Sunday, August 25, 2013

መንግስትን ከድተው ከአገር የሸሹት አቃቢ ሕግ በርካታ ሰነዶችን ይዘው ነው የሸሹት!

መሪዎቻችን ነገ ፍ/ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል!

እሁድ ነሐሴ 19/2005
መንግስትን ከድተው ከአገር የሸሹት አቃቢ ሕግ በርካታ ሰነዶችን ይዘው ነው የሸሹት!

ነገ ሐምሌ 20/2005 መሪዎቻን ፍርድ ቤት እንሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡ ከአንድ ወር በላይ ለሚርቅ ያህል ወቅት ተቋርጦ የነበረው የመንግስታዊው ፍርድ ቤተ ችሎት ነገ እንደሚቀጥል ተገምቷል፡፡ የአቃቤ ሕግን የሀሰት ምስክሮች በተራዘመ ወቅትና የተከሳሽ ቤተሰቦች፣ ጋዜጠኞች እና ዲፕሎማቶች በማይገቡበት በዝግ ሲያስደምጥ የነበረው ችሎት የሰነድ ማስረጃዎችን መመልከት ከጀመረ በኋላ ነበር የተቋረጠው፡፡ በሰነድ ማስረጃዎቹ በዳያስፖራ ሙስሊሞች የተዘጋጁ ዶክመንተሪ ቪዲዮዎች የቀረቡ ሲሆን ሆኖም ቪዲዮዎች የመንግስትን ክስ ውድቅ በማድረግ በተቃራኒው የመሪዎቻችንን ሕጋዊነትና የጥያቄያችንን መሰረታዊነት አመላካች ሆነው ታይተዋል፡፡ በወቅቱ በነበረው ችሎት አቃቤ ሕግ ‹‹ያሳየሁት ቪዲዮ በጭብጥነት እንዳይያዝብኝ›› ብሎ እስከመጠየቅም ደርሶ እንደነበርም ተገልጿል፡፡

ነገ ነሀሴ 20 ይጀመራል የተባለውና እስከ ነሀሴ 24 ይዘልቃል በሚል ቀጠሮ የተያዘለት ችሎት ቀጠሮው ከመሰጠቱ በፊት ቀዳሚው ችሎት በድንገት የተቋረጠ ሲሆን፤ ችሎቱ የተቋረጠው ፍርድ ቤት ሳይቀረብ ከዳኞች ቢሮ መጣ በተባለ ውሳኔ ነው፡፡ ችሎቱ በተደጋጋሚ ግዜ በአቃቤ ሕግ ጥያቄ መሰረት ሲቋረጥና ሲቀጥል የመቆየቱ ዋነኛ መንስኤ ከምስክር እጦትና ለማስረጃነት የሚቀርብ ሰነድ ካለመኖሩ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ አቃቤ ሕግ ፍርድ ቤት አቀርባለሁ ካላቸው 197 ምስክሮች ፍርድ ቤት ማቅረብ የቻለው ከ80 የማይልቅ ሰው ብቻ ሲሆን፤ ይህም በከባድ ጥረት እና በተራዘመ ቀጠሮ በመታገዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአቃቤ ሕግ የሀሰት መስክሮች ምስክርነታቸውን ከመስጠታቸው በፌት በማእከላዊ ሀላፊዎች ቢሮ በፕሮጀከተር የታገዘ ስልጠናም ይሰጣቸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከአገር የኮበለሉት አቃቤ ሕግ ቴድሮስ ባህሩ ሲሸሹ ከመሪዎቻችን ክስ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰነዶችን ይዘው መውጣታቸው ታውቋል፡፡ ‹‹ባላመንኩበት እና ንጹህን በሚወነጀሉበት ችሎት ሕሊናዬን ሽጬ መቅረብ አልሻም›› በሚል አሜሪካ የገቡት እኒሁ አቃቤ ሕግ በመንግስት ተገደው እንጂ ክሱን ለማቆም ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ለወዳጆቻቸው ሲናገሩ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ የመልቀቂያ ጥያቄ ለመስሪያ ቤታቸው አስገብተውም መስሪያ ቤታቸው ፍትህ ሚኒስቴር ‹‹የያዝከውን ጉዳይ ስትጨርስ ትለቃለህ›› የሚል ምላሽ ሰጥቷቸው እንደነበር ተመልክቷል፡፡

No comments: