Thursday, June 16, 2016

በኦሮሚያ ክልል በመንግስታዊ ድርጅቶች የተካሄደውን ግምገማ ተከትሎ 12 ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ


በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ መንግስታዊ ድርጅቶች ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ግምገማ ተከትሎ 12 ሃላፊዎች ሃሙስ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የቀድሞ የገላን ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ከበደን ጨምሮ በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ላይ የነበሩ 12 የክልሉ አመራሮች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ግለሰቦቹ አርብ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሏል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የክልሉ ሃላፊዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክትትል ሲካሄድባቸው መቆየቱን የኦሮሚያ ክልል ስነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ለመገናኛ ብዙሃን ባሰራጨው መግለጫ አመልክቷል።

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በክልሉ የመንግስት ሃላፊዎች ላይ ግምገማ እየተካሄደ ሲሆን፣ ባለፈው ሳማንት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትና ምክትላቸው ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል።

ለወራት ያህል ጊዜ በቆየው በዚሁ ግምገማ እስካሁን ድረስ 500 የሚበልጡ ሃላፊዎች በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ ታውቋል።

የክልሉ ምክር ቤት አብዛኞቹ ሃላፊዎች ለእስር ተዳርገው የክስ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ በመግልጽ ለሎች ሃላፊዎች እየተፈለጉ መሆኑን አመልክቷል።

ኢሳት ዜና

No comments: