Wednesday, June 8, 2016

በሰሜን ጎንደር ዳባት ግጭት ተቀሰቀሰ

በሰሜን ጎንደር ዳባት ከተማ ላይ በቀድሞ መንግስት የተተከለ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ወደ ትግራይ ክልል ለመውሰድ የተደረገ ሙከራ በህዝቡና በታጠቁ የመንግስት ሃይሎች መካከል ግጭት መቀስቀሱን እማኞች ለኢሳት ገለጹ።
የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሩን ለመውሰድ የመጡ ሁለት ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረው የዳባት ነዋሪ ህዝብ ከመንግስት ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ በመግባት ሲታኮሱ እንደነበር ከስፍራው ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለኢሳት እንደተናገሩት ትራንስፎርመሩን ጭኖ የነበረው መኪና መቃጠሉንም አስረድተዋል። በወቅቱ ተጭኖ የነበረው ትራንስፎርመር ህዝቡ ከመኪናው ማስወረዱም ታውቋል።
የአካባቢው ፖሊስ ትራንስፎርመሩን ለመጫን የመጡትን ሾፌሮች ማሰሩ የታወቀ ሲሆን፣ እስካሁንም ፍጥጫው መቀጠሉ ታውቋል።
ህብረተሰቡ ወደ ትግራይ ክልል ሲወስድ የነበረውን ትራንስፎርመር በሃይል እንዳይወሰድ ማገድ የቻለ ሲሆን፣ የፌዴራል ፖሊስም ከተማውን ተቆጣጥሮት እንደሚገኝ መረዳት ተችሏል።
በዳባት መንገዶች የተዘጉ ሲሆን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚጓዙ ወደ ሁለት መቶ መኪኖች መንቀሳቀስ አለመቻላቸውንና፣ የስልክ መስመር መቋረጡም ለማወቅ ተችሏል። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ድረስ በህዝቡና በፖሊስ መካከል ፍጥጫው መቀጠሉን ከስፍራው የደረሰ ዜና ያስረዳል።
25 አመት በላይ አገልግሎትን ሲሰጥ የነበረውን ትራንስፎርመር ወደ ትግራይ ክልል በመውሰድ በሃገር ውስጥ የተመረተን መሳሪያ በምትኩ አገልግሎት ላይ ለማዋል እቅድ መያዙን ከነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል።
የወልቃይት ጠገዴ ስኳር ፋብሪካ ንብረት የሆነና ራማ የተሰኘ ተቋራጭ ድርጅት ክሬን በማሰማራት ትራንስፎርመሩን ለመጫን ተሰማርቶ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎች፣ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ከባድ ተሽከርካሪ  ማሽኑን በማጓጉዙ ሂደት  ተሳታፊ እንደነበር አክለው አስታውቀዋል። በድርጊቱ ቁጣ የተሰማቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የሁለቱን ተሽከርካሪዎች ሹፌሮች በቁጥጥር ስር እንዳዋሉም ለመረዳት ተችሏል።
የዞኑ አስተዳዳሪዎች ከከተማዋ ነዋሪ ጋር ለመምከር ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ወደከተማዋ መግባታቸውንና የነዋሪው ቁጣ መቀጠሉን ምንጮች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አክለው ገልጸዋል።
ከወራት በፊት በተመሳሳይ ድርጊት ከጎንደር ከተማ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መሳሪያ (ትራንስፎርመር) ወደ ትግራይ ክልል እንዲወስድ መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

ኢሳት

No comments: