Wednesday, June 15, 2016

ግብፅ ፖለቲከኞችና ምሁራን በአባይ ግድብ ላይ ጥቃት ማድረስ እንደማራጭ እንዲወሰድ ጠየቁ

የግብፅ መንግስት በመገንባት ላይ ባለው የአባይ ግድብ ላይ ጥቃትን እንደአማራጭ ሊወስድ እንደሚገባ የሃገሪቱ የፖለቲካ አመራሮችና ምሁራን ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸውን የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

በጉዳዩ ዙሪያ ይፋዊ ምላሽ የሰጡት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳምህ ሽክሪ በበኩላቸው በመነሳት ላይ ያለውን አማራጭ ሃሳብ ውድቅ ማድረጋቸውን አስዋት ማሶሪያ የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥቃትን እንደአማራጭ የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ ለንግግር እንኳን የማይቀርብ ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ከአንድ አመት በፊት በስህተት በቀጥታ ስርጭት በቀረበ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የግብጽ ባለስልጣናት በአባይ ግድብ ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይኸው ጉዳይ አሁንም ድረስ በግብፅ ፖለቲከኞች በኩል በመቅረብ ላይ ሲሆን፣ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሹክሪ ከአንድ አመት በኋላ ለጉዳዩ ዳግም ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል።

ኢትዮጵያና ግብፅ ሱዳንን በማካተት ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለመመርመር ጥናት እንዲካሄድ ቢስማሙም ግብጽ ግድቡ የወንዙን ፍሰት ይቀንሳል ስትል ስጋቷን በመግለጽ ላይ ናት።

ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ግድቡ የሚያመጣውን ተፅዕኖ በማጥናት ላይ ሲሆኑ፣ ግብፅ የጥናቱ ውጤት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ትገልጻለች።
ይኸው ጥናት በስምንት ወራቶች ውስጥ እስኪጠናቀቅ ድረስ ግብፅ የግድቡ ግንባታ እንዲቋረጥ ስምምነት ተደርሷል ብትልም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የተደረሰ አዲስ ስምምነት የለም ሲል ማስተባበያ መስጠቱ ይታወሳል።
ኢሳት



No comments: