Tuesday, June 7, 2016

“እነሱ የሚፈልጉትን እኛ አንሆንም” ይላል ሃብታሙ አያሌው። እኛስ ? - ግርማ ካሳ



አንድ ደስ የምትለኝ አባባል አለች። ሕግ መንግስቱ የሚፈቅድለትን መብት ተጠቅሞ፣ ለሰላም፣ ለመብት፣ ለፍትህ ስለጦመረ፣ በፈጠራ ክስሽብርተኛተብሎ በወህኒ እየማቀቀ ያለው፣ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊው፣ ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ፣ ብዙ ጊዜ ጽሁፉን የሚያጠቃልልበት አባባል ናት።ሁሉም ለኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ለሁሉምየምትል። ደስ የምትለኝና ትክክለኛ አባባል።
ዛሬ ደግሞ ሌላ ሃሪፍ አባባል አነበብኩኝ። በሰማያዊ ፓርቲ /ቤት ነው። የሕሊና እስረኞችን እና የገዢው ፓርቲ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን ለማሰብ በተዘጋጀ ዝግጅት ወቅት የተነገረች። በወህኒ በደረሰበት ስቃይና ቶርቸር፣ በሽተኛ ሆኖ በአሁኑ ወቅት እየተሰቃየና ሕክምና እየወሰደ ያለው፣ ሃብታሙ አያሌው የተናገረው ነው።
እነሱ የሚፈልጉትን እኛ አንሆንምነበር ያለው ወጣቱ ሰላማዊ ፖለቲከኛና የቀደሞ የሕሊና እስረኛ ሃብታሙ አያሌው። በጣም ትልቅ አባባል።
እነርሱ እየደበደቡን፣ እያሰሩን፣ እየገደሉን፣ ከቤታችን እያፈናቀሉን ከመስሪያ ቤታችን እያባረሩን፣ አንገታችንን ደፍተን፣ ባርያ ሆነን፣ ተሸማቀን፣ እነርሡተነሱሲሉን እየተነሳን፣ቁሙሲሉን እየቆመን፣ እንደ ሮቦት እንድንኖር ነው የሚፈለጉት። እነርሱ፣ ራሳቸው ጠባብና ዘረኛ ሆነው፣ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ..” እየተባባልን እኛም ጠበን እና ተጣበን፣ የአስተሳሰብ ድሃዎች ሆነን፣ በዘር እንድንለያይ ነው የሚፈልጉት። እነርሱ ስል ራሳቸውንየጸረ-ሽብርተኛና የአገር ደህነነት ግብረ ሃይልብለው የሚጠሩት በነጀነራል መሐመድ (ሶሞራ) የነሱስ፣ በነጌታቸው አሰፋ የሚመሩት፣ በኔ እይታ፣ አገሪቷን እያሸበሩ ያሉትን ነው።
እነርሱ ዶር መራራ ጉዲና እንዳሉት ከጫካ ወጡ እንጂ ጫካ ከነርሱ ውስጥ አልወጣም። የሚፈልጉትን ለማቆየትና ለማግኘት የሚቀናቸው ጡንቻ ነው። የነርሱ የጨዋታ ሕግ ሃይል ነው። ሌላውም እንደነርሱ የቂም በቀልና የጫካ አስተሳሰብ እንዲኖረው ነው የሚፈልጉት። በአጭር አማርኛ ሌሎቻችን እንደርሱ የወረድን እንድሆን ነው የሚፈልጉት።
እንግዲህ ውሳኔው የኛ ነው። ሃብታሙ አያሌውእነርሱ የሚፈለጉትን እኔ አልሆንምብሏል። እኛስ ?
ብዙዎቻችች ተስፋ ቆርጠን፣ ነጻነታችን ሌሎች በዉጭ አገር ያሉ (ኤርትራ ያሉትን ጨምሮ) እንዲያጎናጽፉን እንፈለጋለን። ብዙዎቻችን በጨለምተኛ አስተሳሰብ ተውጠናል። ወደፊት ልናደርግ የምንችለው ላይ ከማተኮር ይልቅ አይምሯችን የታያዘው ባለፉት ስህተቶቻችንን ላይ ነው። ትላንት ስለወደቅን፣ ከአሁን ለአሁን እንደገና እንወድቃለን ብለን፣ እዚያው ትላንት በወደቅንበት ቦታ ነው ያለነው። ትግል ውጣ ዉረድ፣ መውደቅ መነሳት መሆኑን ረስተናል።
እንግዲህ ትግል የሚጀመረው ለራሳችን ቃል በመግባት ነው። ትግል የሚጀምረው በአይምሯችን አጭቀን ካስቀምጥናቸው የፍርሃት፣ የተስፋ መቁረጥ፣ የራስ ወዳድነት ጎጂ መናፍስት በመላቀቅ ነው። ሌሎች ነጻነታችንን እንዲሰጡን ሳይሆን መብታችንን ለማስከበር የራሳችንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ በመሆን ነው።እነርሱ የሚፈልጉትን እኔ አልሆንምበማለት ነው።
ላለፉት ስድስት ወራት በኦሮሚያና በሰሜን ጎንደር/ወልቃይት ጠገዴ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አይተናል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች አሁን ያለውን አገዛዝ የሚቃወሙ ናቸው። ሆኖም በወልቃይትና በኦሮሚያ የተነሱ ጥያቄዎች ከዘዉግ ጋር የተገናኙ ናቸው።
በኦሮሚያአዲስ አበባ ልትሰፋ ነውበሚል በማስተር ፕላኑ ዙሪያ ነው እንቅስቃሴው የተጀመረው። በመሬት ላራሹ ዙሪያ እንቅስቃሴዎች አገር አቀፍ ለማድረግ ጥረቶች ቢደረጉም የኦሮሞ ልሂቃን ግን ፍቃደኝነት አላሳዩም። እንደዉም በየቦታው የዘረኛውና የብዙዎች ደም ያለበት የኦነግ ባንዲራ ነው ሲዉለበለብ ነው ያየነው።
በሰሜን ጎንደር እና በወልቃይትእኛ ትግሬ አይደለንም፤ አማራ ነን“ … በሚል ነው እንቅስቃሴው የተጀመረው። ሕወሃቶችተጋሩ (ትግሬ) ናችሁበሚል ህዝቡ ላይ ጫና አደረጉ። ሕዝቡ ደስተኛ ስላልሆነ ተቃዉሞ አስነሳ። ሕወሃቶች የካርድ ጨዋታ ሲጫወቱ ሕዝቡም ማድረግ የማይፈለገውን ነገር አደረገ። የራሱን ካርድ መዘዘ። ለዘመናት ትግሬ፣ አማራ ሳይባባል፣ እየተዋለደ፣ ሲፈልግ በአማርኛ፣ ሲፈለግ በትግሪኛ እየተናገረ፣ ሲፈልግ ጎንድር፣ ሲፈለግ ሽሬ እየሄደ እየነገደ፣ ይኖር የነበረ ህዝብ ዉስጥ የዘረኝነት ግለቱ ጨመረ።ከዚያም የተነሳ ግጭቶች ተፈጠሩ።
እንግዲህ እንዳየነ፣ በሁለቱም ቦታዎች የተነሱ ተቃዉሞዎች ከኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት ….ጋር የተገናኙ ናቸው። ግን መሆን አልነበረበትም።ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ..” እየተባለ ክፍፍል አስፈላጊ አልነበረም። እነርሱ ያንን ነበር የሚፈልጉት። ስለሆነላቸውም ኦሮሞው በኦሮሞ ጥያቄ ዙሪያ ተቃዉሞ ሲያሰማ ብቻዉን ተመታ። በወልቃይት በአማራነት ዙሪያ ጥያቄ ሲነሳ በተናጥል መመታት ሆነ። ህዝቡ አማራ፣ ኦሮሞ እያለ በመከፋፈሉ፣በተበታተነ ሁኔታ የሚነሱ ተቃውዎዎችን ለመቆጣጠርና ለመጨፍለቅ ገዢዎች ተመቻቸው።
እንግዲህ መንቃት አለብን። ኦሮሞም፣ እንሁን አማራ፣ ሶምሌም እንሁን ትግሬ፣ አኙዋክም እንሁን ወላይታአዎን ልዩነትቶች አሉን፤ ግን ከሚለያየን የሚያስተሳስረን እና የሚያዛምደን እንደሚበልጥ፣ የብዙዎቻች ጥያቄ ተመሳሳይነት ያለው፣ የመብት፣ የዲሞክራሲ፣ የእኩለነት የልማት ጥያቄ መሆኑን፣ ያሉንን ልዩነቶች አጥብበን ልዩነቶቻችን የመከፋፈል ምክንያት ሳይሆን የዉበታችን መገለጫዎች መሆናቸውን ተረድተን፣ በጋራ በኢትዮጵያዊነት ስር መሰባሰብ ይኖብናል።እነርሱ እንደሚፈልጉት እኛ እኔ አንጠበም፣ እነርሱ የሚፈልጉትን እኛ አልሆንምማለት መጀመር አለብን።

Millions of voices for freedom - UDJ


No comments: