Tuesday, June 7, 2016

እነ አቶ በቀለ ገርባ በጨልማ ቤት ታስረው እንደሚገኙ ተገለጸ

አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች የኦፌኮ አመራሮች አሁንም በጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ጠበቃቸው አቶ ወንድሙ ኢብሳ ለኢሳት ገለጹ። በተመሳሳይም ጥቁር ልብስ እንዳይለብሱ የተከለከሉ ከአምቦ የመጡ 16 እስረኞች ጸጉራቸውን ተላጭተው /ቤት መቅረባቸውም ተመልክቷል።
ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓም ልብሳቸውን በመነጠቃቸው በሌሊት ልብስ ቁምጣና ከናቴራ እንዲሁም በባዶ እግር /ቤት የቀረቡት እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ በጨለማ ቤት ውስጥ መሆናቸውም ለኢሳት የገለጹት የታሳሪዎች ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ ናቸው።
አቶ ወንድሙ ኢብሳ ለኢሳት እንደተናገሩት እነ አቶ በቀለ ገርባ ግንቦት 23 ቀን 2008 የነበራቸው ቀጠሮ የተሰረዘው በሰብሳቢው ዳኛ መታመም እንደሆነ ቢገለጽም፣ እነ አቶ በቀለ ወደችሎት እንዳይሄዱ የተደረጉት ግን ጥቁር ልብስ በመልበሳቸው መሆኑን መረዳት ተችሏል።
የግንቦት 23 ቀጠሯቸው ጥቁር ልብስ በመልበሳቸው የተስተጓጎለው እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ ተለዋጭ ቀጠሮ ለግንቦት 26 የተሰጣቸው ሲሆን፣ በቀጠሮው ዋዜማ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ልብሶቻቸውን እንደወሰዱባቸው ለችሎቱ ማስረዳታቸውም ተመልክቷል። ልብሶቻቸውን ወስደው ወደ ጨለማ ቤት ካስገቧቸው በኋላ፣ በቀጠሯቸው ሰዓት የሚለብሱት አጥተው በቁምጣና ካነቴራ ችሎት ለመገኘት መገደዳቸውን አቶ በቀለ ገርባ ለችሎቱ አስረድተዋል።
እነ አቶ በቀለ ገርባ ወደ ችሎት ከመግባታቸው በፊት የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል በችሎት የተገኙ ከጠበቆች በቀር እንዲወጡ መደረጋቸውንም ከአቶ ወንድሙ ኢብሳ ማብራሪያ መረዳት ተችሏል።
በሌሊት ልብስና በባዶ እግር ችሎት ለመገኘት የተገደዱበትን ምክንያት ለፍ/ቤቱ ያስረዱት አቶ በቀለ ገርባ፣ ከእስር ቤቱ ውስጥ ባለው ዘረኝነትና አድልዎ መማረራቸውን በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን ገልጸው ወደ ሌላ እስር ቤት እንዲቀየሩ፣ ወይንም የእስር ቤቱ ሃላፊዎች እንዲቀየሩላቸው ጠይቀዋል። /ቤቱ ጥያቄያቸውን ካልመለሱ ከቀጣዩ ቀጠሮ በህይወት ለመቆየታቸው ጥርጣሬ እንዳላቸው አቶ በቀለ ማሳሰባቸውን ከታሳሪዎቹ ጠበቃ ከአቶ ወንዱሙ ኢብሳ ማብራሪያ መረዳት ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በኦሮሚያ ህዝባዊ አመፅ ለገደሉ ዜጎች ሃዘናቸውን ለመግለጽ በሚል ጥቁር ለብሰው ችሎት እንዳይሄዱ የተከለከሉ 16 ተከሳሾች፣ ለተቃውሞ ሁሉም ጸጉራቸውን ተላጭተው ሰኞ ዕለት /ቤት መቅረባቸው ታውቋል። እነዚህ  16 እስረኞች ከኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከአምቦ ተይዘው የታሰሩም መሆናቸውም ታውቋል።
ከኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ እንቅስቃሴ በተያያዘ በፌዴራል ከፍተኛ /ቤት ብቻ ክስ የተመሰረተባቸው 104 ሰዎች እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ያልታወቁ ደግሞ በምርመራና በክልል እስርቤት መገኘታቸውን መረዳት ተችሏል።
ኢሳት



No comments: