Friday, June 17, 2016

ኢትዮጵያ በጅቡቲ ድንበር ወታደሮቿን ማስፈሯ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በጎረቤት ጅቡቲ በምትዋሰንበት የደንበር አካባቢ በርካታ ወታደሮችን ማስፈሯ ተገለጠ።
ይኸው በኮሎኔል አመራር ስር የተሰማራው ወታደራዊ ሃይል ታዱራህ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በምትገኘው የባልሆ ከተማ የሰፈረ ሲሆን፣ የወታደሮቹ ቁጥር በትንሹ 150 እንደሚደርስ በደህንነት ዙሪያ ሪፖርቶችን የሚያቀርበው አፍሪካ ኢንተሊጀንስ አርብ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ በአፋር ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ አለመረጋጋትን እያሳየ እንደመጣ ያወሳው የደህንነት ተቋሙ ወታደሮቹ መሰማራት በተጠርጣሪ ታጣቂዎች ላይ ዕርምጃን ለመውሰድ ያለመ እንደሆነ አመልክቷል።
በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ የሚገኙ የአፋር ታጣቂዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድንበር አካባቢ ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።
ከወራት በፊት በዚሁ የድንበር አካባቢ የተቀሰቀስን ግጭት ተከትሎ በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ወደብ የጫኑትን ንብረት እንደያዙ በስፍራው ለቀናት መሰንበታቸው የሚታወቅ ነው።
ከቀናት በፊት በድንበሩ አካባቢ የሰፈሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች በሚጠረጠሩ የአፋር ታጣቂዎች ላይ እርምጃን ሊወስዱ ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ መሆናቸውን የደህንነት ተቋሙ ገልጿል።
ይሁንና፣ የኢትዮጵያም ሆነ የጅቡቲ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ በድርጊቱ በአካባቢ ውጥረት ማንገሱ ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የጅቡቲ ተቃዋሚ ሃይሎች ከወራት በፊት ለአምስተኛ ጊዜ የጅቡቲ ወደብ ሆነው በተመረጡ ኢስማዔል ኦማር ጉሌ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ማቅረብ በመጀመራቸው በሃገሪቱ ውጥረት በመታየት ላይ መሆኑን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የአፍሪካ ህብረትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት (ኢጋድ) በሚያዚያ ወር የተካሄደው የጅቡቲ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ነው ቢሉም የጅቡቲ ተቃዋሚ ሃይሎች ተቋማቱ ላይ ተቃውሞ ማቅረብ መጀመራቸው ታውቋል።
በሃገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አካላት እንቅስቃሴ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚገልጹት የፓርቲ አመራሮች ከጅቡቲ ወደብ መስፋፋትና ከአገልግሎት አሰጣት ጋር በተገናኘ ሙስና እየተስፋፋ መምጣቱን አክለው አስታውቀዋል።

ኢሳት

No comments: