Tuesday, December 15, 2015

መንግስት በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው አመፅ ካቅሙ በላይ መሆኑን አመን ።

በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት በፈጠሩ ኃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

ህዳር 23፣ 2008
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ሊቀላቀሉ  ነው በሚል  መሰረት የሌለው ወሬ በሚያናፍሱ ሀይሎች ላይ እርምጃ  እንደሚወስድ የኦሮሚያ  ክልላዊ  መንግስት አስታወቀ።
የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው  ኃይሎች  በክልሉ  ላይ በማተኮርና በሽብርተኝነት ከተፈረጁ  ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና በፀረ ሰላም ሚዲያዎች የሀሰት ወሬ በመንዛት ሁከት ለመፍጠር ሲያደርጉት የነበረው ጥረት በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ  የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ለኢብኮ በላከው መግለጫ አመለክቷል።
የከሰሩ የፖለቲካ ኃይሎችና በአሸባሪነት የተፈረጁ  ድርጅቶች በጋራ በመሆን ከሰሞኑ በተለያዩ ፀረ ሰላም ሚዲያዎች ባሰራጩት የሀሰት ወሬ  በኦሮሚያ የተወሰኑ ዞኖችና ወረዳዎች እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁከት ተፈጥሯል፡፡
በዚህ ድርጊታቸውም ለንብረትና ለሰው ህይወት ህልፈት ቀጥተኛ ተዋናይ በመሆን ላይ ይገኛሉ ብሏል መግለጫው፡፡

ለሁከት ተግባራቸው የተጠቀሙት አጀንዳ፤ የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን  በማስተር ፕላን ስም ለመቀላቀልና የኦሮሚያን ከተሞች በዘመናዊ አሰራር ለመምራት በክልሉ የወጣውን የከተሞች  አዋጅ  የኦሮሚያን ከተሞች ለፌዴራል ለመስጠትና የኦሮሚያን መሬት ለማስቆረስ ነው የሚል ፍጹም ከእውነት የራቀ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ነው ሁከቱን ያስነሱት ብሏል ቢሮው ፡፡
የጥፋት ኃይሎች እንደሚያናፍሱት ህገመንግስቱንና ፌዴራላዊ አወቃቀሩን  በመጣስ  የኦሮሚያን መሬት አሳልፎ ለአዲስ አበባ የመስጠት፤ አርሶ አደሩንም የማፈናቀል ዓላማ ጨርሶ ሊኖረው እንደማይችልም አትቷል።
የክልሉ ከተሞች አዋጅም ከጋራ ልማት እቅዱ ጋር የማይገናኝና ዓላማውም ለክልሉ ከተሞች የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ቀጥተኛ ምላሽ ለመስጠት፤ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊቶችን ለመዋጋት፤ የሚሰበስቡትን ገቢም ለራስ ልማት የሚያውሉበትን አሰራር ለመፍጠር፤ የከተሞችና የገጠሩን እድገት በማስተሳሰር ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማስገኘት ያለመ ብቻ ነው ብሏል፡፡
በተወሰኑ አንዳንድ የክልሉ  አካባቢዎች ባሉ  የትምህርት ተቋማት የተፈጠረው የሁከት ድርጊት በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞንና በምእራብ ወለጋ ጨሊያ ለሶስት ሰዎች ህይወት መጥፋት መንስኤ ሆነዋል፡፡
በጸጥታ ኃይሎች ላይ ድብደባ ከመድረሱም ባሻገር በመንግስትና የግለሰቦች ንብረት ውድመትም ደርሷል፡፡
በተፈጠረው ሁከት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የክልሉ መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ  ለተጎጂ ወገኖች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
የተፈጠረው ሁከት በአሁኑ  ጊዜ  በቁጥጥር ስር መዋሉን የገለፀው የክልሉ መንግስት፣ የጥፋት ሀይሎቹ ለፈጠሩት ሁከትና ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ እንደሚሆኑና ከጥፋታቸው በአፋጣኝ እንዲሰበሰቡ መንግስት ያሳስባል ብሏል መግለጫው፡፡
መንግስትና ሕዝብ የጀመሩትን ፀረ ድህነት ትግል እንደማይደናቀፍ በመግለፅ የእነዚህን የጥፋት ኃይሎች እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ በአንድነት እንዲቆሙና የፀረ ድኅነት ትግሉን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪውን ያቀርባል ብሏል የኦሮሚያ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት።
Source: ebc.et

No comments: