Tuesday, December 15, 2015

ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ያነሳውን የትግል ችቦ ሌላው ኢትዮጵያዊም ተቀብሎ ያበራል!


Protest in Ethiopia, Oromia region

ገለታው ዘለቀ
የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ከዚህች ከኣዲስ ኣበባዋ የመሬት ነጠቃ ጥያቄ በጅጉ ገዝፎ የሄደ ነው። ከፍተኛው ጥያቄ የመልካም ኣስተዳደር ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ ህወሃትይህን ዘረኛ ፖለቲካውን ተሸክሞ ኣዲስ ኣበባ ከገባ በሁዋላ በተለይ ኦሮሞንና
 ኣማራን ጸጥ ኣድርጎ ለመግዛት የተጠቀመው ዘዴ በነዚህ ክልሎች ውስጥ ከታች እስከ ላይ ያሉትን ባለ ስልጣናት በኣልተማሩና የማስተዳደር ችሎታ በሌላቸው ነገር ግን ታዛዥ ብቻ በሆኑ ሰዎች መሙላት ነበር። ወያኔዎች ይህን ያደረጉበት ምክንያት ህወሃት ይዞት የተነሳው ጥያቄ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ ባለመሆኑና ዋናው ዓላማው የሆነ የራሱን ክብ ለመጥቀም በመሆኑ እነዚህን ክልሎች ኣፍኖ የሚይዝለት ኣስተዳደራዊ መዋቅር ስላስፈለገው ነው። ህወሃት ያሻውን ያደርግ ዘንድ “የራሴ” የሚለውን ክብ ለመጥቀም ይችል ዘንድ በየክልሉ የራሱን መጠቀሚያዎች መፈለግ ስለነበረበት ነው። በነዚህ ክልሎች ሰው በባትሪ ተፈልጎ የሚሾመው ህወሃት የኣሳቡ እስኪሞላ ድረስ ፈረስ የሚሆኑትን ሰዎች በማግኘት ላይ የተመሰረተ ነበር። የማይጠይቅ፣ የሚፈራ፣ ለጥቅም የሚንበረከክ፣ እውቀት የሌለው፣ በባትሪ እየተፈለገ የሚሾመው ህወሃት ቀድሞ ላሰበው የግል ጥቅም ስራው ኣንድ ራሱን የቻለ ስትራተጂ ኣድርጎ ስለወሰደው ነው። ውሎ ሲያድር ይህ ስትራተጂ ምን ኣመጣ? ከባድ የመልካም ኣስተዳደር ችግር በተለይ በኦሮምያና ኣማራ ክልሎች ኣመጣ። የበቁ የነቁ የኦሮሞ ተማሪዎች ወይ በኦነግ ወይ በተቃዋሚ እየተፈረጁ ተወገዱ። የኦሮሞ ህዝብ ልቡ ኣዘነ። የተማሩ ልጆች እያሉኝ፣ ጥሩ ጥሩ ማስተዳደር የሚችሉ ልጆች እያሉኝ ለምን እንዲህ ኣደራጋችሁኝ? እያለ ኣነባ። ኣማራው ኣካባቢም እንደዚሁ ታዛዡን እየፈለጉ ሲሾሙ በክልሉ ቀልጣፋ ኣገልግሎት ጠፋ፣ ህዝቡ ወደ ወረዳ ወደ ክልል ወደ ዞን ሲሄድ የሚያገኛቸው ባለስልጣናት ችግሩን የማይረዱ ኣንዳንዴም በሚያሳፍር መልኩ ህዝቡ የሚለው እንኳን የማይገባቸው ሆነው ተገኙ። ተራው ሰው የበለጣቸው መሪዎች በየቦታው በመኖራቸው ህዝቡ ከኣመራር ኣካላቱ የሚጠብቀው ነገር ጠፋ። በተለይ የነዚህ የሁለቱ ክልሎች ትልቅ ችግር ይሄ ነው። ህወሃት እነዚህን ክልሎች ከቀጣበት መንገድ ሁሉ በጣም ኣስከፊው ቅጣት ይሄ ነው። በራሳቸው ልጆች በጃዙር ቀጣቸው። በርግጥም ልጆች እያሏቸው የተማሩትን የተሻሉትን እያባረረ በማይሆኑ ሰዎች እንዲተዳደሩ መደረጉ ትልቅ ቀውስን ኣምጥቷል። ህወሃት እነዚህ ሰዎች መሳሪያው ስለሆኑና እላይ ቆልለውት እየሰገዱለት ስለሚኖር ደስ ብሎታል። የመጣው ማህበራዊ ቀውስ ግን ልክ የለውም። ይህ ችግር በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ቢታይም በኦሮምያና በኣማራ ግን የከፋ የከፋ ሆኖ ይታያል። በኣንዳንድ ቦታዎች ህወሃት ስልጣን ሲይዝ የወረዳ ሊቀመንበር የሆኑት ህወሃት ከመምጣቱ በፊት ችሎታ የሌላቸው ጥሩ ምግባር ያልነበራቸው ወዘተ ነበሩ። እነዚህን ሰዎች እየሰበሰበ የቀበሌ ምክር ቤት፣ የወረዳ ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤት እያለ ነው ይሾም የነበረው። ህዝቡ ለጊዜው ይስቅ ነበር። ይሁን እንጂ መራራው እውነት ግን እነዚህ ሰዎች የዚህን ህዝብ እጣ ፈንታ የሚወስኑ ስለነበር ሳቁ ወደ ኣዘን በፍጥነት ተቀየረ። ኣንዳንድ ለምልክት ከየብሄሩ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ደግሞ ህወሃት በኣጃቢ ስም የቁም እስር ኣስሯቸው የህወሃትን ፍላጎት እያስፈጸሙ እንዲኖሩ ተደርገዋል።ይህ ችግር ለብዙ ኣመታት ሲቆይ የመልካም ኣስተዳደር ብሶቱን ኣበዛና እነሆ ዛሬ ህዝቡን በእንባ ኣራጨ።
ኣንዱ የዛሬው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የሚያስተዳድሩትን ህዝብ ጥለው ህወሃትን ቆመው የሚያበሉ የክልሉን ኣስተዳዳሪዎች ማውገዝ፣ ህወሃት የፈጠረው ይህ ራስ ወዳድና ስግብግብ ፖለቲካ እንዳስቆጣቸው ለመግለጽ፣ ለውጥን ለመሻት ነው። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከመልካም ኣስተዳደሩ ችግር በተጨማሪ ኣጠቃላይ የፖለቲካው ኣወቃቀር ህዝቡን ግራ ግብት ኣደረገው። በተፈጥሮ ሃብት፣ በባህል፣ በፖለቲካ ተሳትፎዎች ግልጽ የሆነ ስምምነት የለም። ይሄ ጉዳይ ከፍተኛ ማህበራዊ ምስቅልቅል ኣመጣ። ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን ስትኖር ኣንዳንድ ክፉ ትውስታዎች(memories) ነበሯት፣ ብዙ መልካም ትዝታዎችም(good memories) ነበሯት። የህወሃት ፖለቲካ የቆመው ግን መጥፎዎቹን ትዝታዎች(bad memories) እየመረጠ በነዚያ ላይ ነው ቤቱን የሰራው። ነገር ግን ፖለቲካ ዓላማው በጎ ለውጥን ማምጣት በመሆኑ ለማህበረሰብ ለውጥ እንደ ኤነርጂ ኣድርጎ ሊጠቀምባቸው የሚገባው ጥሩ ጥሩ ትዝታዎችን በማጉላት ነበር። የኛ ፖለቲካ ግን በተቃራኒው መጥፎ ትዝታዎችን በማጉላት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠረው ኤነርጂ ኔጌቲቭ እንዲሆን እየታገለ ነው።ታዲያ ፖለቲካ በመጥፎ ትዝታዎች ላይ ሲቆም ኣንዱ ውጤት ይህ ነው። ቡድኖችን ማጋጨት፣ ብሄራዊ ማንነትን ማኮሰስ ፣ ኣገርን ማስጠላት ስደትን ማብዛት ነው። ይህ ጉዳይ ህዝቡን ውስጡን ጎድቶታል። ፖለቲካ በመልካም ትዝታዎች ላይ ቆሞ እነሱን እያራገበ መጥፎዎቹን ሊያርምና ሊክስ ነበር የሚገባው። ኣለመታደል ሆነብንና የህወሃት ፖለቲካ መጥፎዎቹን እያራገበ፣ ማራገብ ብቻ ሳይሆን ማጣፈጫ ጨው ጨመር እያደረገ የውሸት ታሪክ እየጻፈ ኣበላሸው። ይህ ጉዳይ በጣም ጎድቶናል። ትልቅ ብሄራዊ ስብራትም ኣመጣ።
ኣሁን የህዝቡ ጥያቄ የለውጥ ጥያቄ ነው። ድሃው ህዝብ በቃል የሚገልጻቸውና የማይገልጻቸውን ውስብስብ ችግሮቹን በማስተር ፕላኑ ለመግለጽ ይሞክር እንጂ ብሶቱ የትየለሌ ነው። ትልቁ ብሶት የተበላሸውን የሶሺዮ ፖለቲካ ስርዓት እንዲለወጥ ከመፈለግ ነው። ህዝቡ ለውጥ ያለ ልክ ተርቧል። ጥያቄው ይሄ ነው።ወለጋ ውስጥ ያለውን ኦሮሞ፣ ምእራብ ሃረርጌ ያለውን ኦሮሞ ወዘተ…. ገንፍሎ እንዲነሳ ያደረገው ጉዳይ የመልካም ኣስተዳደር እጦትና ይህን ተከትሎ የመጣው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግፎች ናቸው።
ታዲያ የህዝቡ ጥያቄ የለውጥ ይሁን እንጂ በዚህ የለውጥ ወራት ጊዜ የትግላችንን ፍሬ ሊለቅሙ ከሚጣደፉ ወያኔዎች መጠንቀቅ ኣስፈላጊ ነው። በሃገራችን የሚመጣው ለውጥ ግዙፍ ለውጥ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን እንደገና ኣፍርሶ የሚሰራ መሆን የለበትም። ኢትዮጵያን እንደገና የሚያንጽ ስራ ነው የሚያስፈልገው። ስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ኣንድነት ኪዳን ውስጥ ልንገባ ይገባል። ይህ ማለት ኢትዮጵያን በመገንጠል ሪፈረንደም ወይም በሌላ መንገድ ኣፍርሰን እንደገና እንስራ ወይም እንገነጣጠል ማለት ኣይደለም። ኢትዮጵያን እንደዚህ ለማሳብ ኣይቻልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽ የሆነ የቡድኖች የድንበር ክልልም የለም። እነዚህ ኣሁን ያሉት ዘጠኝ ክልሎች ትናንት ወያኔ የፈጠራቸው፣ እንዳሻው የሰራቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ስትፈጠር ዘጠኝ ክልል ነበረች የሚል ታሪክ የለም። ወያኔ በፈጠረው ኮራብትድ ክልል የመገንጠል ሪፈረንደም ኣይሰራም። ኣገራችን ኣንድ ናት። የተቀየጠው ህዝብ ብዛት ከብሄሮች ቁጥር በልጧል። ወያኔ እንደሚለው ሳይሆን የጋራ ግዙፍ ታሪኮች ኣሉን። የጋራ ሃብት ኣለን። ወንዞቻችን የተፈጥሮ ሃብቶቻችን የጋራ ናቸው።ኣንዳንድ የወያኔ ኣባላት ከዚህ በፊት ጥለውት የነበረውን የመገንጠል ጥያቄ ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ ሲነሳባቸው ሊያነሱ ይችላሉ። ኣምነውበት ባይሆንም ለጊዜው መሸሸጊያ ይሆነናል ከሚል ትግራይን ለመገንጠል ያስቡ ይሆናል። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በቀጥታ ኣይደለም። እንዲህ ኣይነት የህዝብ ተቃውሞ ሲነሳ ይህንን ትግል ሃይጃክ በማድረግ ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያ ኣገሪቱን ኣፍርሰው፣ በተለይ ኣማራውንና ኦሮሞውን ኣባልተው ነው የሚሄዱት። የመገንጠል ጥያቄው ከሌላ ብሄር እንደመጣ ኣድርገው ሌላውን ብሄር በየቤትህ እደር ኣይነት ከበተኑ በሁዋላ የሚያስቡትን ለማድረግ ይሞክሩ ይሆናል። ከዚህ በፊት ኣንስተውት ጥለውት የነበረ ጥያቄ ቢሆንም ወያኔ ኣይታመንምና ይህን ብንገምት ኣይፈረድም። ሃያ ኣምስት ዓመት ሲዘርፉ ቆይተው ኣሁን የመገንጠል ነገር ቢያመጡ ፍጻሜው ምን ይሆናል? የሚለውን ጥያቄ እናዘግየውና እንደዚህ ሊያስቡ ስለሚችሉ ለዚህ ፍላጎታቸው የኦሮሞም ህዝብ ሆነ የኣማራ ወይም የደቡብ እንዲሁም ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመች ኣይሆንም። የኦሮሞ ጥያቄም ሆነ የሌላው ህዝብ ጥያቄ የለውጥ፣ የመልካም ኣስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ናቸው።
የለውጡ ጥያቄ ኢትዮጵያን እንደገና የማነጽ ስራ ነው። ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ ማለት እኛ በቋንቋ የተለያየን ቡድኖች ኣብረን ስንኖር የኣንድ ቡድን የበላይነት ሳይኖር እንዴት ኣብረን በእኩልነት እንኑር? እንዴት ኣድርገን ያለንን ባህል በኣንድ በኩል ወደ ላይ እያሳደግን በሌላ በኩል ወደ ጎን እየተማማርን እንኑር? የቋንቋ ሃብቶቻችንን እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም? እንዴት ኣድርገን የተሻለ ብሄራዊ ማንነት እንገንባ? በኣካባቢያችን ያለውን የተፈጥሮ ሃብት እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም? ፖለቲካዊ ኣሰላለፋችን እንዴት እናድርገው? በሚሉ ጉዳይች ዙሪያ የመግባቢያ ኣሳብ ማምጣትና በዚህ ስምምነት ላይ መተዳደር ማለት ነው መስማማት ማለት:: ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ ማለት ወደፊት ለቡድኖች ሁሉ እኩልነትን የሚያመጣ ኣሳብ ማመንጨትና በዚያ ላይ ኣቋም ይዞ ኣዲሲቷን ኢትዮጵያን መገንባት ነው። በመሆኑም የለውጡ ጥያቄ ሰፊ ነው። ኢትዮጵያውያን ለውጥ ሲያነሱ ኣገራቸውን ለማፍረስ ኣይደለም። ኢትዮጵያ ማለት ኦሮሞ ነው። ኦሮሞ ማለት ኢትዮጵያ ናት። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ነው። ስለሆነም የኦሮሞን ጥያቄ እንደግፋለን። ለውጥ ይምጣና የተሻለ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ማእቀፍ ውስጥ እንግባ። ሁላችን የኦሮሞ ወንድሞቻችንን ጥያቄ ደግፈን ለመልካም ኣስተዳደርና ለዴሞክራሲ እንታገል። በትግላችን ላይም ሆነ በውጤቱ ላይ በኣንድም በሌላም መንገድ ለወያኔ መሰሪ ዓላማ እድል ፈንታ ኣንሰጥም።ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ያነሳውን የትግል ችቦ ሌላው
ኢትዮጵያዊም ተቀብሎ ያበራል!
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያችንን ይባርክ
ገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.com
Source: Ecadforum

No comments: