Tuesday, June 14, 2016

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አንድ እስረኛ ተገደለ፣ በሌሎች እስረኞች ላይ ጉዳት ደረሰ

ፖሊሶች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ማክሰኞ ዕለት ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ አንድ እስረኛ መገደሉን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።
የእስረኛን ቤተሰቦች በመደበኛ ሰዓት ምግብ እንዲያቀብሉ ዕገዳ ተጥሎ የዋለ ሲሆን፣ በመጨረሻ ምግብ ቢገባም እንደወትሮው ማነጋገር አልተፈቀደም።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት፣ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ለእስረኛች ከሶስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ይገባ የነበረው ስንቅ፣ እስከ ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ተከልክሎ የቆየ ሲሆን፣ ቤተሰብ ሲጓላላ መዋሉን መረዳት ተችሏል።
ከሰዓት በኋላ ቤተሰብ ስንቅ ይዞ እንዲገባና እስረኞቹን እንዲያገኝ የተፈቀደ ሲሆን፣ ቀደም ሲል እንደነበረው አሰራር 15 ደቂቃ ጊዜ ግን እንዳልተሰጣቸውም ታውቋል።
በቤተሰብ ላይ ማዘግየቱና ዕገዳው የተከተለው በወህኔ ቤቱ ውስጥ ከተከሰተ ችግር የተያያዘ መሆኑም ምንጮች ገልጸዋል። ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ፖሊሶች በሰነዘሩት ጥቃት ቁጥራቸው ባልታወቀ እስረኞች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ለጊዜው የአባቱ ስም ያልታወቀ ታምራት የተባለ አንድ እስረኛ መገደሉንም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። ወደ እስር ቤቱ አምቡላንሶች ሲመላለሱም ታይተዋል። ስለተከሰተው ሁኔታና ጉዳቱ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢሳት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ኢሳት

No comments: