Saturday, December 19, 2015

“የተረገመ አዙሪት”

ሰላማዊ ተቃውሞ፣ ከፖሊስ ጋር ግጭት፣ ከዚያ ረብሻና እስር፣ ቃጠሎና ግድያ... ከዚህ አሳዛኝ የጥፋት ሰንሰለት መላቀቅ ያቃተን፤ መውጫ የሌለው አዙሪት የሆነብን ለምንድነው?
እንዲህ አይነት ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር፤ መንግስት እየደጋገመ የሚናገረው ነገር አለ። ቅሬታዎችን ማቅረብ፣ ተቃውሞን በሰላም መግለፅ፣ ተፈጥሯዊ መብት ነው ይላል - ሁልጊዜ። እና፤ መንግስት ይህንን መብት ከምር የሚያከብር ከሆነ፤ ለምን... ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ረብሻና ግድያ ይሸጋገራል?
በየጊዜው የሚፈጠሩ ቅሬታዎችንና ተቃውሞዎችን፣ አንድ በአንድ በቀጥታ እያስተናገደ ምላሽ ለመስጠትና ለማስተካከል ቢተጋ ኖሮ፤ ችግሮችን ለመፍታት ከማገዝ አልፎ፤ ረብሻ የማይነካካው ሰላማዊ  ተቃውሞ እንዲለመድ ይረዳ ነበር፡፡ 
መንግስት ይህንን ሃላፊነቱን አልተወጣም፡፡ ስልጡን የፖለቲካ ባህል እገነባለሁ እያለ ለአመታት ቢናገርም፤ ከነባሩ አዙሪት አልወጣንም፡፡ 

ነገር ግን፤ መንግስት፣ ሰላማዊ ተቃውሞን ለማስተናገድ ጨርሶ የማይፈልግ ቢሆንም እንኳ፣ በዚህም ሃላፊነቱን ባለመወጣት ዋና ተጠያቂ ቢሆንም እንኳ፣ እኛስ በራሳችን አቅም፣ ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ብጥብጥ እንዳያመራ መከላከል አንችልም? 
መቼም፣ አብዛኛው ሰው፣ ጨዋ ነው። የተቃውሞ ድምፅ ለማሰማትና አቤቱታ ለማቅረብ፣ ወደ አደባባይ የሚወጡ ብዙዎቹ ሰዎችም፣ በአመዛኙ የሰውን ሕይወትና ንብረት ለመጉዳት አይፈልጉም። ታዲያ፣ ለምንድነው በየጊዜው፣ እንዲህ አይነት ቀውስ የሚፈጠረው?
እዚህ ላይ ችግር አለ። አብዛኞቹ ሰዎች  ጨዋ ቢሆኑም፣ የሰውን ሕይወትና ንብረት ለመንካት ፍላጎት ባይኖራቸውም፤ በሰላማዊ ተቃውሞ መሃል፤ ዝርፊያንና ጥቃትን ለማስቆም ይቸገራሉ። በሌላ አነጋገር፤ መዝረፍና ማቃጠል ለሚፈልግ ሰውጥሩአጋጣሚ ይሆንለታል። ከዚያም አልፎ ራሱን፤ዋና የነፃነት ታጋይ፣ ዋና ተቆርቋሪ፣ ዋና ተወካይአስመስሎ ስለሚሾም፣ተው የሰው ንብረት አትዝረፍ፣ አታቃጥልብለን በድፍረት አንጋፈጠውም። እንዲያውም፣ አለቃ ወይም መሪ ይሆንብናል። 

አንድ መጥፎ ሰው፤ ነገሩን ሁሉ የሚረብሽብን፤ አድራጊ ፈጣሪ የሚሆንብንና ወደ ጥፋት አቅጣጫ የሚመራን፣ አለምክንያት አይደለም። እሱን ለመገሰፅና ለማረም ከሞከርን፤ከሃዲ፣ ሰርጎ ገብ፣ ተብለን አጣብቂኝ ውስጥ እንዳንገባ እንሰጋለን፡፡ከሃዲ... ያዘው፣ ፈንክተውብሎ ቢያነሳሳብን፣ በዚያ ግርግር መሃል፣ ምን ሊፈጠር እንደሚችልና ምን ሊደረስብን እንደሚችል ለመገመት ያስቸግራል።ወደ ጥፋት መንገድ አንሄድም፤ ሰላማዊ ተቃውሟችንን አትረብሽብንየሚል ትችትንም ሆነ ተግሳፅ መስማት፣ እንደ ጥቃትና እንደ ሽንፈት ይቆጥረዋል - ትችታችን ትክክለኛና ተገቢ ቢሆንም እንኳ። ግን፣ እንዲያው፣ ትችታችን ተገቢ ባይሆንስ? ትችት ስለተሰነዘረበት ብቻ... “ያዘው ፈንክተው”...? 
ይሄማ፣ አምባገነን መንግስት ከሚፈፅመው አፈናና ረገጣ በምን ይለያል?
አዙሪቱ ይህንን ይመስላል።

የመንግስት ጭፍን ፕሮፖጋንዳንና ጥፋትን፣ አፈናንና ጉልበተኝነትን ለመቃወም፤ እንከን የሌለው ትክክለኛና ጥርት ያለ ሰላማዊ ተቃውሞ ለማሰማት ብንችል እንኳ፤ እዚያው ከመሃላችን አንድ ሁለት መጥፎ ሰው አይጠፋም። ስልጣን ባይኖረውም፣ ትንሽአምባገነን ሊሆንብን ይሞክራል፡፡ እሱ ከሚነግረን ወሬ ውጪ፤ ለየት ያለ አንዳች መረጃ መስማት ያንጨረጭረዋል፡፡ አንዳች የተለየ የአስተያየት አማራጭ ለማየትም አይፈልግም። አለመፈለግ ብቻ አይደለም፡፡ በከሃዲነት እንድንፈረጅ ማድረግ እንደሚችል ያውቃል፡፡ እናም ጭፍን ስሜትን በማራገብና በአሉባልታ፣ በዛቻና በጉልበት፣ ዙሪያውንዝምበማሰኘት፣ አለቃና መሪ ሆኖ ያርፈዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ሰው እንደሚኖር ስለምናውቅና ስለምንሰጋም ነው፤ ጭፍን ስሜቶችንና መጥፎ ድርጊቶችን ለማስቆም ብዙም ለመጣር የማንነሳሳው። እናም፤ ሰላማዊው ተቃውሞ፣ በአንድ በሁለት ሰው ተረብሾ ወደ ግርግር ይቀየርብናል። ይሄ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያትስ?
የተቃውሞ ድምፃችንን ለማጉላላትና እንዳይደበዝዝ መመኘት ተገቢ ቢሆንም፤ ለዚህ በትጋት ከመጣጣር ይልቅ፣ ወደቀላልየአቋራጭ መንገድ ካዘነበልን፣ ለስህተት እንጋለጣለን፡፡ እንዴት በሉ፡፡  

አንደኛ ነገር፤ የተቃውሞ ድምፅን የሚያበርድና የሚያደበዝዝ ከመሰለን፣ እውነተኛ መረጃንና ምክንያታዊ አስተያየትንም ጭምር ችላ ብለን፣ ሰምተን እንዳልሰማን እናልፋለን። [ከድካምና ከጥረት የሚገላግል አቋረጭ መንገድ ያገኘን ይመስለናል። ግን፤ መዘዝ አለው። በዚሁ ምክንያት፣ አስተዋይ፣ ብልህና ቀና ሰዎችን እያገለልን እንደምንሄድ አናውቅም] ይህም ብቻ አይደለም።
የተቃውሞ ድምፅን ለማማሟሟቅና ለማድመቅ የሚረዳ እስከመሰለን ድረስ፣ ተገቢ ላልሆኑ ነገሮችም ጭምር ቦታ መስጠት እንጀምራለን፡፡ ለምሳሌ፤ አንድ ሁለት ሰዎች በጭፍን የሚያስተጋቡትን የውሸት መረጃም ሆነ የጥፋት አዝማሚያ፣ ለማስተካከልና ለማረም ከመሞከር ይልቅ፣ አይተን እንዳላየን ማለፍ ይቀለናል። [ለጊዜው፣ቀላልነው። ነገር ግን፣ እነዚያ በጭፍን ስሜት የተዋጡ አንድ ሁለት ሰዎች፣ ራሳቸውን አለቃና መሪ አድርገው በእኛው ላይ እንዲሾሙ፣ እድል እንከፍትላቸዋለን።] ለዚህም ነው፤ በመጀመሪያው ቀንና በማግስቱ፣ ሰላማዊ የነበረው የተቃውሞ ድምፅ፣ ቀስ በቀስ በረብሻ እየተዋጠና እየተወረሰ እንዳይሄድ ለመከላከል የምንቸገረው።
አንዴ መበላሸት ከጀመረ በኋላ ደግሞ፤ እየከበደና እየተባባሰ ይቀጥላል፡፡ 

ጭራሽ፣ይሄ አገር ወዴት እያመራ ነው?” የሚል ጥርጣሬ እስኪያድርብን ድረስ፣ አገር ምድሩ ይቀወጣል።የተሻለ ነገር ያስገኝ ይሆናልብለን የጀመርነው ነገር፤ ከቀድሞው ወደ ባሰ ውጥንቅጥ እንዳያወርደን መስጋት ይመጣል። ያኔ፤ ለጉልበተኛ ባለስልጣን፣ መንገዱ ተመቻቸለት።
ከሰላማዊ ተቃውሞ ይልቅ፣ ረብሻ የሚመቻቸው ባለስልጣናት አሉ። ለምን? አሃ፤ ጥያቄዎችንና ትችቶችን የማስተናገድ ጣጣን ያስቀርላቸዋል፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞ በረብሻ ከተወረሰበቃ፤ በማንኛውም መንገድ፣ (በፕሮፓጋንዳ፣ በዛቻና በጉልበት)... ሁሉንም ሰው ፀጥ ለማሰኘት፣ በቂ ሰበብ ይሆንላቸዋል። በሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ሰዎችን ብቻ በህግ ከመዳኘት ይልቅ፤ በዚህችው አጋጣሚና ሰበብ፣ አገሬውን ሁሉ ዝም ለማሰኘት፣ የትችትና የተቃውሞ ድምጽን ጨርሶ ለማጥፋት ይሞክራሉ።

ፕሮፓጋንዳውን፣ አፈናውን፣ ጉልበተኝነቱን፣ ከቀድሞው የባሰ ለማድረግ የሚጠቅም ማመካኛ ይሆንላቸዋል - ረብሻው። ጥያቄዎችን፣ አቤቱታዎችንና ትችቶቸን እያስተናገዱ፣ ስህተቶችን ለማስተካከልና ጥፋቶችን ለማረም ከመትጋት ይልቅ፤ ሁሉንም ሰው ዝም ማሰኘት  ይቀላቸዋል። ለጊዜው፣ቀላልይመስላል። ግን፤ መፍትሄ አይሆንም። ባለስልጣናትና መንግስታት፣ በሰበብ አስባቡ፣ገናናእየሆኑ መሄድ፤ቀላልመስሎ ቢታያቸውም፤  ብዙም አያዛልቅም። ቢሆንም ግን፤ ሰበብ ተገኘ ተብሎ፣ገናናለመሆን መሯሯጥ፤ በየአቅጣጫውና የየጊዜው፣ በተደጋጋሚ የሚታይ፣ የተለመደ የበርካታ ባለስልጣናት  ባህርይ ነው። ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር፤ ለቀውሱ ሁነኛ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ፤ በዚያ ሰበብ፤ ከዜጐች ላይ ገናና ለመሆን ይገለገሉበታል፡፡ 
በአገራችን ብቻ ሳይሆን፤ ደረጃው ቢለያይም፣ በሁሉም አገራት፣ የዘመናችን ሦስቱ ዋነኛ አለማቀፍ የቀውስ ምንጮችን ተመልከቱ። 

በመንግስት እልፍ ቁጥጥሮችና ጫናዎች ሳቢያ የሚፈጠርየቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ በአለም ዙሪያ፣ ከድሃ እስከ ሃብታም አገራት፤ ሁሉንም እያናወጠ አይደል? ግን፤ ጥፋተኞቹ መንግስታት ብቻ አይደሉም፡፡ እኛም እንተባበራቸዋለን፡፡ 

በአንድ በኩል፤... የግል ኢንቨስትመንትንና ቢዝነስን፣ የግል ስኬትንና ብልፅግናን፣ በአድናቆትና በአርአያነት ለማየት የሚቸገር ኋላቀር ባህል በአገራችን ሞልቷል። በሌላ በኩል ደግሞ፤... በዚህም በዚያም በአየር ባየር አልያም በሙስና፣ በድጐማም ሆነ በልዩ ድጋፍ ... (ያለ ስራ እና ያለ ጥረት) ሃብት ለማግኘትና ተጠቃሚ ለመሆን መዋከብም የተለመደ ነው፡፡ እነዚህ አዝማሚያዎች፤ በብዙ ዜጐች ዘንድ የሚታዩ ስህተቶች ናቸው፡፡ የመንግስት ምላሽስ?

መንግስት፤ ቢዝነስን የሚያናንቅን ባህል ለመግታትና የአየርባየር ወከባን ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ ወደ ነፃ ገበያ ስርዓት ለመጓዝ ከመትጋት ይልቅ፤ በዚሁ ሰበብ፤ ከነአካቴው ቢዝነስንና ነፃ ገበያን በእንጭጩ የሚቀጭ፣ የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን፣ የገደብና የክልከላ፣ የታክስ ጫናና የመዋጮ ዘመቻ ማካሄድ ቀላል ይሆንለታል።

ያው፤ ቢዝነስ ሳይስፋፋ ደግሞ፣ ከስራ አጥነትና ከድህነት መላቀቅ አይቻልም። አሳዛኙ ነገር፤ በስራ አጥነትና በድህነት እየተማረርን፣ ለዚህ ችግር መፍትሄ እንዲፈለግለትድማፃችንን ለማሰማትአደባባይ ብንወጣ፤ ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚወጣው ድምፅ፣የሸቀጦች የዋጋ ቁጥጥር ይደረግ”... የሚል መፈክር ይሆናል። 

መንግስት ይህንን አግኝቶ ነው?
በዚሁ ሰበብ፤ ቢዝነስ ላይ፣ ተጨማሪ ጫናና ቁጥጥር በማወጅ፣ ይበልጥ የመንግስትን ገናናነት ለማግዘፍ የሚመኝ ባለስልጣን፣ እንደሚኖር አትጠራጠሩ። በግል ኢንቨስትመንትና በቢዝነስ ላይ ጭፍን ጥላቻን እያራገብን፣ መንገዱን ለመንግስት አመቻቸንለት ማለት ነው። እናም፣ ቢዝነስ እየተደናቀፈ፤ ከስራ አጥነትና ከድህነት ጋር እንደተቆራኘን እንቀጥላለን።
አዙሪት ነው። ለኛ አይበጅም። ለመንግስትም አያዛልቀውም። ቢዝነስን እየገታ፣ገናናመሆን፣ ውሎ ሲያድር መዘዙ እየከፋ ይሄዳል። በጊዜ ካልባነነ፣ መውደቂያው ይሆናል።
ሁለተኛና ሦስተኛ የቀውስ ምንጮች፤ የሃይማኖት አክራሪነትና የዘረኝነት አባዜዎች ናቸው፡፡ በአንድ በኩል፣ መንግስታት፣ የአክራሪነት ሽብርንና የዘረኝነት ግጭትን በቀጥታ ከመከላከል ይልቅ፤ በዚሁ ሰበብ፣ የዜጎችን ቅሬታ፣ ትችትንና ሰላማዊ ተቃውሞን አፍነው ዝም ለማሰኘት፣ ይጠቀሙበታል። በአገሬው ላይገናናለመሆን፣ አስተማማኝ ማመካኛ ይሆንላቸዋል።አገርን ከሽብር ለመታደግ፤ ሕዝብን ከዘረኝነት እልቂት ለማዳን”...እያሉ፤ ያሻቸውን ነገር ለማድረግ ይሞክራሉ።

አሳዛኙ ነገር፤ እኛም፣ እንመቻችላቸዋለን። የተቃውሞ ድምፅን ለማድመቅ የሚጠቅም እየመሰለን፣ ወይም ደግሞ የተቃውሞ ድምፅ እንዳይደበዝዝ በመስጋት፣... በፅናትና በትጋት ትክክለኛ መላ ከማበጀት ይልቅ፤ ሃይማኖትንና ተወላጅነትን ከፖለቲካ ጋር የማደበላለቅ አዝማሚያ፣ አቋራጭ መፍትሄ ሆኖ ይታየናል፡፡ ወይምጊዜያዊ ችግር ነውብለን በቸልታ እንቀበለዋለን።
በዚሁ አዝማሚያ ለመንሸራተት፣ አእምሯችን ፈቃደኛ ባይሆን እንኳ፤ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን... አክራሪነትንና ዘረኝነትን የሚያስተጋቡ መጥፎ ሰዎችን በዝምታ ለማለፍ፣ ወይም እንደ ጊዜያዊ ችግር አይተን ቸል ለማለት ይዳዳናል። ነገር ግን፣ አንድ ሁለት ሰው የሚያስተጋባው የዘረኝነት ወይም የአክራሪነት መርዝ፣ ከጎናችን ተሰልፎ በዝምታ ስናልፈው፤... ለአፍታ በአዳማቂነት አገልግሎ፣ በራሱ ጊዜ የሚከስም፣ ተራ ችግር አይሆንልንም።

በተገላቢጦሽ፣ ዋና ጉዳያችንን ሁሉ ጠቅልሎ እየዋጠና እየቀበረ፣ ከመክሰም ይልቅ እየተግለበለበና እየተቀጣጠለ ለመስፋፋት እድል ያገኛል፡፡ ብዙም ሳይቆዩ፤ በሃይማኖት ተከታይነት ወይም በዘር ወደ ማቧደን ይሸጋገራሉ፤ ከዚያም በየፊናቸው የየቡዱኑ አለቃ፣... አድራጊ ፈጣሪ ይሆኑብናል። 
እንዲህ፣ ነገር እየተበላሸ፣ አገሬው ወደ መናወጥ እያመራ፤ ብዙዎቻችንየባሰ መጣብለን መስጋት ስንጀምር፤ መንግስት ምን ያደርጋል?

የአክራሪነትን ሽብር፣ የዘረኝነትን ግጭት እየተከላከለ፤ የዜጎችን ቅሬታና ሰላማዊ ተቃውሞ ለማስተናገድ፤ እንዲሁም... የዜጎችን ነፃነትና መብት ለማስከበር መትጋትና መጣር ይችላል። ግን፤ ይሄ አድካሚ ነው። ከዚያ ይልቅ፤ አክራሪነትንና ሽብርን፤ ዘረኝነትንና ግጭትን በመዋጋት ሰበብ፤ ቅሬታዎችንና ተቃውሞዎችን በሙሉ እያፈነአይነኬ ገናና መንግስትለመሆን መሞከር ይቀላል።
በእርግጥ፤ቀላልነቱለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። አፈናው ሲደራረብና የዜጎች እሮሮ ሲባባስ፤ ውሎ አድሮ፣ የተቃውሞ ድምፅ ግንፍል ብሎ መውጣቱ አይቀርም። ግን፤ ምን ዋጋ አለው? ያቺ ታፍና የነበረች የተቃውሞ ድምፅ፣ እንድትጎላ በመጓጓትና እንዳትደበዝዝ በመስጋት፤ መንግስትን የሚቃወም ማንኛውንም ነገር (አክራሪነትንና ዘረኝነትንም ጭምር...) የማስተናገድ አዝማሚያ ይሰፋል። የአቋራጭ መፍትሔ ምርኮኞች እንሆናለን፡፡

ያው፤ በበርካታ አገራት እንደታየው፤ የዜጎች የተቃውሞ ድምፅ፣ በአክራሪዎች ወይም በዘረኞች ድምፅ እየተዋጠ፣ ነገሩ ሁሉ ይቃወሳል። ብዙ ሰዎች በስጋት ይጨነቃሉ።
ያኔ፣ የመንግስት ስራ፣ አክራሪነትንና ዘረኝነትን መከላከል ሳይሆን፣ እግረመንገዱን አገሬውን በአፈናና በጉልበት ዝም ለማሰኘት መሯሯጥ ይሆናል። ኡደቱ ይቀጥላል። የታሪክ ጉዞ ሳይሆን፣ የታሪክ አዙሪት ውስጥ እየተሽከረከሩ፤ መከራን እየደጋገሙ ማየት!

Source: addisadmassnews

No comments: