Sunday, June 19, 2016

የአገራችን-ሦስቱ-ሳጥኖች

 የአገራችን ሦስቱ ሳጥኖች!!
በገንዘብ መግዛት ሀብትን፤ በሥልጣን መግዛት ጉልበትን፣ በውበት መግዛት ፍትወትን፣ በመዋቅር መግዛት ሹመትን ያሳያል። በሐሳብ መግዛት ግን ልህቀትን ያመለክታል። ----”
ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ሳጥኖች አሉ። ሁለቱ ሳጥኖች በጣም ይፈለጋሉ። ስለሚፈለጉ ወይ ይዘረፋሉ፤ ወይ ይሰረቃሉ። አንደኛውን ሳጥን ግን ዞሮ የሚያየው የለም። ሁለቱ በውስጣቸው በጣም ተፈላጊ ነገር አለ ተብሎ ስለሚታመን፤ ሳጥኖቹ በፖሊስ በዘበኛ፣ አንዳንዴም በወታደር ይጠበቃሉ። አንደኛው ሳጥን ግን ጠባቂ የለውም። ውስጣቸው ያለው ነገር ሲጨምር የሚያመጡት ለውጥ አለ ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ሁለቱ ሳጥኖች ቶሎ ቶሎ ይቆጠራሉ። አንደኛው ሳጥን ግን የሚያስታውሰው የለም።
ሁለቱ ሳጥኖች የምርጫ ሳጥንና የገንዘብ ሳጥን ናቸው። አንዱ ውስጥ ሥልጣን፣ ሌላው ውስጥ ገንዘብ አለ። ሥልጣን ያለበትን ሳጥን ፖለቲከኞች ይፈልጉታል። ስለዚህም ይሰብሩታል፣ ይገለብጡታል። ገንዘብ ያለበትን ሳጥን ሙሰኞች ይጓጉለታል። ይሰብሩታል፤ ይገለብጡታል። ሕዝቡም ስለ እነዚህ ስለ ሁለቱ ሳጥኖች ጉዳይ ይከታተላል። ሲዘጉና ሲከፈቱ ኮሚቴ ያቋቁማል። ሲቆጠሩና ሲመዘኑ ማወቅ ይፈልጋል። ሥልጣንና ገንዘብ ስላለባቸው።
ሦስተኛው ሳጥን ግን ከእነዚህ ሁሉ ይለያል። ዘጊ እንጂ ከፋች የለውም። ሠሪ እንጂ ተከታታይ የለውም። በውስጡ ያለውን ነገር ለማወቅ ባለቤቱም፤ ሕዝቡም አይጓጉም። ማንም እንደ ልቡ ያገኘዋል። ግን አይጠቀምበትም። ጥበቃ የለውም፤ ግን ማንም አይሰብረውም። ተመልካች ያጡ ወረቀቶችን በውስጡ እንደያዘ በየግድግዳው ላይ አርጅቷል። ሰዉም በዚህኛው ሳጥን ውስጥ ለማስገባት ብዙም አይፈልግም። እንደ ሁለቱ ሳጥኖች ፈላጊ የለውም ብሎ ያምናልና። ለምን?
ምክንያቱም ሦስተኛው ሳጥንየሐሳብ መስጫ ሳጥንስለሆነ። ዓለምን የቀየረው ሐሳብ ቢሆንም እኛ ሀገር ግን ብዙም ፈላጊ የለውም። መሥሪያ ቤቶችም የተሰጣቸውን ርዳታ እንጂ የተሰጣቸውን ሐሳብ ሪፖርት አያደርጉም። ሀገር የምታድገው፣ የምትለወጠውና የምትሠለጥነው በሐሳብ ነው። ያውም በሰላ ሐሳብ። ያደጉ ሀገሮች ማለትም ታላላቅ አሳቢዎችና ታላላቅ ሐሳቦች ያሏት ሀገር ማለት ናት።
እስኪ አንድ እንኳን የሀገሪቱ መሪ፣ የፖለቲካ ልሂቅ፣ ባለ ሥልጣን፣ ሀገሪቱ ያፈራቻቸውን አሳቢዎች ከመጽሐፎቻቸው፣ ከንግግሮቻቸው፣ ከአባባሎቻቸው በንግግሩ ውስጥ ሲጠቅስ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? እውነት ዐሳቢዎች ሳይኖሩን ቀርተን ነው? ይህች ሀገርስ እንደ ሀገር ለዘመናት የኖረቺው ያለ ሐሳብ ነው? እንዴት ተደርጎ። ነገር ግን ለሐሳብና ለዐሳቢዎች የምንሰጠው ቦታ ኢምንት ስለሆነ ነው። በየቦታው የተጣሉት የሐሳብ መስጫ ሳጥኖች የሚነግሩንም ይኼንን ነው።


No comments: