Saturday, August 6, 2016

ስለምን ነገን ታበላሹብናላችሁ? ሃብታሙ - ሃብታሙን በተመለከተ ( Grace Abate)

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም የሃብታሙ አያሌውን የውጭ ህክምና አስመልክቶ የተለያዩ ምክንያቶችን እየሰጡ ሲያንከባልሉት የነበረውን ቀጠሮ ዛሬ እልባት ይሰጣሉ ብለን ተስፋ ብናደርግም፤ስለነሱ ተግባር እኛ ተሸማቀቅን፡፡ የመኃል ዳኛው ሁለት ነገሮችን ጠቅሰው ለመስከረም 25 2009 . ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡ 1. የካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ቦርድ በፃፈው ደብዳቤ ላይ ‹‹እዚህ መታከም ስለማይችል›› ብለው የተጠቀሙበትን ሃረግ በማውጣት እዚህ ማለት ካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል ነው ወይስ? በአገር ውስጥ? የሚለው ግልፅ አይደለም ያሉ ሲሆን፡፡ 2. ታካሚው የያዛቸው በሽታ በአገር ውስጥ የህክምና ተቋማት ሊታከሙ የማያስችል መሆኑ እና አለመሆኑን ለማረጋገጥ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መልስ ይዘው እንዲመጡ የሚል ነው፡፡
=
የመጀመሪያውን ብናየው ታካሚው ከሁለት በላይ የህክምና ተቋማት ታይቶ በሪፈር ወደ ካዲስኮ ከመሄዱ በላይ አሁን ያለበት የጤና ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ በግልፅ እየታወቀ እዚህ ማለት ምንድን ለማለት ነው? ብሎ መጠየቅ በሰብአዊነት ላይ ማሾፍ ጭምር ነው፡፡ ሁለተኛው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህ ህመም በግርድፉ አገር ውስጥ ህክምና ማድርግ ይቻላል ወይስ አይቻልም ብሎ መጠየቅስ ምን የሚሉት ነው? ህክምናው አገር ውስጥ መሰጠቱና አለመሰጠቱ ሳይሆን ዋናው ነገር ህመሙ የደረሰበት ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ጤና ጥበቃ የሃብታሙን የህመም ደረጃ ሳይሆን የሚያየው ህክምናውን የሚሰጡ ተቋማት የሉም ወይስ አሉ የሚለውን ነው፡፡
-
ይህ ማለት ህመሙ ገና ጀምሮት ለመታከም ያለና ህመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶበት እስካሁን ድረስ በህመም ማስታገሻ ያለ ህመምተኛን እኩል የሚያምህ ምንድን ነው? ብሎ ጠይቆ መልሱ ሲከተል፤ጀነን ብሎ እንትን እኮ በአገራችን ውስጥ በዚህ በዚህ የህክምና ተቋማት ይሰጣል እንደማለት ነው፡፡በተለይ የጥያቄው አካሄድ ይህን ፊት ለፊት የሚያመጣ ነው! ስለዚህ ጉዳዩን ቀድሞ ያለቀለት ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ይመስላል ጠበቃ አምሃ በቪኦኤ ቀርበው ከዚህ በኋላ እደማይገፉበት የገለፁት፡፡ ይህ ወጣት ፖለቲከኛ ይህን ስርዐት ከነምናምኑ በሰላም ትግል የወንድ በር ለመስጠት ሲታገል የነበረ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የበቀል ድርጊትን ማሳረፍ በትውልዱ ላይ ጥላቻን መዝራት ነው፡፡ሰዎቹ በዚህ ከባድ ጊዜ ውስጥ ሆነው እንኳን ስለምን የበቀልን ድርጊት እንደሚገፉበት አይገባኝም፡፡ የእነሱን ዛሬ አሳምረው ስለምን ነጋችንን እንደሚያበላሹ አይገባኝም???

No comments: