Saturday, June 25, 2016

በኦሮሚያና በአማራ ክልል በግጭቶች የደረሱ ጉዳቶች በድጋሚ እንዲጣሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠየቁ

”330 በላይ ሰዎች ስለመሞታቸው መረጃ አለኝ” - መድረክ
የኢሰመኮን ሪፖርት አንቀበለውም ብለዋል

   የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተከሰቱ ተቃውሞና ግጭቶችን ተከትሎ የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርት እንደማይቀበሉት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ አስታወቁ፡፡ ከማንም የማይወግን ነፃ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ የጠፋው ህይወትና የደረሱት ጉዳቶቹ በድጋሚ እንዲጣሩም ጠይቀዋል፡፡ 

መድረክ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ተቃውሞና ግጭት 330 በላይ ዜጎች ስለመሞታቸው መረጃ እንዳለው ጠቁሞ የኮሚሽኑ ሪፖርት የሟቾችን ቁጥር በግማሽ ያሳነሰ ነው ብሏል፡፡  በኦሮሚያ ክልል 292 ሟቾች ስምና ሙሉ መረጃ እንዳለው የገለፀው መድረክ፤ 41 ያህል ማንነታቸው ያልተለዩትን ጨምሮ የሟቾቹ ቁጥር 330 በላይ ነው ብሏል፡፡ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት 400 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና የፀጥታ ኃይሉም ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀሙን የሚገልፅ ሪፖርት ማውጣታቸውን የጠቀሱት ሰማያዊና መድረክ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሟቾች ቁጥር 173 ብቻ ናቸው ማለቱ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡በተቃውሞ ወቅት በመንግስት የተወሰደው እርምጃአስፈላጊና ተመጣጣኝ ነውማለቱም የፀጥታ ኃይሉንና መንግስትን ከተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ የተወጠነ ነውብለዋል፤ ፓርቲዎቹ ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ፡፡
 ከኦሮሚያ በተጨማሪ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን እንዲሁም በደቡብ ክልል በኮንሶ ወረዳ፣ ዜጎች መብቶቻቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ የኃይል እርምጃ ተወስዶባቸዋል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ በዚህ ሂደት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡ 

በየአካባቢው ተቃውሞና ግጭቱን ተከትሎ የደረሱ ጉዳቶችን ገለልተኛ አካል እንዲያጣራ በተደጋጋሚ መንግስትን ሲጠይቁ እንደነበር የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤መንግስት ጥያቄያችንን ቸል ብሎ ራሱ መርጦ ባቋቋመው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲጣራ ማድረጉ የተቃዋሚዎችን ጥያቄና ማሳሰቢያ ወደ ጎን መግፋቱን ያመለክታልብለዋል፡፡ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ያልተጣራ በመሆኑም ኮሚሽኑ ያቀረበው ሪፖርት ተአማኒነትና ተቀባይነት የሌለው ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞና ጉዳዩ በድጋሚ ተጣርቶ፣ ጉዳቱ እንዲገለፅ አሳስበዋል፡፡ ተቃውሞና ግጭቶቹን ተከትሎ የታሰሩ የፓርቲ አባላት፣ አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እንዲፈቱ የጠየቁት ፓርቲዎቹ፤ በማረሚያ ቤት ይደርሳሉ የሚባሉ የመብት ጥሰቶችም በአስቸኳይ እንዲቆሙ አሳስበዋል፡፡ በሌላ በኩል በቅርቡ በአዲስ አበባህገወጥ ግንባታ ናቸውበሚል እየፈረሱ ያሉ ቤቶች፤ የዜጎችን መጠለያ የማግኘት መብት የሚቃረንና የሰው ህይወትም እየቀጠፈ በመሆኑ ድርጊቱን እንቃወማለን ብለዋል - ፓርቲዎቹ፡፡ 
ቤቶችን የማፍረስ እርምጃ በርካቶችን ቤት አልባ አድርጎ፣ ለተጎሳቆለ ኑሮ እየዳረገ ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ መንግሥት ከድርጊቱ እንዲታቀብ ጠይቀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መንግስት ተገቢውን ካሳ በመክፈል እንዲያቋቁማቸው የጠየቁት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ፤ የልማት ተነሺዎችም በአግባቡ መብታቸው ተጠብቆ መስተናገድ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ 
Addis Admass News

No comments: