል፣ ሁሉም አደብ ይገዛ።
„ለ ሃገር ሰው፣ የ„መድሃነ፥ኢትዮጵያ„ ደወል፣/1 ይስተጋባ፣ እውነቱም ይሰማ!“ (ለማንበብ ይጫኑ)፣
እንተባበር ፣ ሁላችንም ከዳር እስከዳር አብረን እናስብ። ሀና አሬንድት / Hanna Arendt/ 3 የፖለቲካ ፈላስፋዋ፣ ሰለዘረኝነት ታመራምራ ጨምቃ ስታስተምርም፣ ያለችው ይህንኑ ነው።
„ዘረኝነት ማለት፣ ማሰብ ማቆም ነው!“ ብላ ነበር! ትክክል ነው!
ስለዚህ ባጭሩ፣ ሌባ ጣትን ወዲያና ወዲህ ከመቀሰር ይልቅ፣ ጣቶቻችንን ሰብሰብ አርገን በአንድነት
ለደግ ጊዜ እናስብ፣ እንታገል!

„ለ ሃገር ሰው፣ የ„መድሃነ፥ኢትዮጵያ„ ደወል፣/1 ፣ እውነቱም ይሰማ!“

No comments: